ኢትዮጵያዊያን ሩህሩህና ደግ ነን ብለን ብናስብም፣ ከዛ ተቃራኒ የሆኑ ብዙ እኩይ ምግባራት ስንፈጽም ተመልክተናል። እንግዳ ተቀባይና ለወደድነው መሬት ነን እንበል እንጂ፣ ስንገፋፋና ስንጠላላ፤ እርስ በእርስም ክፋትን ስናደርግ ታይተናል። ደጋጎች የሌሉ፣ ቀና ልብ ያላቸው በጎ ሰዎች የጠፉ እስኪመስል ድረስ፤ ጭካኔና ጥፈት ጎልቶ ሲታይም ቆይቷል።
በቀደመው ዘመን የሚነገር አንድ ታሪክ አለ። እንዲህ ነው፤ እኛ የበለጠ ጨካኞች ነን የተባባሉ ተፋላሚ ወገኖች ግፍ በየተራ በመሥራት ይፎካከራሉ። በዚህም የተነሳ ለቀናት ዋናውን ጦርነት አቋርጠው ይቆያሉ። አንዱ የአንዱን ምርኮ እያወጣ አንዱን አካሉን ቆርጦ ለባላንጣው ወገኖች በአቅራቢያ እንዲያገኙት ያስቀምጣል። ሌላኛውም እኔ እብስ ብሎ ካጎረበት አውጥቶ የዛኛውን ወገን ሌላም አካል ጨማምሮ አጉድሎ ይልካል።
እንዲህ እንዲህ በየተራ ለቀናት የሰው ልጅ ላይ ግፍ እየፈፀሙ ሲላላኩ ይቆያሉ። ይህ ሂደት ቀጥሎ በስተመጨረሻ እጅግ ዘግናኝ የሆነና ራሳቸውም ሊቋቋሙት ያልቻሉት ጭካኔ በአንዱ ወገን ላይ ተፈጽሞ፤ አንደኛቸው ምነው ቢቀርብን ብለው ግፍ መሥራታቸውን እንዳቆሙ ይነገራል።
የግፍ ትንሽ የለውምና በሰው ሕይወትም ሆነ አካል እንዲሁም ንብረት ላይ የሚፈጸም ማናቸውም ጭካኔና ግፍ እየጠነከረና እየገዘፈ ይሄዳል እንጂ እንደማይቀንስ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በማናለብኝነትም ሆነ ለፉክክር ተብሎ የሚገባበት እንዲህ አይነት ዘግናኝ ድርጊት ይቅርና በአጋጣሚ የሚፈጸመውም ዘላለም የማይጠፋ ቁርሾ መፍጠሩ አይቀሬ ነው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከተካሄዱ አያሌ ጦርነቶች አኳያ የሟቾች ቁጥር በአንጻራዊነት ቢሰላ እንደቅርቦቹ እንደማይሆን ከጦር መሣሪያዎቹ ዘመናዊነት አንፃር ተነስተው የሚናገሩ አሉ። ታዲያ መሣሪያዎቹ ጅምላ ጨራሽ ሲሆኑና ዘመናዊ ሲባሉ፣ አስተሳሰባችን ግን ሳይዘምን እጅግ ኋላቀር እየሆነ መጓዙ እንደቀጠለ ከተግባራችን መረዳት ይቻላል።
ሰው ተዘቅዝቆ ተሰቀለ ሲባል ጉድ ተብሎ ለቀናት ያሳዘነን ድርጊት እጅግ አነስተኛው ግፍ እስኪመስለን ድረስ አሁን አሁን የምንሰማው ለጆሮም ይሰቀጥጣል። ጦርነቱን ተንተርሰው የሚፈፀሙ የግፍ ዓይነቶች ከመበራከታቸው አኳያ የሚያወግዘውም ሆነ የሚደነግጥ እየቀነሰ ስለመምጣቱ ብዙ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም።
በሌላ በኩል፣ በግለሰብ ደረጃ ሕጻናት ላይ ጭምር የሚፈፀም የግፍ ተግባርም መብዛቱ ብቻ ሳይሆን ፈጻሚውና አፈጻጸሙ እየዘገነነ መጥቷል። የወራት እድሜ ያላት ሕጻን ልጁን አባት ደፈረ ብለው በወላጅ መካከል ያለ አስተሳሰብን የሚያበላሽ መረጃም ይፋ ሆኗል። አደራ የተሰጣቸውን ሕጻናት በዘግናኝ ሁኔታ ያረዱ፣ ፍሪጅ ውስጥ የጨመሩ እንዲሁም ይህን መሰል አሰቃቂ ግፍን የሚፈጽሙ ከሟቾች ጋር ያላቸው ግንኙነት እምብዛም ነበር። ከጓደኛው ጋር በተፈጠረ ግጭት አበባየሁ ጨፍረው የተመለሱ ልጆቹን በግፍ የሚያርድ ጓደኛ ያለበት አገርም በመሆናችን እርምጃችን ከአሁኑ ካልታሰበበት ከዚህም እንደሚብስ አዲስ ማለዳ ታመላክታለች።
አገር በሰቆቃ ውስጥ እንድትኖር የሚፈልጉ የአንዱን ተግባር ወደሌላው እያደረጉም ሆነ እያጋነኑ ጥላቻ እንዲፈጠር የሚያደርጉና ቁርሾው እንዳይጠፋ የሚሠሩ አሉ። በተለይ በጦርነት ቀጠና ውስጥና በጥላቻ መንፈስ ውስጥ ያሉ ጠላት ያሉትን ለማጥቃት ሲሉ ቆመንለታል የሚሉትን ሰብዓዊነት ሲጥሱ ማየት የተለመደ ነው። ሴቶቻችን ተደፈሩብን ብሎ የሌላውን እያሳደዱ መድፈር፣ ሕጻናትን ለሰቆቃና መከራ መዳረግ፤ በበቀል ስሜት ንብረትና ሀብትን መዝረፍና ማውደሙ ከዚህ ቀደም ካለው ብሶ ቀጠለ እንጂ እንዳልቆመ ይታያል።
ተፋላሚ ወገኖች በያዙት መንገድ ምን ያህል ዘመን፣ እንዲሁም ምን ያህል መስዋዕትነት ከፍለው ለመቀጠል እንዳሰቡ ለራሳቸውም ግልፅ የሆነላቸው አይመስልም። እድሜ ልካቸውን እየተፋለሙ ለመቀጠል ቢወስኑ እንኳን ጭካኔያቸውን እንደነሱ ልጆቻቸው ሊቀጥሉት እንደማይቻላቸው ሊረዱት ይገባል።
ጦርነት ሕጋዊ እስኪመስል ድረስ መገዳደል የሚፈቀድበት ሂደት ቢሆንም፣ ከጥንት ጀምሮ ሕግና ሥርዓት አለው። ምርኮኛ፣ ቁስለኛ እንዲሁም አስከሬን ጭምር የራሱ ክብር አለው። በዓለም ዐቀፍ ድንጋጌ ጭምር የተደገፈ የሚጠበቅላቸው መብትና የሚፈጽሙት ግዴታ እንዳለ የተለያዩ መርሆዎችን ማንሳት ይቻላል።
“ሙት አይወቀስም” እየተባልን ባደግን ማኅበረሰብ ውስጥ ሆነን፣ የማናውቀው አስከሬን ለቀብር ሲያመራ “እምፅፅ..” እያልን ከንፈር በመምጠጥ የምናዝን ኅብረተሰቦች አሁን አሁን እያሳየን ያለነው አጉል ጀብደኝነት ሊቆም እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ትመክራለች።
በጦርነት የተሰዉ ተፋላሚ ወገኖች አስከሬንን ለማሳየት መጣደፍ፤ ይህን ያህል ሕዝብ አለቀ ብሎ እንደጋራ ጠላት ለመደሰት መቸኮል እንዲሁም ምርኮኛን ለመቀስቀሻነት መጠቀም ሊያሳፍር የሚገባ እንደከባድ ግፍ መቆጠር ያለበት ድርጊት ነው። ፌስቡክ እንዳይከለክለን ሳይሆን ሕሊናችን ከልክሎን እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ተግባራትን ከማሰራጨት መቆጠብ ነበረብን።
ታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ ተራ ተዋጊዎችን አስከሬን ምስል ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ብሎ መጠቀም ይዘገንናል ይቁም ማለት ለዚህ ትውልድ ብቻ ሳይሆን፣ ለቀጣይ ትውልድም የሚያመረቅዝ ቁስል እንዳይፈጥር መታሰብ አለበት። ኹሉም ሰው የሚወደውና የሚሳሳለት ቤተሰብ እንዳለው ልናስተውል ግድ ይለናል።
ወንበዴም ይሁን ሀብታም ነጋዴ፣ ተራም ሰው ይሁን ዝነኛ ፖለቲከኛ ግፍ ሲፈጸምበት ዐይቶ ዝም የሚል ቤተሰብ አይኖረውም። አገራችንን እዚህ ደረጃ ያደረሳት የዘመናችን ቁርሾ ብቻ እንዳልሆነ የምንረዳ፣ ለምንሳሳላቸው ልጆቻችን ሌላ ዙር መከራን አናስቀምጥላቸው። የምናቆይላቸው የገንዘብ እዳ ይብቃቸውና ግጭታችንንም ሆነ አለመስማማታችንን ፈትተን አብረን በአንድ አገር ዜግነትም ሆነ በጉርብትና ለመኖር ሰላም እንደሚያስፈልገን ከአውሮፓ የ500 ዓመት የጦርነት ታሪክ መማር እንችላለን። ለቀዝቃዛውም ሆነ ለሚፋጁት የዓለም ጦርነቶች መንስኤ የሆኗቸው የየዘመናቱ አሸናፊዎች በተሸናፊዎቻቸው ላይ የፈጸሙት ግፍም እንደሆነ ልናስተውል እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።
ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015