• ከወልድያ ከተማ ኮምፕዩተርና ሌሎች ቁሳቁሶችን ያሸሹ ባንኮች አሉ ተብሏል
በቅርቡ የተቀሰቀሰውን ሦስተኛ ዙር ጦርነት ተከትሎ በተለያዩ የሰሜን ወሎ ከተሞች ከሰኞ ነሐሴ 23/2014 ጀምሮ ማንኛውም የባንክ አገልግሎት ተቋርጦ እንደሚገኝ አዲስ ማለዳ ከነዋሪዎች አረጋግጣለች።
በዚህም ጦርነቱ ጉዳት የደረሰባት ቆቦ ከተማን ጨምሮ በወልዲያ፣ ውጫሌ፣ ሲሪንቃ፣ መርሳ እና ውርጌሳ የመሳሰሉ ከተሞች፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ (ከአራት ቀናት በላይ) ኹሉም ባንኮች አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ነው የተገለጸው።
አንድ የወልድያ ከተማ ነዋሪ እንደተናገሩት፣ በከተማዋ ከሰኞ እለት ጀምሮ የባንክ አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፣ ቅዳሜ እለት ለአንድ ሰው እስከ ኹለት ሺሕ ብር በመስጠት በተወሰነ መልኩ ሲሠሩ ነበር ብለዋል።
ሆኖም ረቡዕ ዕለት ዓባይ ባንክ ከፍቶ የነበረ ቢሆንም፣ ሰዎች ሮጠው ሲሄዱ ብር ሳይሰጥ ወዲያው ሊዘጋ ችሏል ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም፣ ‹‹ብር የለንም ወደ ደሴ ከተማ ወስደነዋል ነው የሚሉት›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ኮምፕዩተር እና ሌሎች ቁሳቁሶችን ጭነው ወደ ደሴ ከተማ የወሰዱ ባንኮች መኖራቸውንም ነው የገለጹት።
‹‹እነሱ (ባንኮቹ) ምን እንዳሰቡ ባናውቅም፣ ቢከፍቱ ምንም ዓይነት ችግር ይገጥማቸዋል ብለን አናስብም›› ሲሉ ተደምጠዋል።
‹‹ባንኮች መቼ ሥራ እንደሚጀምሩም አናውቅም። የከተማ አስተዳደሩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ወደ ሥራ እንዲገቡ ረቡዕ ዕለት ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ በማግስቱ ከመብራት ኃይል በቀር ቢሮ የከፈተ ተቋም አልነበረም›› በማለትም ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ፣ ከሐሙስ እለት ጀምሮ የከተማዋ እንቅስቃሴ የተረጋጋ ይመስላል ሲሉ ገልጸው፣ ወደ ደሴ ሸሽተው የነበሩ ነዋሪዎች እየተመለሱ እንደሆነና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችም በከፊል ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመዋል። ከሐሙስ እለት ጀምሮ ባጃጅ እና ሌሎች ተሽከርካሪዎች ወደ እንቅስቃሴ መመለሳቸውን፣ ሱቆች መከፈታቸውን ብሎም የከተማዋ እንቅስቃሴ የተሻለ መሆኑን በማንሳትም፣ ቀድሞ ከወልድያ በቅርብ ርቀት ሲሰማ የነበረው የከባድ መሣሪያ ድምጽም እንዲሁ በዚህ ዕለት እንደማይሰማ ነው የጠቀሱት።
የላሊበላ ከተማን በተመለከተ፣ የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ተስፋ ሀብቴ እንደገለጹት፣ ባንኮች አጋጠመን ባሉት የገንዘብ እጥረት ከሰኞ እለት ጀምሮ የአገልግሎት መቆራረጥ ነበር።
በዚህም የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ስላልተከፈላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ከባንክ አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ ችግሩን ለመፍታት የተደረገውን ሙከራ ገልጸዋል።
ብዙ ሰዎች የንግድ ባንክ ደንበኞች በመሆናቸውና፣ ባንኩ ተሽከርካሪ ከተመደበልኝ ከሌላ ቦታ ገንዘብ አምጥቼ አገልግሎት እሰጣለሁ በማለቱ፣ ተሽከርካሪና የጸጥታ አካል ተመድቦለት ከሌላ ቦታ ገንዘብ አምጥቶ ማክሰኞ እለት አገልግሎት ሲሰጥ መዋሉን ነው የተናገሩት።
ይሁን እንጂ፣ ገንዘቡ በእለቱ በማለቁ ረቡዕ እለት እንደገና አስመጥቶ ሐሙስ አገልግሎት ሲሰጥ መዋሉን እንዲሁም በገንዘብ እጥረት የተነሳ ለጊዜው ወደ ሥራ ካልገባው ከዓባይ ባንክ በስተቀር ኅብረት እና አቢሲኒያ ባንኮች ሐሙስ እለት ወደ ሥራ መግባታቸውን አመላክተዋል።
ደንበኞች እስከ አምስት ሺሕ ብር የተገበደ አገልግሎት እያገኙ ሲሆን፣ በቂ ነው ባይባልም ለማረጋጊያ የሚሆን ሥራ እየተሠራ መሆኑን ነው የጠቀሱት።
የመንግሥት ሠራተኛውንና አመራሩን ሰብሰቦ በጄኔራሎች አሁን ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ትክክለኛ መረጃ የተሰጠ በመሆኑ፣ የመንግሥት ሠራተኞች ሥራቸውን እንዲሠሩ፣ ሕዝቡም እንዲረጋጋ ተደርጓል ብለዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ዋና ከተማ ደሴም በተመሳሳይ ለተወሰኑ ቀናት የባንክ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን፣ ከረቡዕ በኋላ ባንኮች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ታውቋል። ይሁን እንጂ በጦርነቱ ስጋት ያደረባቸው ሰዎች ከወልድያና ሌሎች አካባቢዎች ወደ ከተማዋ በመግባታቸው ከፍተኛ የሆነ ወረፋ መኖሩም ተመላክቷል። አንድ ሰው ማውጣት የሚችለው ብርም ከፍተኛው ከኹለት ሺሕ የበለጠ አለመሆኑ ነው የተገለጸው።
ነዋሪዎቹ ባንክ የተቀመጠ ብር እያለን መጠቀም ባለመቻላችንም መሠረታዊ የሚባል ችግር ነው እያጋጠመን ያለው ሲሉ ገልጸዋል።
በእንደዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ወቅት የባንኮች መዘጋት የዜጎችን ስቃይ የሚያባብስ በመሆኑም፣ ተቋማቱ ገንዘብ አልቋል በሚልና በሌሎች ሰበቦች አገልግሎት በማቋረጣቸው ወቀሳ ሲቀርብባቸው ሰንብቷል።
ይህ ዘገባ ወደ ህትመት በተላከበት የመጨረሻ ሰዓት ወልዲያ ከተማ የባንክ አገልግሎት መጀመሩ ተሰምቷል፡፡
ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014


