በርካታ ቅሬታዎች ሲቀርቡበት የቆየው የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ለትርፍ ያልተቋቋመ ተቋም ሆኖ ሊቀጥል መሆኑን አዲስ ማለዳ ጉዳዩን ሲከታተሉ ከቆዩ የወላጅና የመምህራን ተወካዮች አረጋግጣለች።
በዚህም ከኻያ ዓመታት በላይ ግብር ሳይከፍል እንዲሁም ያለፈቃድ ሲሠራ እንደኖረ የተነገረለት ይኼው ትምህርት ቤት፣ በመጪው ዓመት በቦርድ የሚተዳደር ሆኖ 80 በመቶ ትርፉም ለትምህርት ቤቱ ማበልጸጊያ ይውላል ነው የተባለው።
ትምህርት ቤቱ ለትርፍ ያልተቋቋመ ለመባል የሚያስችለውን ሥራዎች በማጠናቀቅ ላይ ሲሆን፣ ከትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው ትዕዛዝ መሠረት በሐሳቡ ተስማምቶ ሙሉ ንብረቱን ማስቆጠሩን ለማወቅ ተችሏል።
ለትርፍ ያልተቋቋመ ተቋም ተብሎ ለመመዝገብም ለሚመለከተው አካል ጥያቄ አቅርቦ ሂደት ላይ እንደሆነና ይህም ተጠናቆ በዐስር ቀናት ውስጥ በጋዜጣ ይወጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የተገለጸው።
ጉዳዩን እዚህ ለማድረስ ከፍተኛ ትግልና ውጣ ውረድ እንደነበረው የገለጹት ተወካዮቹ፣ በተለይ ትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ትምህርት ቤቱ ቀድሞ በነበረበት የጥፋት ተግባሩ እንዲቀጥል ከፍተኛ ተባባሪዎች ነበሩ ብለዋል።
ይሁን እንጂ የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕ/ር) በተለየ ሁኔታ ሲያግዟቸው እንደነበር በመግለጽ፣ ትምህርት ቤቱ የ30 ዓመት ግብር እንዲከፍል፣ ንብረቱ እንዲወረስ እንዲሁም ክስ እንዲመሠረትበት ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለፍትህ ሚኒስቴር የሚላክ ደብዳቤ ጽፈው እንደነበር አንስተዋል።
የትምህርት ቤቱ አመራሮችም ሊስማሙ የቻሉት ሚኒስትሩ የጻፉትን ደብዳቤ ካዩ በኋላ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከሚኒስትሩ በታች ያሉ አንዳንድ የሥራ ኃላፊዎች ግን ይህ እንዳይሆን ሲያጓትቱ መቆየታቸውን ነው የተናገሩት።
ሆኖም ከዚህ በፊት ትምህርት ቤቱ በእኔ ስር ነው ሲል የቆየው የግሪክ ማኅበረሰብ እድር፣ ሕንጻዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ትምህርት ቤቱ እንዲጠቀምበት በነጻ ሰጥቻለሁ የሚል ደብዳቤ ነው የጻፈው። የሆነ ጊዜ ላይ ግን ኪራይ ክፈሉ ወይም ልቀቁ ሊል እንደሚችል ተገንዝበናል ሲሉ ገልጸዋል። ይህ እንዳይሆን ለትርፍ ያልተቋቋመ ሆኖ የሚመዘገብበት ሁኔታ በትክክል እንዲካሄድ እንከታተላለን ነው ያሉት፤ ተወካዮቹ።
ተወካዮቹ አክለውም ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከትምህርት ሚኒስቴር የሚኒስትር ኃላፊነታቸው ሊለቁ ይችላል በሚል ግምታዊ አካሄድ፣ እጅ ላለመስጠት አሁንም አሻጥር ለመሥራት እየሞከሩ እንዳሉ ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ትምህርት ቤቱ ለቀጣዩ ዓመት የትምህርት ዘመን ከትምህርት ሚኒስቴር ፈቃድ ማግኘት የሚችለው እና የማስተማር ሥራውን መቀጠል የሚችለውም፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ ተቋም ሆኖ በሚመለከተው ሕጋዊ አካል ምዘገባውን ከጨረሰ በኋላ፣ ሕጋዊ ቦርድ ሲያቋቁም ብቻ እንደሆነ ተነግሯል።
ተዋካዮቹ በመጨረሻም፣ ትምህርት ሚኒስቴር ዘግይቶም ቢሆን ይህን እርምጃ መውሰዱን አመስግነው፣ እንደ ግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ፈቃድ ሳይኖራቸው እና ግብር ሳይከፍሉ በሕገወጥ መልኩ ሲሠሩ በኖሩ ሌሎች የውጭ አገር መሠረት ያላቸው ትምህርት ቤቶች ላይም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በቀጣይ ተመሳሳይ እርምጃዎችን ይወስዳል ብለን እናምናለን ሲሉ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኘው የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት፣ ከኻያ ዓመታት በላይ ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖረው እንዲሁም 200 ሚሊዮን የሚጠጋ ዓመታዊ ገቢ ከተማሪ ወላጆች እያገኘ፣ ለመንግሥት ግብር ሳይከፍል መኖሩን አዲስ ማለዳ ከዚህ በፊት በሠራቻቸው ዘገባዎች ለአንባቢዎች ማድረሷ አይዘነጋም።
ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014



