በተለያዩ የእንስሳት መድኃኒቶች ላይ የዋጋ ንረት መከሰቱ ለዘርፉ ፈታኝ ስለመሆኑ የእንስሳት ሐኪሞች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
እንስሳትን ከተለያዩ በሽታዎች የመፈወስ አቅም ያላቸው መድኃኒቶች ዋጋ መናሩ በእንስሳት ላይ ጉዳት ከማስከተሉም በተጨማሪ፣ በዘርፉ ለተሰማሩ ሠራተኞች ፈተና ስለመሆኑ የእስሳት ሐኪሞች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ጌታሁን አድማሱ የተባሉ የእንስሳት ሐኪም የዋጋ ንረት የሚስተዋልባቸው የመድኃኒት ዓይነቶች እንስሳትን የመፈወስ እምቅ አቅም ያላቸው ናቸው ብለው፤ አሁን አሁን ግን እየጠፉም ከመሆናቸው ባሻገር በምትካቸው ገበያ ላይ የሚገኙት ደግሞ የጎንዮሽ ጉዳታቸው ያመዝናል ብለዋል።
ለአብነትም ‹‹tetraclozan cattle›› (ቴትራክሎዛን ካትል) የሚባል መድኃኒት በወራት ውስጥ ከ60 ብር ወደ 1 ሺሕ 400 ብር ከፍ ማለቱን ጠቁመዋል። በተያያዘም፤ ‹‹oxy20›› የተሰኘ መድኃኒት ከዚህ በፊት እስከ 91 ብር ይሸጥ የነበረ ሲሆን ሰሞኑን ወደ 190 ብር ከፍ ብሏል ብለዋል።
ሌላኛው ሰይድ ጀማል የተባሉ የዘርፉ ምሁር አንድ ‹‹Vival penistrip›› (ቪቫል ፔኒስትሪፕ) የተሰኘ የእንስሳት መድኃኒት ቢያንስ ከኹለት ወራት በፊት 250 ብር ሲገዛ እንደነበር አስታውሰው፤ ሰሞኑን ግን ወደ 700 ብር ማሻቀቡን ተናግረዋል።
የመድኃኒቱ ዋጋ ከ250 ወደ 700 ብር ከፍ ከማለቱ በፊት በአንድ የገበያ ወቅት ወደ 400 ብር ከፍሎ እንደነበር አንስተዋል።
ሌሎች በርካታ የእንስሳት ሐኪሞች በበኩላቸው፣ በተለይም ‹‹Vival penistrip›› ያሳየው የዋጋ ጭማሬ ፈጣን ነው ያሉ ሲሆን፤ ከ700 ብርም በላይ እስከ 800 እና 900 ብር እየተሸጠ መሆኑን አንስተዋል። በመሆኑም ሥራ እስከማቆም ድረስ መማረራቸውን ሳይናገሩ አላለፉም።
ይህን ተከትሎም በርካታ እንስሳት ሕክምና ማግኘት የማይችሉበት ጊዜ ሰፊ መሆኑና ለሠራተኞቹም ችግር መፍጠሩ ተጠቅሷል። ‹‹እኛ በእንስሳት ሕክምና ሙያ ብዙ መስዋዕትነትን ከፍለን የተማርን ሰዎች መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ባለመስጠቱ እስከ ‹‹Doctor of veterinary medicine›› ያሉ ባለሙያዎች ሥራ አላገኘንም። በግል የሥራ ዘርፍ እንስሳትን በማከም እንቅስቃሴ ብንጀምርም ሰው ሠራሽ የመድኃኒት የዋጋ ንረት በማሳየቱ ለእንስሳቱም ሆነ ለሠራተኞቹ አስቸጋሪ ሆኗል።›› ሲሉም አክለው አብራርተዋል።
ከዚህ አልፎ አርሶ አደሩ በመድኃኒት ዋጋ መናር ምክንያት በርካታ እንስሳትን በሞት እየተቀማ ስለመገኘቱ ተነስቷል። ነጋዴዎች በበኩላቸው፣ ዋጋውን የጨመሩብን አከፋፋዮች ናቸው ይላሉ። አከፋፋዮች ደግሞ የዋጋ ጭማሬ የተደረገው ከአስመጪዎች ነው ይላሉ። አስመጪዎች በበኩላቸው የዶላር ምንዛሬ መጨመር ነው በማለት እንደሚያሳብቡና በዚህ መካከል ግን እንስሳቱ፤ አርሶ አደሩና የዘርፉ ሠራተኞች የከፋ ችግር እያሳለፉ ስለመሆናቸው ነው የተገለጸው።
የመድኃኒቱ ዋጋ ከቀን ወደ ቀን የሚጨምርበት አጋጣሚ መኖሩም ሰይድ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። በተያያዘም አንድ ‹‹viva›› (ቪቫ) የተሰኘ የእንስሳት መድኃኒት ከወራት በፊት 50 ብር ሲገዛ እንደነበር እና ከትንሽ ቀን ቆይታ በኋላ ደግሞ ወደ 70 ብር ከፍ ማለቱን አስታውሰው፤ ይባስ ብሎ ሰሞኑን ወደ 150 ብር ክፍ ብሏል ሲሉ አስረድተዋል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ከሳምንታት በፊት 9 ብር ከ50 ሳንቲም ሲሸጥ የነበረ ‹‹3400mg teter›› መድኃኒት ሰሞኑን 20 ብር ገብቷል ነው ያሉት።
በመሆኑም መንግሥት የእንስሳት መድኃኒት ገበያን በትኩረት ሊያስሰው ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስቀምጠዋል።
ይህን ተከትሎም በእንስሳት እርባታ ሥራ የተሰማሩ አንዳንድ ሰዎች ሥራውን እስከማቆም ውሳኔ ሳይደርሱ እንዳልቀሩ ገልጸዋል። ቅሬታ አቅራቢዎቹ የዋጋ ንረቱ እንዲፈጠር ያደረገው የኮንትሮባንድ ንግድ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፣ መንግሥት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
የተነሳውን የዋጋ ጭማሬ በተመለከተ ምን ምለሻ እንደሚሰጥ ለማወቅ ለብሔራዊ የእንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014



