በፖስታ ቤት የሚላኩ እቃዎች መጥፋት በደንበኞች ላይ ቅሬታ ፈጥሯል

0
1010

በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የተለያዩ ቅርንጫፎች የሚገለገሉ ደንበኞች ብዙ ጊዜ የሚልኩት እቃ በአግባቡ ከተቀባዩ እጅ እንደማይደርስ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

‹‹እኛ የላክነው እቃ ወይም ከሌላ ወገን የተላከልን እቃ ጠፍቷል እየተባልን ከስረን እንቀራለን። በተጨማሪም እቃ ልከን ቢደርስልን እንኳን ብዙ ጊዜ ለወራት ተመላልሰን እንዲሁም ሠራተኞች አመናጭቀውንና አጉላልተውን ነው የሚሰጡን።›› ሲሉ ገልጸዋል።

ሥማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ተገልጋይ፣ ‹‹ከአዳማ ወደ ሌላ የገጠር ወረዳ ከተማ የሞባይል ስልክ ከላኩኝ በኋላ በተባለው ቀን ሳይደርስ ቀረ። ይደርሳል ከተባለበት ቀን ለአንድ ወር ያህል ስልኩ ወደተላከበት ቅርንጫፍ ባስጠይቅም ገና አልደረሰም በማለት ለረዥም ጊዜ ሲያጉላሉኝ ነበር።›› ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹አዳማ ያለው ቅርንጫፍ ንብረቱን የተቀበለበትን ደረሰኝ ወረቀት ይዤ ስጠይቅ እኛ ልከናል ብለው የተላከበትን ቀንና ቁጥር ሲያሳዩዋቸው እንደነበር እና በመጨረሻ መኪናው መንገድ ላይ ተበላሽቶ ጋራዥ በገባበት ወቅት ጠፍቶብን ነው ያልደረሰው።›› የሚል ምላሽ ከተቀባዩ ቅርንጫፍ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል።

‹‹ይሁን እንጂ፣ የሞባይል ስልኩ ዋጋ እንዲከፈለኝ ወይም ተመሳሳዩ እቃ ምትክ እንዲሰጠኝ ስጠይቅ፣ ቆይ እስኪ ከዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ጋር መነጋገር አለብን በሚል ዓመት ሙሉ ካስጠበቁኝ በኋላ፣ በብዙ ጭቅጭቅ የሞባይል ስልኩ ከተገዛበት ዋጋ ጋር የማይገናኝ አነስተኛ ገንዘብ ነው የሰጡኝ። በእኔ እምነት ተቋሙ ውስጥ የተሳሰሩ ሌቦች አሉ›› በማለት ተናግረዋል።

ሌላኛዋ ቅሬታ አቅራቢ እንዲሁ ‹‹የተለያዩ ጌጣጌጦችን ውጭ አገር ካሉ ዘመዶቼ አስልኬ ሳይደርሰኝ ነው የቀረው። እርግጠኛ ባልሆንም ቦሌ አዲስ አበባ ያለው የጉምሩክ ኮሚሽን ለዚህ ተጠያቂ ነው›› ብለዋል።

‹‹አዲስ አበባ እንደገባ እርግጠኛ ስለነበርኩኝ ለመክሰስ ባስብም እነሱ የታወቁ ናቸው። ምንም ማድረግ አይቻልም ሲሉኝ ተውኩት። ብዙ ሰዎች በፖስታ ቤት እቃ ልከው በአግባቡ እንደሚስተናገዱት ኹሉ በርካቶችም እንደእኔ የላክነውና የተላከልን እቃ ቀልጦ ቀረ ሲሉ እሰማለሁ።›› ነው ያሉት።

‹‹የትምህርት ማስረጃዎችን በተደጋጋሚ እልክ ነበር። የላኩበት ቦታ የሚደርሱትም በተባለው ቀን ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ሰዎች ውድ እቃ ልከው ጠፍቶባቸው ቀረ ሲባል ስለምሰማ ምንም ነገር ከመላክ ተቆጥቤያለሁ።›› ሲሉ በተቋሙ ያላቸው አመኔታ ሙሉ እንዳልሆነ የገለጹ ሌላ ተገልጋይም አሉ።

‹‹ከውጪ አገር እቃ አስልከው ሳይደርሳቸው የሚቀር ደንበኞች እንዳሉ አውቃለሁ። ላፕቶፕና የእጅ ሰዓት አስልከው ሳያገኙ የቀሩ የማውቃቸው ሰዎችም አሉ።›› ያሉ ሌላ ግለሰብ ደግሞ፣ ‹‹ተቋሙ ካለው ረዥም እድሜና ታሪክ አንጻር ሌቦች በውስጡ እንዳሉ አያውቅም ማለት ስለሚያስቸግር እርምት ሊያደርግ ይገባል።›› ሲሉ መክረዋል።

የሚነሱት ቅሬታዎች ትክክለኛነት ያላቸው በመሆኑም እርምጃ የማይወሰድባቸው ከሆነ፣ የተቋሙን ተዓማኒነት የሚያወርድ ነው ሲሉ አሳስበዋል።

እንዲሁም የደንበኞች የሳጥን ኪራይ ዋጋ በተለይ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ከፍተኛ ጭማሪ በማሳየቱ፣ የደንበኞቹን ቁጥር ከመቀነሱ ባሻገር ጭማሪው ምንን አስመልክቶ እንደተደረገ ቅሬታ መፍጠሩን ነው ለማወቅ የተቻለው።

ከዚህ በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የላክነውን እቃ በታማኝነት የፈለግነው ቦታ በተባለው ጊዜ አድርሶልናል በማለት አስተያየት የሰጡም አሉ።

አዲስ ማለዳ ለኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት፣ ከላይ የቀረቡትን ቅሬታዎች በማንሳት ማብራሪያ የጠየቀች ሲሆን፣ የሚመለከተው የሥራ ኃላፊ ደውሎ ምላሽ እንዲሰጥ እናደርጋለን ቢባልም የተሰጠ ምላሽ የለም።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here