ሦስት ባንኮች በኦነግ ሸኔ ቡድን መዘረፋቸው ተነገረ

0
3125

ሦስት ባንኮች በኦነግ ሸኔ ቡድን ተዘርፈዋል ተብሏል

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን አሙሩ ወረዳ ሦስት ባንኮች በኦነግ ሸኔ ቡድን መዘረፋቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንዳሉት፣ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን አሙሩ ወረዳ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የኦነግ ሸኔ ቡድን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ አዋሽ ባንክ፣ ኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ በድምሩ የሦስት ባንኮችን መግቢያ በር እና ካዝና በመስበር ዘረፋ ፈጽመዋል ብለዋል።

በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ዞን አሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች እና በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሀሮ ከተማ የኦነግ ሸኔ ቡድን በዜጎች ላይ እንዲሁም በመንግሥት ተቋማት እና በግለሰቦች ንብረት ላይ ጥቃት እያደረሰ እና እየዘረፈ እንደሚገኝም ነዋሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች መረጃውን እስካጠናቀረችበት ጊዜ ድረስ፣ ከነሐሴ 23 እስከ ነሐሴ 25 ቀን 2014 ባሉት ተከታታይ ሦስት ቀናት ብቻ በአጋምሳ ከተማ የተለያዩ ቦታዎች በኦነግ ሸኔ ቡድን 11 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ሌሎች 11 ሰዎች ላይ ቀላል እና ከባድ የአካል መቁሰል ደርሶባቸዋል። እንዲሁም ከ20 ያላነሱ ሰዎች ደግሞ መፈናቀላቸውንም ተናግረዋል።

በተጨማሪ ከ20 በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች ቤት እንደወደመ እና በገንዘብ ያልተተመነ ሀብት ማለትም የቁም ከብቶች፣ የግብርና ምርቶች፣ የቤት ቁሳቁስ እና ሌሎች ንብረቶችም ተዘርፈዋል ነው የተባለው።

እነዚህ ጥቃቶች እና ዝርፊያዎች እየተፈፀሙ የሚገኙት፣ በአካባቢው የሚገኙ የመከላከያ ኃይል፣ ልዩ ኃይል እና ሌሎች የጸጥታ አካላት እየወጡ መሆናቸውን ተከትሎ ነው ተብሏል።

በኦሮሚያ ክልል ባሉት በኹለቱ የዞን ከተማዎች የተረጋጋ ሰላም ባለመኖሩ በቡድኑ ጉዳት እየደረሰባቸው የሚገኙ ሰዎች ወደ ጤና ተቋማት አቅንተው የሕክምና አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ ተገልጿል።

ከሀሮ እና አጋምሳ የሚዋሰኑ ከተማ ሲሆኑ፣ ከሌሎች ከሚያዋስኗቸው አካባቢዎች ጋር ያሉ አውራ ጎዳናዎች በቡድኑ እየተዘጉ እንደሚገኝ እና ዜጎችም መንቀሳቀስ እንዳይችሉ የተገደዱበት ሁኔታ ነው ያለው ተብሏል።

መንግሥት በአካባቢው ያለውን የጸጥታ ችግር በዘላቂነት በመፍታት ሰላምን እንዲያረጋግጥ እና የንጹሃንን ሕይወት እንዲታደግ ነዋሪዎች ጠይቀዋል።

አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ለክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ያደረገችው ሙከራ ምላሽ አላገኘም።

የኦነግ ሸኔ ቡድን በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በተለይም በምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብ ሸዋ እና በምሥራቅ ሸዋ ዞኖች፣ በየጊዜው ሰዎችን እየገደለ መሆኑ እና ጥቃት እያደረሰ እንደሚገኝ ሲገለፅ እንደቆየ እና አሁንም ቆሟል ለማለት እንደማይቻል ተነግሯል።

የኦነግ ሸኔ ቡድን ከኹለት ሳምንት በፊት ለክልሉ ነዋሪዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ምንም ዓይነት ጥቃት እንደማያደርስ ‹ተናግሮ› የነበረ ቢሆንም፣ እውነታው ግን ይህ እንዳልሆነ እና ከድርጊቱ እንዳልተቆጠበ ነዋሪዎች ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here