የታሸገ ውኃ መያዣ ኘላስቲክ ቀለም ሊቀየር ነው

የታሸገ ውኃ መያዣ ኘላስቲክን ማቅለሚያው ቀለም ሊቀየር መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምርና ልማት ማእከል ፓኬጂንግ ዳይሬክተር ደሴ አበጀ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ እስካሁን ባለው ጊዜ የታሸገ ውኃ መያዣ ፕላስቲክ ሰማያዊ ያመዘነ ቀለም ያላቸው ሲሆን፣ ከጥቅምት 1/2015 ጀምሮ ግን ነጭ ይሆናል ብለዋል።

ይህን ቀለም ለመቀየር የታሰበው ውኃቸው ለአገልግሎት ከዋለ በኋላ የሚጣሉ የኘላስቲክ መያዣዎች በሚጠበቀው ልክ ለአገልግሎት እየዋሉ ባለመሆናቸው በብዛት ሲጣሉ የአፈር ለምነትን እያበላሹ ስለሆነ ነው ተብሏል።

የኘላስቲክ መያዣ ቀለም ከተቀየረ ለበርካታ አገልግሎት እንደሚውል እና ለአብነት ኘላስቲክ ጠርሙሱ ሪሳይክል ተደርጎ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካዎች ለሸሚዝ፣ ለብርድልብስ እና ለሌሎች ተያያዥ አልባሳት መሥሪያነት የሚያገለግል ይሆናል ተብሏል።

ይህ የኘላስቲክ መያዣ ቀለም መቀየሩ በቀጣይ ለጨርቃጨርቅ እንዲሁም ለአምራች ፋብሪካዎች ጉልህ አስተዋፅዖ እንዳለው እና ከውጭ አገራት ለምርታቸው የሚያገለግሉ ተመሳሳይነት ያላቸውን ቁሳቁሶች የማስመጣት እድላቸውን እንደሚቀንስላቸው ተጠቁሟል።

እነዚህ የጨርቃጨርቅ እና የክር ፋብሪካዎች ከውጭ አገራት የሚያስገቧቸውን ተመሳሳይነት ያላቸው ቁሳቁሶች እና የቀለም ዓይነቶች በመቀነሳቸውም በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከ40 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን እንደሚቻል ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ይህን ቀለም ለመቀየር የኢትዮጵያ የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ከ2013 ከመጀመሪያዎቹ ወራት ጀምሮ እስከ ሰኔ/2014 ድረስ ለተከታታይ አንድ ዓመት ተኩል ምርምር እንዳደረገ እና ውጤታማ ሆኖ በመገኘቱም ከኹለት ወር በፊት ጥናቱን አጠናቆ ማፅደቅ እንደተቻለ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከአንድ መቶ በላይ የሚሆኑ የታሸገ ውኃ አምራች ፋብሪካዎች እንዳሉ እና ከዚህ ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ፋብሪካዎች የኘላስቲክ ጠርሙስ ቀለም በመቀየሩ ሐሳብ እንደተስማሙ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

እስካሁን ባለው አንድ የታሸገ ውኃ ፋብሪካ ተቋሙን አስፈቅዶ የኘላስቲክ ጠርሙሱን ቀለም ቀድሞ መቀየር እንደቻለ እና ሌሎቹ ተቋሙ ባስቀመጠበት ቀነ ገደብ ጀምረው የሚቀይሩ ይሆናል ተብሏል።

 የኢትዮጵያ የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ አፅድቆ ተግባራዊ የሚያደርገውን የታሸገ ውኃ መያዥያ የኘላስቲክ መያዣ የቀለም ቅያሬን የማይተገብሩ አምራች የውኃ ፋብሪካዎች ከተገኙ በሕግ ተጠያቂ እንደሚያደርግ ተነግሯል።

በተያያዘም የኢትዮጵያ የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ ያደረገውን የጥናት ምርምር በግል ድርጅት ላይ እንደሚሠሩ የሚያወሱ አንዳንድ ግለሰቦች ጥናቱን ራሳቸው እንዳጠኑ በማስመሰል መግለጫ የሚሰጡ እንዳሉ ደርሰንበታል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ከዚህ አንፃር አንድ የፌዴራል እና የመንግሥት ተቋም መርምሮ፣ አፅድቆ፣ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰናዳ ባለበት ወቅት፣ ምርምርን በመስረቅ የራስ አስመስሎ በመገናኛ ብዙኀንም ሆነ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ማሳወቅ ተገቢነት እንደሌለው ገልፀዋል።

የዚህ ዓይነት ሕገወጥ ድርጊቶች ላይ የሚሳተፉ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ያስጠነቀቁት ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይ ከተግባራቸው የማይቆጠቡ አካላት ካሉ የኢትዮጵያ የምግብና መጠጥ ኢንዱስትሪ በሕግ ተጠያቂ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here