ሕወሓት በዋግ፣ በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ መክፈቱ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ

0
1107

ዕረቡ ነሐሴ 25 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የሕወሓት ቡድን በዋግ፣ በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ መክፈቱ አስታውቋል።

አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ “መንግሥት ለሰላም አማራጭ ዕድል ለመስጠት ሲል የሕዝብ ማዕበል አስነሥቶ ሕጻናትን፣ ወጣቶችንና አረጋውያንን ለመማገድ የመጣውን የአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂ፣ በምሥራቅ አማራ በኩል በጀግንነት ሲከላከል ቆይቷል።” ሲል ገልጿል።

ቡድኑ በምሥራቅ አማራ በኩል በቆቦና አካባቢው የከፈተው ወረራ በመከላከያ ሠራዊትና በደጀኑ ሕዝብ ጠንካራ የመከላከል ብቃት የተነሣ ባሰበው ልክ እንዳልሄደለትም አገልግሎቱ አስታውቋል።

”በዚህም ምክንያት ለሰላም የተሰጠውን ሁለንተናዊ አማራጭ አሽቀንጥሮ ጥሎ ወረራውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እያስፋፋ ይገኛል።” ያለው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ቡድኑ በዋግ፣ በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ መክፈቱን ገልጿል።

ይሄንን የሕወሐት ወረራ የመከላከያ ሠራዊት በተሟላ ዝግጅትና በጽኑ ቁመና እየተከላከለ እንደሚገኝም የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በመግለጫው አስታውቋል።

”ለሰላም የተዘረጋው እጅ በሕወሓት ዕብሪታዊ ወረራ ምክንያት እንዳይታጠፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚቻለውን ያድርግ“ ሲልም አሳስቧል።

በተጨማሪም ”ወገን የሆነው የትግራይ ሕዝብም ይሄንን የዕብሪት ወረራ በማውገዝ ሕወሓት ከሚያስከትልበት መከራ ራሱን ነጻ ያውጣ” ሲል ጥሪ አቅርቧል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here