በክረምት ወቅት የሚደረግ ጉዞ እምበዛም የሚመከር እንዳልሆነ እሰማለሁ። መንገዶች አመቺ ላይሆኑ ይችላሉ ከሚለው ሐሳብ አንስቶ የአየር ጠባይ ፈታኝ መሆኑ እንደ ምክንያት ሲጠቀስም ገጥሞኛል። ግን ደግሞ የምድሪቱ የልምላሜ መልክ እንዴት ውብ እንደሆነ ለማየት ከዚህ ወቅት የተሻለ መኖሩን እንድጠራጠር ሆኛለሁ።
ከአዲስ አበባ 660 በላይ ኪሎሜትር ተሻግረን፣ የደብረ ታቦር ወይም የቡሄ በዓልን በደብረ ታቦር ከተማ አክብረን ማግስቱ ላይ ነው። በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ አሳሳቢነት እና ግብዣ ወደ አንድ ጥንታዊና ታሪካዊ ቦታ አቀናን። ወደ ሠማዕቱ ቅዱስ ገላውድዮስ ጥንታዊ ቤተክርስትያን።
ከቤተክርስትያኑ ደጅ ላይ ሆነን በደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር የሆኑት ጌታቸው ጋሻው ስለስፍራው እና ስለቤተክርስትያኑ ታሪክ አጫወቱን። ከነገሩን ላካፍላችሁ፤
ሠማዕቱ ቅዱስ ገላውድዮስ ጥንታዊ ቤተክርስትያን በ1550ዎቹ በአጼ ገላውድዮስ የተመሠረተ ነው። ሕንጻ ቤተክርስትያኑ እንዲገነባና በዛ ስፍራ እንዲገኝ ምክንያት የሆነው ደግሞ የንጉሡ ስዕለት መግባት ነው። በጊዜው ግራኝ አሕመድን ድል ማድረግ ከቻሉ በቦታው በቅዱሱ ሰማዕት እና በቅድስት ድንግል ማርያም ሥም ቤተክርስትያን እንደሚያሠሩ ቃል ገብተው ነበር።
በዛ መሠረት የተገነባው ይህ ቤተክርስትያን፣ የጎንደር ኪነሕንጻን አጉልቶ ያሳያል። ይህንንም የታሪክና የቅርስ መምህሩ ጌታቸው ሲያብራሩ እንዲህ አሉ፤ ‹‹በኪነ ሕንጻ ጥበብ ታሪክ ሦስት ዋና ዋና ምዕራፎች አሉ። የመጀመሪያው ቅድመ አክሱም የነበረው ነው። ያንን የተከተለው የላሊበላ ሲሆን ሦስተኛው የጎንደር የኪነ ሕንጻ ጥበብ የሚባለው ነው። ይህም ትንንሽ ድንጋዮችን በኖራ በማጣበቅ ቤት የመሥራት ጥበብ ነው። ግንባታው (የቤተክርስትያኑ) የዛን ዘመን የግንባታ ጥበብ ያሳያል።››
ከዚህ የኪነ ሕንጻ ጥበብ ባሻገር በዚህ ቤተክርስትያን ውስጥ የታዩና የተሰሙ ብዙ አስደናቂ ነገሮች አሉ። ከዚህም የብዙዎችን ቀልብና ትኩረት የሚስበው የአፈሩ ነገር ነው። በዚህ ቤተክርስትያን ውስጥ የቀብር ስነስርዓት የሚፈጸመው በቅጥር ጊቢው ውስጥ ነው። ታድያ ግን ጊቢው ለበርካታ ዘመናት የአካባቢውን ማኅበረሰብ በዚህ ሲያገለግል፤ ቦታ ሞላ ተብሎ አያውቅም። ምክንያቱ ደግሞ ቦታው ሰፊ ሆኖ ወይም ሌላ ብልሃት ተገኝቶ አይደለም።
ጌታቸው እንደነገሩን ምንም እንኳ እስከ አሁን ሳይንሳዊ ጥናት ተደርጎ ማብራሪያ ባይሰጥበትም፣ በቤተክርስትያኑ ቅጥር የሚገኘው አፈር የተለየ ባህሪ አለው። ይህ የተለየ ባህሪው ምንድን ነው የተባለ እንደሆነ መልሱ እንዲህ ነው፤ የት እንደሚያደርሰው የሚታወቅ ባይሆንም፣ አንድ ቀብር ከተፈጸመ በኋላ የተቀበረው አካል አንድ እንኳ ምልክት ሳይቀርለት ይሰወራል። ወይም ደግሞ ‹እዚህ ጋር እገሌ ተቀብሯል፤ የእገሌ የመቃብር ስፍራ ነው› ብለው ቆፍረው ቢመለከቱ ዋሾ ይባላሉ እንጂ አንዳች ለምስክርነት የሚገኝ ነገር የለም።
‹‹ስለዚህ ሐውልት አይሠራም። ይሄ የእገሌ የቀብር ቦታ ነው ተብሎ የሚለይ ነገርም የለም። መሬቱ ሲቆፈር ሁሌም አዲስ መሬት ነው የሚሆነው።›› ሲሉ ጌታቸው በቦታው የሚገኘውን አፈር አስደናቂ ባህሪ ነገሩን።
በጉዳዩ ላይ የተሠራ ጥናት ባለመኖሩ አዲስ ማለዳ ሐሳብ እንዲሰጡ ወደ አጥኚዎች አላቀናችም። ግን ከዚህ በኋላ ቦታውና ይህ አስደናቂ ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝና የአፈር ጥናት ባለሞያዎች ጉዳዩ ምን እንደሆነ እንዲመረምሩ መረጃውን በማድረስ ድርሻዋን ትወጣለች።
ይህ ክስተት ወይም የአፈሩ ተፈጥሮና ሁኔታ ከተለመደው ወጣ ያለ ነው። ከተለመደው ብቻ ሳይሆን አስደናቂ ከተባለውም የተለየ ነው። ለምሳሌ ከዚህ ቀደም ነፍስ የተለየችው ስጋ ፈጽሞ ሳይበሰብስና ስጋው ሳይፈርስ የሚገኝባቸው፣ በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዱስ የተባሉ ሃይማኖታዊ ስፍራዎች መኖራቸው ይታወቃል። ይህንንም በሚመለከት ባህር ተሻግረው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ አጥኚዎች የተለያየ መላምት ሲሰጡ ተሰምቷል።
ይህኛው ግን ከዛም ለየት ያለ ነው። የቀደመውን በእምነት ለሚቀበሉ ሰዎች ተአምርና የቃል ኪዳን ውጤት እንደሆነ ሲናገሩ የምንሰማ ሲሆን፣ ሳይንሱ ግን ይህ ነው የሚል ተጨባጭ መልስ ሰጥቶ አያውቅም። ምንአልባትም እንዲህ ያለው ተአምር በኢትዮጵያ ብቻ ያለ ከሆነም በጥናትና ምርምር በመመልከት የባለሞያዎችን ዕይታ ማግኘቱ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ ሊያግዝ ይችላል። ማብራሪያ ቢገኝለትም፣ ባይገኝለትም ግን ነገሩ አስደናቂ መሆኑ አይቀየርም። በዛም አለ በዚህ ግን ውጤቱ ለቱሪዝም ዘርፍ ቀላል የማይባል ግብዓት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
በስፍራው ለጉብኝት ከተገኘን መካከል ለጥናትና ምርምር ምነው ተዘገየ የሚል ጥያቄ ለቅርስና ታሪክ መምህሩ ጌታቸው ቀርቦ ነበር። እርሳቸውም የእኔ ዕይታ ነው ሲሉ እንዲህ አካፈሉን፤ ‹‹እንደ አገር የአፈር ጥናት ላይ የተራቀቀ ጥናት መሥራት ይቀረናል ብዬ አስባለሁ። ምናልባትም ማስተዋወቅ ላይ የእኛ ድክመትም ስላለ ሳይመጡ ቀርተው ይሆናል። ግን በሳይንስ እስከ አሁን ተረጋግጦ እንዲህ ስለሆነ ነው የሚል ማብራሪያ መስጠት አይቻልም።››
ጌታቸው አያይዘው እንደነገሩን ከሆነ፣ በአካባቢው የታመነ አንድ ታሪክ አለ። እንዲህ ነው፤ በዘመኑ ሰዎች ለቀብርና ለተለያየ መንፈሳዊ አገልግሎት እስራኤል መሄድን አብዝተው ይመኙና ይናፍቁ ነበር። ምክንያቱም እስራኤል የክርስትና መነሻ ናት። ይህን ታሳቢ በማድረግ ታድያ በጊዜው ከእስራኤል አፈር ተጭኖ መጥቶ በዚህ ቤተክርስትያን ቅጥር ጊቢ እንዲሆን ተደርጓል። ከእስራኤል ብቻም ሳይሆን በኢትዮጵያም ከዋልድባ ገዳም አፈር ተጭኖ መጥቶ በዚህ ስፍራ እንዲገኝ ሆኗል።
እርግጥ ነው! ይህ ታሪክ የአፈሩን ባህሪ ለማስረዳት በቂ ትንታኔ አይደለም። ምክንያቱም በእስራኤልም ሆነ በዋልድባ ገዳም የተቀበረን የሰው አካል የሚሰውር እንዲህ ያለው ክስተት ስለመኖሩ የተነገረ ነገር የለም። ለጊዜው ግን በእምነት ለሚቀበሉት ቦታው ቃልኪዳን ያለው ቅዱስ ስፍራ እንደሆነ ይታመናል።
ከዚህ ስንሻገር፣ በዚህ ቤተክርስትያን ውስጥ በርካታ ነዋያተ ቅድሳት እና ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ። ከእነዚህም የግራኝ አሕመድ ለምድ አንደኛው ነው። ይህም በተገደለ ጊዜ ለብሶት የነበረው እንደሆነ መምህሩ ጌታቸው ባደረጉልን ገለጻ ጠቅሰዋል። ከዛም ባለፈ የነገሥታት የክብር እቃዎችን ጨምሮ የቆዩ የብራና መጻሕፍት በቤተክርስትያኑ ይገኛሉ።
ከብራና መጻሕፍቱ አንድ ሰው ብቻ የማያነሳቸው ግዙፍና ጥንታዊ የብራና መጻሕፍት እንዳሉም ተነግሮናል። እነዚህም በርካታ ሲሆኑ የተጻፉበት ጊዜ ከጥንት ከቤተክርስትያኑ መታነጽ ጀምሮ ከአምስት እና ዐስር ዓመት በፊት እስከተዘጋጀው ድረስ የሚያጠቃልሉ ናቸው። የሚገርመው በዚህ ቦታ እስከ አሁን የብራና ጽሑፍ አለ፤ የብራና ላይ ጸሐፊዎችም አሉ።
ይህ ቤተክርስትያን እንደ ሌሎች በርካታ አብያተ ክርስትያናት ሁሉ የሚተዳደረው በምዕመኑ መዋጮ ነው። እንደ ልምዱ ‹በእንተ ሥማ ለማርያም› ብለው ከነዋሪው ደጅ ጠንተው የእለት ቀለባቸውን የሚያገኙ የቆሎ ተማሪዎችም በዚህ ስፍራ አሉ። አብነት ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ሲሆን፣ የድጓና የቅኔ ትምህርት ይሰጣል።
ታድያ ይህን የመሰለ ታሪክ የያዘን ስፍራ የማስተዋወቅ ሥራን ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ እንደጀመረ ሰምተናል። በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍልም በቅርቡ ማለትም ከአራት ዓመት ገደማ በፊት ነው የተከፈተው። እናም ትልቁን ኃላፊነት ይህ የትምህርት ክፍል የሚወስድ ሲሆን፣ ከተሠራው ይልቅ ብዙ የሚሠራ የቀረ ሥራ እንዳለ ነው ጌታቸው የገለጹት። የቤተክርስትያኑ ታሪክና ቅርስ ተጠብቆ እንዲቆይም ሙያዊ ድጋፍ በዩኒቨርሲቲው በኩል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ ቤተክርስትያን ታድያ ከበጌ ምድር በረከቶች መካከል አንደኛው ነው። የአሁኑ ደቡብ ጎንደር እና አካባቢው በጌ ምድር ተብሎ ይታወቅ እንደነበር የነገሩን ደግሞ መሠረት ወርቁ ናቸው። እርሳቸውም በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ሲሆኑ የአለቃ ገብረሃና የባህል ጥናት ዳይሬክቶሬትም አስተባባሪ ናቸው።
በጌ ምድር የሚለው ሥያሜ አንድም ‹በጎ ምድር› ከሚል የመጣ እንደሆነ እንደሚታመን ይናገራሉ። ይህም ስፍራው መልካም የሆነ ምድር ነው እንደማለት ነው። አንድም አካባቢው ደጋማ ስለሆነና በብዛት የበግ እርባታ ስላለበት ለዛ ነው ‹በጌ ምድር› የሚል ሥም ያገኘው የሚል ዕይታ አለ።
በአሁኑ አጠራሩ ደቡብ ጎንደር የተባለው በጌ ምድር ታድያ ይህን የሠማዕቱ ቅዱስ ገላውድዮስን ቤተክርስትያን ጨምሮ በርካታ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ቅርሶች ያሉት ነው ብለዋል።
መሠረት፣ አካባቢው የጥንታዊው፣ መካከለኛውና ዘመናዊው የታሪክ አሻራ አለው ሲሉ የገለጹት ይህ አካባቢ፤ ከዘመናት ቀድሞ ደግሞ ‹ምድረ ዳብር› እንዲሁም ‹አፈሯናት› (አፈሩ እናት) የሚል ሥም እንደነበረው ጠቅሰዋል። ‹አፈሯናት› ተብሎ ምድሩ የተሞካሸውና ‹አፈሩ እናት ነው› የተባለው የማያበቅለው ባለመኖሩ ነው።
ስለበጌ ምድርና ቀደመው ታሪክ መሠረት በብዙ አጫውተዉናል። ለጊዜው ይህን ያህል ካልን የቀረውን በተያያዘ ጉዳይ ስንመለስ እናወሳዋለን።
ለመዝጊያ
ለሰማይ የቀረብን እስኪመስለን ወርዶ ይጋርድ የነበረው ደመና በዝናብ ተተካ። የክረምት ጉዞ እንዲህ ዝናብ ሲሆን ነው ለመንገድ የማይመቸው!
‹ወዲህ ኑ! እህል ሳትቀምሱማ አትሄዱም!› አሉን። ከቤተክርስትያኑ ጊቢ አለፍ ብሎ ወደሚገኝ፣ በቆሙ ቀጫጭን እንጨቶች ወደተዋቀረ አንድ አዳራሽ አመላከቱን። ዝናቡ እያሳደደን በሚመስል ሁኔታ እኛም በሩጫ በአዳራሹ ጣሪያ ስር ታደምን። እንግዳ ተቀባይ መንፈስ ያላቸው የሠማዕቱ ቅዱስ ገላውዴዎስ ቤተክርስትያን አባቶች፣ ሊቃውንትና መሪጌታዎች እንዲሁም አዳጊ የሆኑ ልጆችና ወጣቶች ልብ የሚያሞቅ መስተንግዶ አደረጉልን። የሚጣፍጠውን አዘጋጅተው ጋበዙን። ስለሁሉም ሁሉን እናመሠግን ዘንድ ደግሞም እንዳንረሳ ያሳዩን ፍቅር እንደ ዕዳ አለብን። ሰላም!
ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014



