በሙሉቀን ታሪኩ በተርጓሚነት የሠራውን ‹የጀግና ማኒፌስቶ› እንዲሁም በዝግጅት የተሳተፈበትንና በቢንያም ዓለማየሁ የተተረጎመውን፤ ኹለቱን የሮቢን ሻርማ መጻሕፍትን መነሻ በማድረግ፣ አብዲ መሐመድ ከደራሲው ከሮቢን ሻርማ ጋር ሲያስተዋውቀን፤ መጽሐፉ ለአንባብያን ሊያደርስ ስለያዘው መልዕክትም እንደሚከተለው አጋርቷል።
ክረምት ተጠናቆ ሲገባ ሥጋዬን ብቻ ሳይሆን ነፍሴንም የሚያነቃቁ መጻሕፍትን ማንበብ ያሰኘኛል። በዚህ የቆየ ልምዴ ምክንያት ወቅቱ ሲቀየር ነፍሴ መንፈሳዊ ምግብ የመሻት ምልክት ታሳየኛለች። ጥቆማው እንደደረሰኝ የቅዱሳንና የጻድቃን፣ የዳኢዎችንና የሙፍቲዎችን መጻሕፍት በማሰስ እደክማለሁ። እነዚህ መጻሕፍት እግዜርን የምለማመንባቸው የስለት ዣንጥላዎቼ ብቻ አይደሉም፣ አብዝቶ ለስጋዊ ተድላ ያደላ የእውቀት መሻቶቼን የማስታግስባቸው የግል ሱባኤዎቼም ጭምር ናቸው።
እነሆ ከሰሞኑ ይህን የቆየ ግብሬን እንደ ጾም የገደፍኩት ዝነኛው የአመራር ጥበብ አማካሪ የሮቢን ሻርማ ኹለት መጻሕፍት በቋንቋዬ ተደጉሰው ሾልከው እጄ ሲገቡ ነው። ወይም እንደ ሉሲፈር ደርሰው ሲጠናወቱኝ ነው ልበል ይሆን? (በነገራችን ላይ…ብዙዎቻችን ልባችንን የምንሰጠው ከመንፈሳዊ አስተምህሮት ይልቅ ለስጋዊው ዓለም እንደመሆኑ… የሚመራንን የግል ፍልስፍና ልቡን የምናውቀው ወደ አምላክና ቤተ-እምነት በምንቀርብባቸው የጥሞና ጊዜያት እንደሆነ መንክራት ግርማ ወንድሙ “በማለዳ መያዝ” ባሉት መጽሐፋቸው ውስጥ አስፍረዋል።)
ሮቢን ሻርማ በዚህ ዓመት ኹለት መጻሕፍት (THE 5 AM CLUB እና THE EVERY DAY HERO MANIFSTO) ወደ አማርኛ የተመለሱት ያለምክንያት አይደለም። ተርጓሚው ሙሉቀን ታሪኩ ቀደም ሲል እግር-በእግር አስግሮ በማደን ዘመን ዘለል ግለታሪኮችን በውርስ ሲተረጉም እናውቀዋለን። የማህተመ ጋንዲ፣ ኔልሰን ማንዴላ፣ ማልኮም ኤክስ፣ ጆርጅ ኦርዌል…ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው። ይሁንና በይበልጥ ሚያስደምመው በሮቢን ሥራ ላይ ከወትሮ በተለየ በዝግጅትና አርትኦቱ ሌሎች ኹለት እውቅ ባለሙያዎችም መሳተፋቸው ነው።
እኔም በእጅጉ በአግራሞት የሞላኝ ገና ሳልገልጠው የተርጓሚዎቹ የደቦ ርብርብ ነበር። በእርግጥ ቅንጅታቸው የሰመረ ሆኖ ያገኘሁት መጽሐፍቹን እያነበብኩ ማጋመስ ሳልጀምር ነበር። (ሰውየው ማን መሆኑን ስገነዘብም ጭምር) የሕይወት ክህሎት መምህሩና ደራሲው ሮቢን ሻርማም ቢሆን ከሌሎች ገናና ሥራዎቹ በላቀ በተለይ እነዚህን ሥራዎች ለመጻፍ በጥልቀት ወደ ራሱ ገብቷል። ከዚህ ቀደም ከሚያውቀው የበለጠ ለማበርከትም በአያሌው ጥሮበታል፤ ግሮበታል። እኔም መጽሐፎቹን አንብቤ ስጨርስ ደራሲው ከጅምሩ ከነበረው የተለየ ሰው ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ሮቢን ሻርማ ማነው?
ከደራሲው በፊት ሰውዬውን መመልከት ይበጃል። ምክንያቱም መጻሕፍቱ በአብዛኛው የተፈተነ የግል ልምዶቹ ውጤት ናቸው። ለመነሻ እንዲሆነን ከእድሜ፣ ከንባብ፣ ከሕይወት ተሞክሮ ሙላቶቹ ጥቂት እንዝገን። …በቤቱ ቲቪ የሚባል የለውም። መኖሪያ ቤቱ በመጻሕፍት የተሞላ ነው። መጽሐፍ የመግዛት ሱስ አለበት። (ይህ ሱስ ግን ጤናማ ነው) በሕይወት እስካለ ማንበብ ከሚችለው የመጻሕፍት ቁጥር የበለጠ ሸምቷል።
በግሉ የመጻሕፍትን ያህል በገንዘብ የሚገዛ ምርጥ ነገር ያለ አይመስለውም። ብዙ ጊዜ መላ ሕይወትን ሊቀይር የሚችል የአንድ መጽሐፍ ብዙ ቅጂዎች ይገዛል። የጀምስ አለን “as you think” ስድስት ቅጂዎች፣ የሼል ሲልቨርስቴይን “the giving tree” ስምንት ቅጂዎች፣ የፖውሎ ኮዌል “the alchemist” አስራ አንድ ቅጂዎች…ወዘተ
ዘወትር ከሌሊቱ 11 ሰዓት ሲል ከእንቅልፉ ይነቃል። በዚህ ሰዓት ተነስቶ ወደማይሞትና የማይሸነፍ ይቻላል መንፈስ ይገባል። በዚህ ሰዓት መንቃቱ ራሱን ለማወቅ፣ ምጥቀቱን ለማውጣት፣ ከውስጡ የተቀበሩ እምቅ ጉልበት ለመፈልቀቅ የመጣ መልካም አጋጣሚ ነው ብሎ ያምናል። ያልተገደበ ስኬትን እጣ-ፋንታው ለማድረግ ሰዓቱን አብዝቶ ይገለገልበታል። በዘመኑ በዚህ ሰዓት በመንቃት አብዮታዊ በሆነ ዘዴ በመጠቀም ግዛቱን ይገነባል። የኢኮኖሚ ግዛት አንዱ ነው።
ከዚህ ሌላ የምርታማነት፣ የሥነ-ጥበብ ፣ የሰብአዊነት፣ የበጎ አድራጎት የግል ነፃነት እና የመንፈሳዊ ግዛትም ጭምር መፍጠር ችሏል። በሚያየው ነገር በጥልቅ ይረካል። ዓለምን ፍጹም ልዩ በሆኑ ሌንሶች ይመለከታል። ማንም ሰው ቢሆን “ከከተማ ጫጫታ ሲርቅ ነው በትክክል ማን እንደሆነ ታስቦ ወደዚህች ምድር እንደመጣ የሚያስበው” የሚላት መርህ አለችው። ከዚህ ባሻገር ሮቢን ሻርማ ደራሲ ነው፡፤ አንባቢውን ያከብራል። ለእነርሱ የሚመጥን ምርጥ ነገር መስጠት እንዳለበትም ያምናል።
ስለዚህ ሥራውን በተመስጥኦና ጥልቀት ይሠራል። ሲጽፍ እያንዳንዱን መስመር በጥንቃቄ ለመጻፍ ብዙ ጊዜ ያጠፋል። ቢሆንም የራሱን የሥነ-ጽሑፍ ሥራዎች ከፍ ያለ ደረጃ ሰጥቶ አያስቀምጥም። (እንደኛው አለማየሁ ገላጋይ) ነገር ግን ከ15 ሚሊዮን እትም የበለጠ የተሸጠለትና ሥራዎቹ በ92 ቋንቋዎች ተተርጉመው የተነበቡለት ሮቢን በዓለም ዐቀፍ የተነባቢነት ደረጃ በሕይወት ካሉ ደራሲያን አንደኛ ነው።
ምን እንማራለን?
ከሮቢን ሻርማ የምንማራቸው ቁምነገሮች ተፈትነው ካለፋ የግል ልምዶቹ ብቻ አይደለም። ገና በማቆጥቆጥ ላይ ያለ ችሎታችንን፣ ሕልማችንን እውን ለማድረግ የሚያስችል ፍልስፍና እንማርበታለን። በተቸረን ጸጋ የላቀ ሥራን ለማበርከት የሚያስችል ልዩና አዳዲስ መንገዶችን ያመላክተናል። ሕይወትን በአስደናቂ መንገድ ለመኖርም ሆነ የመንፈስ ነጻነት ለመጎናፀፍ የሚያስችሉ ጥልቅ ሐሳቦችን እንገነዘባለን።
ሮቢን የሚያስገነዝበን በቃላትና በምክር ብቻ አይደለም። (ሰውዬው እንደ ሌሎች የሥነ-ልቦናና የሥነ-ስኬት ሊቆች መካሪ ብቻ አይደለም። አመራማሪ፣ ጠያቂ፣ ሞጋች፣ ጎብኚ፣ አሳሽ፣ ፈታሽም ጭምር እንጂ) ቦታዎቹ ድረስ በመሄድ…በመውጣትና በመውረድ ውስጥ ባለ ድካም ውስጥ ፎቶ በማስቀረትም ጭምር በመሆኑ ውስጣችን ሰርጾ ለመግባት ከአሳማኝ በላይ ምክንያቶች አሉት።
በወጣትነቱ የዓለም የቦክስ ሻምፕዮን ከመሐመድ አሊ ጋር የነበረው ገጠመኝ ስለተማረው ሰብአዊ ትህትና፣ በመቀጠል የኖቤል ተሸላሚው ታላቁ መሪ ቄስ ዴዝሞንድ ቱቱ ጋር በነበረው ቆይታ ስለሰው ልጅ እኩልነት የቀሰማቸው ትምህርቶች፣ በመኪና አደጋ ሙሉ ለሙሉ ፊቱን ካጣው የመኪና ግልቢያ የዓለም ሻምፒዮን “ኒካላውዳ” የቀሰማቸው ታላቅ ጥንካሬ፣ ዐይኑን በማርገብገብ መጽሐፍ ስለጻፈው የሞት አፋፍ ላይ ስለነበረው የቅንጦት ሕይወት ስለኖረው ጂን-ዶሚኒክ፣ በሞታቸው ጫፍ ላይ ያሉ ሰዎች 5 ዋነኛ ፀፀቶቻቸው፣ ሮም ድረስ ተጉዞ የሊዮናርዶ ዳቬንቺ ሥራዎች ያሉበት ኤግዚቢሽን በመጎብኘት በኪነ ሕንጻ፣ ሥነ-ስዕል፣ ቅርጻ ቅርጽ እና ከግል ማህደሮቹ የሸመታቸው ግኝቶች ሌሎችም በአጥጋቢ መልኩ በምልአት በመጽሐፉ ተዘርዝሮ እናነባለን።
በይበልጥ ከራሱ ክህሎት በመነሳት የሚነግረን አስተምህሮቱ ሚዛን ይደፋብናል። ውስጣችን እንዳለ የምንጠረጥረው ያልተጠቀምንበት ችሎታ ወደ ስቃይ እንደሚቀየር ነግሮን ሲያበቃ በዚህ ሁከት በበዛበት ዘመን ሳለን በጥሞና የምናስብበት ክፍተት በመፈለግ የልጅነት ሕልማችንን፣ የተረሳ የሕይወት ግባችንን መልሰን እንድናገኝ በማመላከት ይጠቁመናል። ወደፊት ብዙ ዓመታት ምድር ላይ የማይቆዩ ሰዎችን ለማስደሰት ብለን ታላቅ ሕልማችንን እውን ከማድረግ እንዳንቦዝን ይጎተጉተናል።
በሮቢን ሻርማ ኹለቱም መጻሕፍት ውስጥ ፍርሃቶቻችንን እና ቅዠቶቻችንን እንዴት በምንኖርለት ሕልም ብርታት ድል መንሳት እንደምንችል እንማርበታለን። ጆናስ ሶክ የተባለ ደራሲ፤ ‹‹ሕልምም ቅዠትም አይቻለሁ። ነገር ግን ቅዠቶቼን መቆጣጠር የቻልኩት በሕልሞቼ አማካኝነት ነው›› ያለው ለዚህም ሳይሆን ይቀራል?
መቋጠሪያ
ሮቢን ሻርማ ራሱን የቻለ ጀግና ነው። የጀግንነት ተምሳሌት መሆን የሚችል የአመራር ጥበብ ሊቅ፣ አማካሪ፣ በጎ አድራጊ፣ ለሩብ ምዕተ-ዓመት ብርቱ ጥረት አድርጎ የሰው ልጆች ውስጣዊ ችሎታቸውን እንዲያውቁ ሲያግዝ የኖረ ቁንጮ ነው። በኹለቱም የብዕር ትሩፋቶቹ አበክሮ የሚያስረግጠው ስለ ጀግኖች ነው። ለእኛ ከአንድ መጽሐፉ “አንድ-ጀግና” ማወቅ በቂያችን ነበር። ግን አልሆነም፣ እልፍ የሆኑ በጓዳ ያሉ ያልተነገረላቸው፣ ሥመ ጥር ሆነው ደግሞ በዓለም መድረክ የተጨበጨበላቸው ጀግኖችን እንተዋወቅበታለን።
‹‹ጀግኖች በማለዳ ነው የሚፈጠሩት›› የሚል መርህ የያዘ ንዑስ ርዕስ ያለው መጽሐፉ፤ እናንተም ዘወትር 11 ሰዓት በመንቃት ሕልማችሁን ገንቡ ሲል ያነቃናል። ማልዶ ተነስቶ ፀጥታ ባለበት ሁኔታ ራስን አንቀሳቅሶ ቀንን መጀመር ለጥራት ልዩ ነው። ቀናችንን ብርቱ እና ነፃ ሆኖ መጀመርን የመሰለ ነገር የለም። ማንኛውም ልዩ አስተዋጽኦ ያለው ታዋቂ ተሸላሚ አትሌት፣ የድርጅት ኃላፊ፣ የተጨበጨበለት የኪነ ሕንጻ ባለሙያም ሆነ ሌላ በእንዲህ ዓይነቱ ልምድ ያልፋል።
በሌላኛው ጥናታዊ የምርምር ዘገባም የ’’ጀግኖችን ማኒፌስቶ’’ በታላቅ ተጋድሎ ከምንጩ እየቀዳ በማፈከር የግዳዩን ፍሬ በነፃነት አንድናጣጥም ከማዕዱ ያጋራናል። ታላላቅ ሕልም ካላቸው ጀግኖች አውደ ግንባር በአካል ወስዶ ከተሞክሯቸው የሚያሳፍሰን አያሌ ቁምነገሮችን ነው። ብዙ ጊዜ ሕይወትን በአግባቡ ኖርን የምንለው ጊዜያችንን ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ተጠምደን ስናውል ብቻ የሚመስላቸው ሰዎች ብዙ ናቸው።
ነገር ግን የሕይወትን ውበት የምታጣጥሙበት ጊዜ ሊኖራችሁ ይገባል ይለናል ሻርማ። በእርግጥ አሁን ከገጠመን አለቅጥ ከናረው የኑሮ ውድነት አንጻር ለእኛ ሕይወትን ዘና ብሎ መኖር በራሱ የሚታሰብ፣ የሚሞከር አይደለም። ይሁንና ለውጤታማነት አንዱና ዋነኛ መግቢያ በር ስለመሆኑ ማጤን ግድ ይለናል። ማኅበረሰቡ ከዚህ የሚቃረን አቋም አስተምሮናል። እርሱም የሕይወት ጉዞ አስቸጋሪ በመሆኑ መታገልና ያለማቋረጥ መድከም እንዳለብን ነው።
ይሄ በራሱ ኪሳራ ነው። ሮቢን ጠንክራችሁ አትሥሩ አይለንም። ነገር ግን የሥራችንን ፍሬ ማጣጣም እንዳለብን አበክሮ ይመክረናል። ሌላው ከኑሮ ውድነት በከፋ በሥራ አጥነትና በዓላማ የለሽነት ድብርት ውስጥ ለተዘፈቀው ወገኔ ሮቢን ሻርማን ቢያገኘው ሁነኛ መላ አያጣበትም። የግል ልምዶቹ እንደፍርግርግ የባቡር መንጠላጠያ ፉርጎ ለመወጣጫነት ይገለገልበታል ብዬ በጽኑ አምናለሁ።



