ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ላለፉት አራት ዓመታት የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ሥራ በማቆማቸው ለአላስፈላጊ ወጪ ተዳርገናል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መቀመጫ ከሆነችው አሶሳ ከተማ እና በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ እንዳስረዱት፣ የኦነግ ሸኔ ቡድን በአሽከርካሪዎች እና በተጓዥ ላይ ግድያ፣ አፈና እና ጥቃት እየፈጸመ በመሆኑ አሽከርካሪዎች አገልግሎቱን ለማቆም ተገደዋል ብለዋል።
በዚህ ሳቢያ በኢኮኖሚ የተሻለ ገቢ ያለው ከ3 ሺሕ 800 ብር በላይ ለአየር በረራ ክፍያ በመፈፀም ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ወደ አዲስ አበባ ከተማ ይጓዛል። የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት፣ የንግድ ሥራን ለማከናወን እና ሌሎች የግል ጉዳያቸውን ለማስፈፀም የሚመላለሱበት ሂደት ቢኖርም ለአላስፈላጊ ወጪ በመዳረጋቸው ተፅእኖ እንዳሳደረባቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪ አነስተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች ለሕክምናም ሆነ የግል ጉዳያቸውን ለማስፈፀም ወደ መዲናዋ ማቅናት እንዳልቻሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።
ከዚህ ባለፈ የትራንስፖርት ተሽከርካሪ ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መጓዝ ባለመቻሉ በንግዱ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች የሕንፃ እንዲሁም የጽሕፈት መሣሪያዎችን፣ ሸቀጣ ሸቀጦችንና ሌሎች ለምግብነት የሚውሉ ቁሳቁስ እና አልባሳትንም ወደ አካባቢው ለማስገባት እንደተቸገሩ አውስተዋል።
ከዚህም አንፃር ማኅበረሰቡ ላይ እያሳደረ ካለው ተደራራቢ ተጽእኖ ጎን ለጎን በተለያዩ የክልሉ ከተሞች ሸቀጣ ሸቀጦችን በተመጣጠነ ዋጋ መግዛት እየቻሉ እንዳልሆነ እና ማግኘት እንዳልቻሉም ገልፀዋል።
ነዋሪዎቹ አክለውም፣ እስከ 2010 ድረስ የሕዝብ አገልግሎት ሰጪ አውቶብሶችም ሆኑ ሌሎች ዶልፊን፣ አባዱላና ተመሳሳይነት ያላቸው ተሽከርካሪዎች ከአዲስ አበባ ከተማ ወደ ክልሉ አገልግሎት ይሰጡ ነበር። ከ2010 በኋላ ግን ላለፉት አራት ዓመታት የትራንስፖርት አገልግሎቱ ተቋርጦ ይገኛል ብለዋል።
ወደ ክልሉ የትራንስፖርት አገልግሎት ሊቋረጥ የቻለው ተሽከርካሪዎች መነሻቸውን አዲስ አበባ ከተማ አድርገው የኦሮሚያ ክልል የሚገኙትን አምቦ፣ አዲስ ዓለም፣ ጊንጪ፣ ባኮ፣ ነቀምቴ እና ሌሎች የተለያዩ አካባቢዎችን አቆራርጠው በሚጓዝበት ወቅት ኦነግ ሸኔ በተለያዩ ቦታዎች መሽጎ በአሽከርካሪዎች እና በተጓዥች ላይ ጥቃት እና ግድያ እየፈፀመ በመሆኑ ነው።
የክልሉ መንግሥት በቡድኑ የሚፈጸሙ ችግሮችን በማስቆም ወደ ክልሉ የሚያመላልስ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያስጀምር ብንጠይቅም ጥያቄው ምላሽ አላገኘም ብለዋል።
አዲስ ማለዳ ስለጉዳዩ የጠየቀቻቸው የኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ታጠቅ ነጋሽ፣ በኢትዮጵያ በአንዳንድ አካባቢዎች በሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ሳቢያ የተስተጓጐሉ የትራንስፖርት መስመሮች አሉ ብለዋል።
ችግሩን ለመቅረፍ እና ሕገ ወጥ ድርጊቶችን ለመቆጣጠር የፌዴራል መንግሥት እየሠራ እንደሚገኝ እና የትራንስፖርት መስተጎጉሎችንም ከክልል ትራንስፖርት ቢሮዎች ጋር በመሆን ለመቅረፍ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ችግሮችን በመቅረፍ በ2015 የሕዝብ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ይደረጋል ያሉት ዳይሬክተሩ ናቸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015



