ዳሰሳ ዘ ማለዳማክሰኞ ጥቅምት 11/2012

0
641

1-ኢትዮጵያ እና ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ለከፍተኛ ጎርፍ እና ዝናብ ሊጋለጡ እንደሚችሉ የዩናይትድ ስቴትስ የአየር ትንበያ ባለሙያዎች አስጠንቅቀዋል። በተለይም አገራቱ ከባድ ዝናብና የጎርፍ መጥለቅለቅ ሲፈራረቅባቸው ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ የኢትዮጵያና የሱዳን ደቡባዊ ክፍሎች፣ ኡጋንዳ፣ የታንዛንያ ሰሜን ክፍል እንዲሁም ኬንያ ለጎርፍ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የውቅያኖስና የህዋ አስተዳደር አስታውቋል። ከዚህ ቀደም እነዚህ አገራት ከመስከረም እስከ ታኅሳስ ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚያገኙት ዝናብ ውስን መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የውቅያኖስና የህዋ አስተዳደር ገልጿል። (ቪኦኤ)
……………………………………………………………….
2–የገቢዎች ሚኒስቴር ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እና ከብሔራዊ ደኅንነት እና መረጃ አገልግሎት ጋር በቅንጅት በመሥራት ግብር የሚያጭበረብሩ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል። በተሰጣቸው እድል መሠረት ተጠቅመው ግብር የማያስታውቁ ድርጅቶች ላይ በቀጣይ የተጠናከረ እርምጃ እንደሚወሰድ እና ግብራቸው በወቅቱ ያላስታወቁ ግብር ከፋዮች በዘገዩበት እያንዳንዱ ጊዜ ያልተከፈለው ታክስ ላይ ከ5 በመቶ ጀምሮ 25በመቶ ድረስ ቅጣት እንደሚጣል ሚኒስቴሩ አስጠንቅቋል። (አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………….
3-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሩስያ የአፍሪካ የጋራ ፎረም ላይ ለመሳተፍ ሩስያ የገቡ ሲሆን ታላቁ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሩሲያ ቆይታቸውም ከአገሪቷ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና ከሌሎች አፍሪካ አገራት መሪዎች ጋር የኹለትዮሽ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። (አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………….
4-በአርባምንጭ አባያ ኃይቅ ላይ በደረሰ የጀልባ መስመጥ አደጋ ስድስት ሰዎች የደረሱበት እንዳልታወቀ የአካባቢው ፖሊስ አስታወቀ። አደጋው የተፈጠረው ትናንት ጥቅምት 10/2012 ከቀኑ 9:00 ሰዓት ላንቴ ተብሎ ከሚጠራው የነጭ ሳር ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ ሰዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ጭና ወደ አርባምንጭ ከተማ ስትጓዝ የነበረች አንዲት ጀልባ በመስጠሟ ነው። የጀልባዋን የነዳጅ ታንከር በመጠቀም እየዋኘ ራሱን ከአደጋው የታደገው የጀልባዋ ኦፕሬተር “ፉራ” በሚባል አካባቢ ከምሽቱ 3:00 ላይ በፓሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉንና በምርመራ ላይ መሆኑን የአካባቢው ፖሊስ አስታውቋል። (ኢቢሲ)
……………………………………………………………….
5-በጎንደር ከተማ አጠራጣሪ እንቅስቃሴ ላይ አገኘኋቸው ያላቸውን 38 ወጣቶች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የጎንደር ከተማ አስተዳደር የሰላምና ደኅንነት መምሪያ አስታወቀ። ትላንት ጥቅምት10/2012 ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጎንደር ከተማ ቀበሌ 15 “ሰሊጥ ለመሰብሰብ ሥራ እየሔድን ነው” በማለት በጉዞ ላይ የነበሩ ከተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች የመጡ 38 ወጣቶች በቁጥጥር ሥር ዉለዋል ብሏል መምሪያው። አንድ ግለሰብ አራት መታወቂያዎችን፣ ሌላ አንድ ወጣት ደግሞ ሰባት የውጭ ሀገር ሲም ካርዶችን እንደያዙ ማረጋገጡንም መምሪያው ተናግሯል። (ዋልታ)
……………………………………………………………….
6-በጉጂ ዞን ሊበን ወረዳ በሲኖትራክ ተሸከርካሪ ተጭኖ ሲጓጓዝ የነበረ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ 5 ሺሕ 147 የሞባይል ቀፎ እና 48 ነጥብ7 ኪሎ ግራም የሚመዝን የብር ጌጣጌጥ፣ ፖሊስና የሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አባላት ባደረጉት ከፍተኛ ክትትል በቁጥጥር ስር መዋሉን የገቢዎች ሚኒስቴር አስታዉቋል። (አዲስ ማለዳ)
……………………………………………………………….
7- የክልል የምርጫ ጽሕፈት ቤቶች ተዓማኒነት ያላቸው እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቋል። የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ እንደተናገሩት፤ የቦርዱ አመራሮች በዋናው መሥሪያ ቤት ደረጃ በሕዝብ ተሳትፎ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን ጥሪ ተደርጎ ተመልምለውና ፓርላማ ቀርበው ሹመት እንደተደረገ ሁሉ፣ በክልል ደረጃም አዲስ የሚመጡት በተመሳሳይ ተዓማኒነት ያላቸው እንዲሆኑ ለማድረግ እየተሠራ ነው። (አዲስ ዘመን)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here