ሙስና ማለት በግል ወይም በቡድን፣ በፖለቲካ መሪዎች ወይም በቢሮክራቶች ሥልጣንና ኃላፊነትን መከታ በማድረግ የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት ለግል ጥቅም የማዋል ኢ-ሥነምግባራዊ ድርጊት መሆኑን ስለሙስና ትርጉም የሰጡ ምሁራን ይገልጻሉ።
በመንግሥትና በሕዝብ ሀብትና ንብረት ላይ ስርቆት፣ ዝርፊያ እና ማጭበርበር መፈፀም፤ ሕግና ስርዓትን በመጣስ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በጎሰኝነት፣ በሃይማኖት ትስስር ላይ ተመርኩዞ አድሎ መፈፀም፣ ፍትህን ማጓደል እና ሥልጣንና ኃላፊነትን አላግባብ በመጠቀም ሕገወጥ ጥቅም ማግኛ ነውም ይሉታል፤ ሙስናን።
ሙስና ከአንድ አገር ሌላ አገር፣ ከቦታ ቦታ የሚለያይ ቢሆንም፣ ሙስና እንዲከሰት የሰዎች የግል ባህሪ እና የማኅበረሰቡ የሕግ ማዕቀፎች እንደ ዋና መንስኤ ይጠቀሳሉ።
በባህሪያቸው ስስታም፣ ውሸታም እና ምግባረ ቢስ የሆኑ ሰዎች ብሎም ስለሙስና ወንጀሎችና ቅጣቶች በቂ የሆነ ግንዛቤ የማይሰጥ ሕግ፣ ሙስና ከተፈጸመ በኋላም አግባብ የሆነ ተጠያቂነትና ጠንከር ያለ እርምጃ የማይኖር ከሆነ አንድ አገር በሙስና ተተብትባ በድህነት ስትማቅቅ ልትኖር እንደምትችል ይታመናል።
በዚህ ረገድ ብዙ የተፈጥሮ ሀብት ያላትን አፍሪካ፣ ሙስና ዋነኛ የእድገቷ ሳንካ ሆኖ ከድህነት ፈቅ እንዳትል እንዳደረጋት ለሰሚ እንግዳ ነገር አይደለም።
ከአፍሪካም ደግሞ ኢትዮጵያ በሙስና የተዘፈቁ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የተቋማት መሪዎች እንዲሁም ግለሰቦች ያሉባት አገራት መሆኗ በብዙ መልኩ ሲነገር የኖረ ነው።
ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማቸውን የማንጠቅሳቸው በርከት ያሉ ሰዎች ስለዚህ ጉዳይ ሐሳብ ሰጥተዋል።
የገጠር ወረዳ መስተዳደር ምክር ቤት ውስጥ የሚሠሩ ባለሙያ በቅርቡ ያዩትን ዐይን ያወጣ ሙስና ሲገልጹ፣ ‹‹የወረዳው ከተማ ውስጥ ለውስጥ መንገድ ግንባታ አሸዋ ከሚያቀርብ አንድ ግለሰብ ጋር ተዋዋለ። ከዚያም ስምንት ቢያጆ አምጥቶ እንዲደፋ የታዘዘው አቅራቢ ኹለት አምጥቶ ስምንት ቦታ ላይ ደፋው። የስድስቱን ቢያጆ አሸዋ ዋጋ የወረዳው አስተዳዳሪ ራሱ በላው። ይኼ ብቻ አይደለም። ተደራጅተው ቆጥበው ቤት ለሚሠሩ የከተማ ነዋሪዎች በሚል ከአርሶ አደሮች የጋራ የግጦሽ መሬት በካሳ ክፍያ ወሰደ። ነዋሪዎቹ ለካሳ የከፈሉትና ለአርሶ አደሮቹ የተሰጣቸው ግን ፈጽሞ የማይገናኝ ነው። እኔ ይህን ኹሉ በቅርበት አውቃለሁ። ግን ፀረ ሙስናውም ዐቃቤ ሕጉም ተባብረው ስለሚበሉ ለማን ምን ይባላል?››
ለሳፋሪኮም የቴሌኮምዩኒኬሽን መሠረተ ልማት ግንባታ በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚሠሩ አንድ ባለሙያ ደግሞ፣ ‹‹አንድ የትራፊክ ፖሊስ አስቆመንና ኹሉንም የጠየቀንን ነገር በሙሉ አሟልተን ሲያገኘን መጨረሻ ላይ ሸኙኝ ብሎ በግልጽ የምሳ ገንዘብ ጠየቀን። ከዚያ 200 ብር ሰጠኹት። ከአንድ ግለሰብ የታወር መገንቢያ ቦታ ተከራይተን መዘጋጃ ለማስጨረስ ስንሄድ፣ ማህተም ለመምታት በግልጽ ገንዘብ ይጠይቃሉ። ለአንድ ሰው ቢሆን ባልገረመን ነበር። መሬቱን ማየት አለብን ይሉና ከአምስት በላይ ሆነው ከቢሮ ይወጣሉ። ከዚያም ለእያንዳንዳቸው ጥሩ አበል ካልተሠራላቸው ጉዳዩን እንደማያስፈጽሙ ይነግሩናል። ከእኛ ምንም አያገኙም፣ ባለመሬቱ ግን ለእያንዳንዳቸው ገንዘብ መስጠት ግዴታ አለበት። በመንግሥት መሥሪያ ቤት እንዲህ ተደንቄ አላውቅም።››
አንድ በጦር ካምፕ ውስጥ የሚኖሩ ግለሰብ ደግሞ፣ ‹‹ሌላው እንዳለ ሆኖ የሰሜኑ ጦርነት የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈ፣ የበርካታ ማኅበረሰብ ኑሮ ያመሰቃቀለ እና አገርን ወደ ኋላ የጎተተ መሆኑን ነው አይደል የምናውቀው?›› ሲሉ ይጠይቃሉ።
ይቀጥላሉ፤ ‹‹ጦርነቱ በሙስና ተራዝሞ ብዙዎችን እየቀጠፈ ቢሆንስ? ጦር መሪዎች ከዚህ የፀዱ ናቸው? በግንባር የሚሞቱ ወታደሮችስ ደሞዛቸው መቼ ነው የሚቋረጠው? ለወታደሩ ከሚሄደው ድጋፍስ በተሰውት ሥም የሚበላ አካል የለም? ሥራ ለመቀጠር በእጅ መንሻ፣ ፈተና ለመፈተን እጅ መንሻ፣ የመንግሥት ተቋማት አገልግሎት ለማግኘት እጅ መንሻ፣ ፍትህ ለማግኘት ሙስና፣ ሎተሪው ከሙስና ጋር የተያያዘ፣ ጦርነት ለማሸነፍ እጅ መንሻ ኹሉም ነገር በእጅ መንሻ ብቻ ሲመስል የአገራችን መጻይ እድል አያሳዝንም?›› መልሰው ይጠይቃሉ።
‹‹ከአቅማችን በላይ ግብር እንከፍላለን። ግን ይኼው ጠዋት የወጣን ቢሯችን የምንገባው ካሰብነው ብዙ ዘግይተን ነው። በምቹ መንገድ ማሽከርከርማ እሱ ቅንጦት ነው። ታዲያ በየዓመቱ የሚጨምር ግብር እየከፈልኩ ከመንግሥት የማገኘው አገልግሎት ግን በተቃራኒው የሚወርድ ከሆነ የምከፍለው ለተወሰኑ ሰዎች የግል ጥቅም እንደሆነ ነው የምረዳው።›› ይህን የተናገሩት ደግሞ በመዲናዋ የመንገድ መዘጋጋት ምን ያህል ጫና እንዳለውና ይህም ለመሠረተ ልማት ግንባታ የሚውለው ገንዘብ ለምዝበራ በመጋለጡ እንደሆነ አስረግጠው የሚናገሩ አስተያየት ሰጭ ግለሰብ ናቸው።
ከወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ አንድ ሠራተኛ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ነገር ሹክ አሉ። ‹‹ዩኒቨርሲቲው ከጀርመን በውድ ዋጋ ያስገባው አንድ ትልቅ ማተሚያ ማሽን ነበረው። ማሽኑ በጣም የቆየ ከመሆኑ በላይ አሁን ገበያ ላይ ስለመኖሩም ያጠራጥራል። የቆዩና ብዙ ጊዜ የማይገኙ ህትመቶች የሚታተሙበት ወሳኝ ሀብት ነበር። ለጥገና ብለው አውጥተው ውድ የሚባሉ ክፍሎቹን ነቃቅለው ሸጠውታል መባሉን ሰማሁ።
ከዩኒቨርሲቲው መረጃ ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ በመሆኑ እርግጠኛ መሆን ባይቻልም፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የሚያሳትማቸው መጽሐፍት ቆመዋል የሚሉ መረጃዎች አሉ። ቆመው ከሆነ ከዚሁ ማሽን ብልሽት ጋር በተገናኘ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።›› ብለዋል።
እንዲሁም በቅርቡ አራት ሚሊዮን ብር የተከፈለበትና ጥቂት ሰዎች (መምህራን) ብቻ የሚናገሩበት ፕሮግራም በአንድ የቴሌቭዥን መርሃ ግብር ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ግለሰቡ ጥቆማቸውን አክለዋል። በእርሳቸው አነጋገር ይህ የቴሌቭዥን መርሃ ግብር ግልጽ የሆነ የዘረፋ ስልት ነው።
‹‹ሹመት በዘር፣ የትምህርት እድል ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በዘር፣ የሥራ ፈቃድ ሳይቀር በዘር፣ በዘር ተሳስሮ የመንግሥትን ሀብት ማኘክ ነው የሚታየው። የአሁኑ ሙስናማ አገራችንን የእብድ አገር የሚያሰኝ እኮ ነው።›› ይላሉ በመዲናዋ ካሉ ክፍለ ከተሞች በአንዱ ሠራተኛ ነኝ ያሉ ግለሰብ።
‹‹አንድ ወጣት 40 ሺሕ ብር ከከፈልክ ባንክ ትቀጠራለህ ያለውን ሰው አምኖ የክፍለ አገር ሥራውን ለቆ ወደ አዲስ አበባ መጣ። ሥራውን እንዲለቅና በቀላሉ እንዲያምን ያደረገው በ14 ሺሕ ብር አንድ ዓመት የፈጀ፣ በሰነድ የተደገፈ የትምህርት ማስረጃ አሠርቶ በ40 ሺሕ ብር ክፍያ ባንክ የገባ ግለሰብ ስለሚያውቅ ነው። እሱ ግን ቅድሚያ ክፍያ 20 ሺሕ ብሩን ከፍሎ አጨብጭቦ ቀረ እንጂ ባንክ ሊገባ አልቻለም። በኋላ ግን በአንድ የግል ባንክ ውስጥ ደንበኞች ለቤትና መኪና መግዣ ከፍ ያለ ብድር በሚስተናገዱበት መስኮት ከሚሠራ ባለሙያ ጋር ተዋውቆ መመሳጠር ጀመረ።
በዚህም ደንበኞች ብድሩን እንደጨረሱ ባለሙያው ጥሩ ደላላ አውቃለሁ በማለት አዛኝ በመምሰል ወደ ወጣቱ ይልካቸዋል። ደላላውም ለባለሙያው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ይከፍለዋል። ስለዚህ ጉዳይ በአንድ አጋጣሚ አውቃለሁ።›› በማለት የሆነውን ያጋሩን ግለሰብ ሥራዬ ወረዳ ውስጥ (አዲስ አበባ) ሆኖ ወሳኝ ኩነት ላይ ነው አሉ።
ስለሚያውቁት ነገር ደፍሮ መናገር አልፈለጉም እንጂ፤ የልደት፣ የጋብቻና የሞት የምስክር ወረቀት ለመስጠት፣ አብሶ ደግሞ የነዋሪነት መታወቂያ መስጠት በግልጽ የሙስና ዋነኛው በር ነው ይላሉ።
‹‹የትኛውም ሠራተኛ ቢጠየቅ ሥራ መልቀቅ ይፈልጋል። አመራር ሆኖ ሥራ መልቀቅ የሚፈልግ ግን አላጋጠመኝም። አመራር ሲኮን እኮ ቁጭ ብሎ መዝረፍ ነው።
እንኳን እነሱ እኛም ሳንሠራ የምናገኘውን እናውቀዋለን። በቅርቡ ለአንድ ቀን ስብሰባ ከከተማ ወጣ ብለን ነበር። የተሰጠን አበል በዐስር ቀን ተባዝቶ 7 ሺሕ ብር ነው። በእርግጥ የእኛ ደሞዛችን አነስተኛ ስለሆነ ይህን ያህል አበል ቢከፈለን እንደድጎማ ሊቆጠር ይችላል፣ አመራሮች የሚበሉት እኮ የሚያስደነግጥ ነው።
ለአንድ ወር እረፍት ልወጣ ነበር፣ ግን መጭው የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያ ወር ደግሞ የ2015 በጀት የሩብ ዓመት መዝጊያ ስለሆነ አበል በሽ ነው። ስለዚህ እንዳያመልጠኝ አልሄድም።›› በማለት የመንግሥት በጀት፣ የሕዝብ ሀብት በአበል ክፉኛ እንደሚበዘበዝ እርሳቸውም አስረግጠው እንደሚያምኑበት ገልጸው ሐሳባቸውን ደመደሙ።
ሰሞኑን ደግሞ ከተመሠረተ ገና ኹለት ዓመት እንኳን ያላስቆጠረው ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ተደረገ የተባለው ሙስና ለብዙዎች አስገራሚ ነበር ማለት ይቻላል።
የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈፃሚ የነበሩትን ጨምሮ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት እና የግንባታ ፈቃድ ኃላፊዎች ከነምክትሎቻቸው እንዲሁም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ከኃላፊነታቸው የተነሱት በክፍለ ከተማው በተንሰራፋው ንቅዘት ምክንያት መሆኑ ተሰምቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ነባር ኃላፊዎች አንስቶ በአዲስ እየተካ ያለው ሕዝብ ያቀርብ የነበረውን የመልካም አስተዳደር በደል መነሻ አድርጎ ባደረገው ማጣራት እንደሆነም ነው የተነገረው።
በተደረገው ማጣራት በክፍለ ከተማ ሌብነት በመገኘቱና የሚሰጡ የመሬት እና የግንባታ ፈቃድ አገልግሎቶች በሙስና የተጨማለቁ በመሆናቸው ለጊዜው መቆማቸውም ታውቋል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በተለይ ከመሬትና ከግንባታ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሆነ ሌብነት እንደሚፈጸም፣ ‹መረጃችሁ ጠፍቷል› እየተባለ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ሲጠየቅበት እንደቆየ በተደጋጋሚ መነገሩ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ፣ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ያለው ሙስና ዐይን ያወጣ ነው ካልተባለ በስተቀር፣ በሌሎች ክፍለ ከተሞችም ሆነ በመላ አገሪቱ ጉዳይ ለማስፈጸም እጅ መንሻ ግድ የሆነ ይመስላል።
በርካታ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ከሙስና ጋር የተያያዘ ታሪክ ይወራባቸዋል። በርካታ የመንግሥት አመራሮች ከሙስና ጋር ሥማቸው ይነሳል። ይህም ሙስናን በጎ ተግባርና በጎ ባህል የሆነ ይመስል ተላምደነው እንድንኖር አድርጎናል የሚሉ ብዙዎች ናቸው።
ብልሹ አሠራር መንሰራፋቱን ተከትሎ ብዙዎች በጉጉት በሚጠብቁት በኮንዶሚንየም ቤት ሳይመዘገቡና ብር ሳይቆጥቡ ዕጣ ውስጥ ተካተው መገኘታቸው የሚዘነጋ አይደለም።
‹ከለውጡ በፊት የነበረው ሙስና ቢያንስ በግልጽ አልነበረም። አሁን እኮ በገሃድ በአካፋ ሆኗል። 99 በመቶ የመንግሥትና የዜጎች የእለት ከእለት እንቅስቃሴም ከሙስና ጋር የተያያዘ ነው።› ብለው የሚገምቱ እልፍ ናቸው።
አዲስ ማለዳ ከፍትህ ሚኒስቴር እንዲሁም ከፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ከወቅታዊ የሙስና ጉዳዮችን ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ለማግኘት ብትሞክርም ስልክ ባለመነሳቱ ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014