በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ በመሆናቸው እንዲሁም ሰዎች በማንነታቸው እየታሰሩ መሆናቸውን በመንግሥት ሥራ ላይ ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በመንግሥት ትምህርት ቤት በመምህርነት እና በሌሎች የመንግሥት ሥራ ኃላፊነቶች ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ በመሆናቸው፣ እንዲሁም በማንነታቸው እየተለዩ እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ማስረጃ ሳይኖር ካለ አጥጋቢ ጥያቄ የሚታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ረብሻ ታስነሳላችሁ፣ በሥራ ገበታችሁ ሙስና ትፈፅማላችሁ እንዲሁም በመንግሥት ተቋማት እና በተለያዩ ቦታዎች ረብሻ እንዲነሳ ታስተባብራላችሁ ተብለው እየታሰሩ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ሙሐመድ ኬቶሎ በአማሮ ልዩ ወረዳ ደርባ ቀበሌ በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመምህርት ተቀጥረው የሚሠሩ ሲሆኑ፣ “የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ዓላማ ታራምዳለህ” ተብለው በልዩ ወረዳው ፖሊስ ለእስር እንደተዳረጉ ለአዲስ ማለዳ መረጃውን ያደረሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
መምህሩ ድንገት ሳያስቡት በልዩ ወረዳው የፖሊስ አባላት ተወስደው እንደታሰሩ እና ከአንድ ሳምንት በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እና ምንም ዓይነት አጥጋቢ ምላሽ ሳይሰጥ በእስር እንደቆዩ ተገልጿል።
ከአስራ አምስት ቀን ቆይታ በኋላ ፖሊስ ጉዳዩን ወደ ልዩ ወረዳው ፍርድ ቤት ያቀረበው ሲሆን፣ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲውን ዓላማ እያራመዱ በትምህርት ተቋማት፣ በጤና ተቋማት እና በሌሎች የመንግሥት ተቋማት ላይ ረብሻ እንዲነሳ ያስተባብራሉ እንደተባሉም የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በተጨማሪም በአማሮ ልዩ ወረዳ እና በተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች በሐምሌ ወር 2014 ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ላይ ተባባሪ እንደነበሩ እና በየወቅቱ በሚታዩ የጸጥታ መደፍረሶች ላይ የጎላ ተሳትፎ አላቸው ከማለት ውጪ በመረጃ ተደግፎ እና አጥጋሚ ምላሽ ሳይሰጥ ፖሊስ በሕጉ ከተቀመጠው ቀነ ገደብ በላይ አስሮ በማቆየት ለፍርድ ቤት ያቀረበበት ሁኔታ እንዳለ ተጠቁሟል።
ለደኅንነታቸው ሲባል ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልተፈለገ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ ያሉ ተጨማሪ ግለሰብም ለእስር እንደተዳረጉ የአካባቢው ነዋሪዎች አስረድተዋል።
እኚህ ግለሰብ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ እንደነበሩ እና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ደጋፊ በመሆናቸው፣ እንዲሁም በአማሮ ልዩ ወረዳ እና በአጎራባች አከባቢዎች በየወቅቱ የሚፈጠሩ የጸጥታ መደፍረሶች ወይም ግጭቶችን አስመልክቶ መረጃ ታጋልጣለህ ተብለው ለእስር የተዳረጉ መሆናቸው ተነግሯል።
በተጨማሪ ሌሎች መረጃዎችንም በአካል እና በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ በመለጠፍ ለሌሎች ግለሰቦች መረጃ አሳልፈህ እያጋራህ ነው ተብለው እንደታሰሩም ነው የተገለጸው።
ከ2012 ጀምሮ መረጃው እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ላለፉት ኹለት ዓመታት ገደማ፣ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት በሥራ ገበታ ላይ የነበሩ ግለሰቦች ሙስና ፈጽማችኋል ተብለው ታስረው እስካሁን ባለው ጊዜ ውስጥ የፍርድ ውሳኔ ያልተሰጣቸው የሥራ ኃላፊዎች እንዳሉም ተጠቁሟል።
አዲስ ማለዳ ስለ ጉዳዩ የጠየቀቻቸው የአማሮ ልዩ ወረዳ ወንጀል መከላከል ቢሮ ኃላፊ ሻለቃ ሲዳሞ ማዳም በበኩላቸው፣ የተነሳው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ በልዩ ወረዳው የታሰሩት በሙስና እና በአካባቢው በነበሩ የጸጥታ ችግሮች ነው ብለዋል።
በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ከተቀመጠው ቀነ ገደብ ውጪ ለፍርድ ቤት ሳይቀርቡ የሚቀሩበት፣ እንዲሁም ውሳኔ ሳይሰጣቸው ለረጅም ጊዜ ታስረዋል በሚለው ጥያቄ ላይ አልስማማም ብለው ስሞታውን በማስተባበል ሰፊ ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014


