የጠራ መረጃ ይሰጥ!

0
816

የሰሜኑ ጦርነት ሦስተኛ ዙር ውጊያ ነሐሴ 18/2014 መጀመሩን ተከትሎ የተጣረሱ መረጃዎችና ፕሮፓጋንዳዎች ዳግመኛ መድረኮችን ተቆጣጥረዋል። ከቀደሙ የእልቂት ድርጊቶች መታረም ያልቻሉ የተፋላሚ ወገን ደጋፊዎቻቸውና ራሳቸው ተፋላሚዎቹ የሚነዙት ወሬ ለኅብረተሰቡ ጭንቀትን የፈጠረ መሆኑን መመልከት አይከብድም።

ጦርነት ውስጥ መገባት የለበትም ሲሉ የነበሩ ድምጻቸው ሳይሰማ ወደ ውጊያ የተገባው ተገዶ እንደሆነ ኹሉም ወገን ለማሳመን ሲሞክር ይታያል። ይህ ቢሆንም ግን፣ በየትኛውም ወገን ጦርነቱን በቶሎ ተቋጭቶም ይሁን በድርድር ተፈትቶ ሕዝቡ በሰላም እንዲኖር ያስችሉ የነበሩ ተደጋጋሚ እድሎች እንዲያመልጡ ሲደረግም ተስተውሏል።

ኹሌም በተፋላሚ ወገኖች መካከል መነጋገርና መወነጃጀል ያለ ቢሆንም፣ ስለጦርነቱ ሂደትም ሆነ ዝርዝር ኹኔታ ሕዝብ የማወቅ መብቱ ሊገደብ እንደማይገባ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ሞትን ሊያስከትል የሚችል ክስተት ይቅርና ስለበጎ ነገርም ሕዝብ የማወቅ መብት እንዳለው ለመንግሥት የሚነገርበት ዘመን ላይ አይደለንም።

ሁሉም መረጃ በይፋ ይነገር ብሎ ወታደራዊ ምስጢሮች ይውጡ፣ አልያም ለፕሮፓጋንዳ የሚውሉ ዘገባዎችን በግብዓትነት ይጠቀሙባቸው ማለት አይደለም። ሆኖም በሕይወት የመኖር ዓለም ዐቀፍ መብትን ከሚነፍግ ማንኛውም ዓይነት ድርጊት ኅብረተሰቡ ቢያንስ ራሱን እንዲጠብቅ የሚያስችለው መረጃ በወቅቱና በአግባቡ ሊነገር ግድ ይላል።

ከዚህ ቀደም ከነበረው ሂደት በተሻለ መረጃዎች ከአንድ ተቋም ብቻ እንዲወጡ በኹለቱም ተፋላሚ ወገኖች ሲደረግ ቢታይም፣ መረጃዎቹ እጅግ የተራራቁ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ኹለቱንም እንዲጠራጠርና የራሱን አማራጮች እንዲፈልግ ማድረጉን መገመት ይቻላል። ኹሉም መረጃ ይውጣ አልያም ታፍኖ ለመንግሥትም ሆነ ለተፋላሚ ወገኑ የሚጠቅም መረጃ ብቻ ሳይሆን መውጣት ያለበት፤ ፕሮፓጋንዳው ከትክክለኛ መረጃ ተለይቶ መሆን ይገባዋል።

ትክክለኛና ያልተዛባ መረጃን በፍጥነት ማውጣት የነበረባቸው አካላት የሚጠበቅባቸውን ባለማድረጋቸው ሠሞኑን ከባድ ውዥንብር ተፈጥሮ እንደነበር መመልከት ይቻላል። ይህ ዓይነት ኅብረተሰቡን ወዳልተፈለገ እርምጃ እንዲገባ የሚያደርግ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ሊቆም እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ጦርነት የብዙዎችን እልቂት እንዲሁም የንጹሐንን ሞት ሊያስከትል የሚችል፣ መኖር ያልነበረበት ተግባር ቢሆንም፣ ዘመኑ ሳይሆን አስተሳሰባችን ሊያስቀረው ካልቻለ ቢያንስ በቶሎ እንዲቋጭና ከየትኛውም ወገን ቢሆን ብዙ ሰው እንዳያልቅ ሊጣር ይገባል። ይህ የሚሆነው ደግሞ የጅምላ እልቂት ያሰበ አካል ካለ መረጃው እንዲወጣና በጥቂት መስዋዕትነት ድል ተገኝቶ የጋራ ጠላት ሴራ ሊከሽፍ ከቻለ ነው።

ውጊያ እንደየቀኑና አዋጊው ስልት ባሕሪውም ሆነ አቅጣጫው በየሰዓቱ ሊቀያየር ስለሚችል፣ መረጃ እጅግ ወሳኝ ግብዓት ነው። በአንድ አቅጣጫ የነበረ ውጊያ ወደሌላ ሲዞር በአስቸኳይ መረጃው ካልደረሰ አልያም በፍጥነት አጋዥ ኃይል ካልተላከ ብዙ መዘዝ ያስከትላል።

ዘመናዊ የመልዕክት መለዋወጫ መንገዶች ጥቅም የማይሰጡ ሊሆኑ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ ገብቶ የጥንቶቹ ማለትም ፈረስና እርግብ አልያም በቅሎና አህያ ለጭነት ጭምር ሊያገለግሉ የሚችሉበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ሊታሰብ ግድ ይላል።

ለጦርነቱ ማስፈፀሚያ ብቻ ሳይሆን ከውጊያው አውድማ ለመራቅ የሚያስቡ ንጹሐን የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ መረጃን በተቻላቸው መንገድ ለማግኘትና ለማጣራት ሊሞክሩ እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ትመክራለች። መንግሥት የሚጠበቅበትን መረጃ በተገቢው ፍጥነትና መጠን ሊያቀርብ አልቻለም ተብሎ ቁጭ ተብሎ ሞትና መከራን ማስተናገድ እንደማይገባ ግልፅ ነው።

እንደአፋር ባህላዊ የመረጃ መለዋወጫ ዳጉ አልያም ኅብረተሰቡ የየራሱን ባሕላዊ አካሄድ ተጠቅሞ ከሌላ ወግን ሳይጠብቅ ራሱ ትክክለኛ የመረጃ ምንጭና አሰራጭ መሆን ይጠበቅበታል። ክፉ ጊዜ ጀግኖችን ያበቅላል፤ ብልሐትንም ይወልዳል እንደሚባለው፣ አስቀድሞ መዘጋጀት ባይቻል እንኳን በፍጥነት ወቅቱ የሚፈልገውን ማኛውንም ነገር ለማግኘት መጣር ከዘመኑ ማኅበረሰብ የሚጠበቅ ነው።

መረጃ በአግባቡ ባለመሰራጨቱ ወልዲያና አካባቢው ላይ የሆነውን መመልከቱ በቂ ነው። ግለሰቦች የወሬ ውዥንብሩ አስፈርቷቸው ያለ ልክ ቢፈናቀሉም ከሁኔታው አንፃር የሚገርም አልነበረም። ነገር ግን፣ የሕዝብ ኃላፊነት የተጣለባቸውና በችግሩ ጊዜ አብረውት እንዲቆዩ የሚጠበቅባቸው የመንግሥት ተቋማት፣ ቀድመው ሳያጣሩም ሆነ ታዘው መሸሽ እንዳልነበረባቸው አዲስ ማለዳ ትረዳለች።

በተለይ ባንኮች ድንገት ተነስተው ዘግተውና እቃቸውን ሸክፈው የሕዝቡን መኖሪያና መተዳደሪያ ገንዘብ አሽገው፣ ደንበኞቻቸውን ለጠላትና ረሃብ ጥለው መጥፋት አልነበረባቸውም። ገንዘቡ እንዳይዘረፍ ጠላትም እንዳያገኘው በሚል ምክንያት ቢሆንም፣ እጅግ ሩቅ ከሆኑ ከተማዎች ዘግቶ መሸሹ ማንን እንደሚጠቅም ግልጽ ነው።

ለተፋላሚ ወገን ፕሮፓጋንዳ የሚጠቅም ተግባርን እንዲሁ በግብታዊነት እንዲከናወን ከማድረግ ይልቅ፣ በአፋጣኝ ለኅብረተሰቡ የድርሻውን እንዲወስድ ማድረግ የተሻለ ነበር። ቅርብ ካለ ከተማ ራቅ ወዳለው እያሸሹ መሄድም እየተቻለ፣ በማን አለብኝነት ሲወሰን ኅብረተሰቡ የባሰ የተቃወሰ ሁኔታ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል።

ኅብረተሰቡን ሊያረጋጋው የሚገባው የመንግሥት አካል ቀድሞ ከጦር ቀጠናዎች የሚወጣ ከሆነ ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ ተደርጎ ሊጠየቅ ይገባል። አደጋ ቢደርስ የአንድ መርከብ ካፒቴን ከተሳፋሪዎቹ መጨረሻ እንዲወጣ የሚደረግበት አስተሳሰብ ጦርነት ላይ ተግባራዊ እንዲሆን መታሰብ ያለበት ዘመን ላይ እንገኛለን።

የጦር መሪ መማረክም ሆነ መሰዋት እንደትልቅ ኪሳራ ሊታይም አይገባም። ትልልቆቹ ባዘዙት ሄዶ የሚሞተው ድሃው ወጣት መሆኑ ባይካድም፣ ሽሽት ላይ እንኳን ከኋላ ለመጠበቅ ሞራል የሌላቸው መሪዎች እያሉ ያልሠለጠነውን ሕዝብ ተዋጉ ለማለት ይቅርና አትሽሹ ለማለት ድፍረት ሊኖር አይገባም።

መሪ እንደሚለው ቃል ትርጓሜ፣ አዋጊዎችም ሆኑ አስተዳዳሪዎች እንደቀደሙት ዘመናት ነገሥታት እየመሩ ጠላትን ይጋፈጡ ማለት ሊያስቅ የሚችል ኋላቀር አስተሳሰብ ተደርጎ አሁን ቢወሰድም፣ ቢያንስ ለሚመሩት ሕዝብ ወዴት እንደሚኬድ ሊነግሩት ይገባል። ጨፍን ተከተለኝ የሚለው የማሞኘት አካሄድ የሚያዛልቅበት ዘመን ስላበቃ፣ ኅብረተሰቡ የግድ መረጃ ሊያገኝ ይገባዋል። መንግሥት መረጃንና ጥቆማን ለማግኘት ሕዝብን የሚጠቀመውን ያህል፣ በተቃራኒው ሕዝቡም በሚከፍለው ግብር ማግኘት የሚገባውን የሩቅ መረጃ በወቅቱ ሊያገኝ ይገባዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here