• አንድ ኪሎ 120 ብር እየተሸጠ ነው
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ክልል ከተሞች በሸማች ማኅበራት የሚቀርበው ስኳር የአቅርቦት እጥረት ምክንያት የስኳር ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ዐሳይቷል።
አዲስ አበባ ውስጥ የጀበና ቡና በመሸጥ ራሷን የምታስተዳድረው ሥሟን መግለጽ ያልፈለገች ወጣት እንደገለጸችው፣ ስኳር በፈለገች ጊዜ አለማግኘቷ፣ ስታገኝም ዋጋው የናረ መሆኑ ለሥራዋ እንቅፋት ሆኖባታል።
‹‹አንድ ኪሎ ስኳር 120 ብር እየገዛሁ መሥራት ከብዶኛል›› የምትለው ወጣቷ፣ የቡና እና ስኳር ዋጋ መናር ተዳምረው አስር ብር ትሸጠው የነበረውን የአንድ ሲኒ ቡና ዋጋ አስራ አምስት ብር እንድታደርግ እንዳስገደዳት ገልጻለች። ከሸማች ማኅበራት በወር አንድ ኪሎ ስኳር ማግኘት የምትቸል ቢሆንም፣ ስኳር ሲመጣ በሚኖረው ረዥም የወረፋ ሰልፍ ምክንያት ስኳር ወስዳ እንደማታውቅ ትናገራለች። በተያያዥ ዋጋዎች መናር ምክንያት ሥራ የመቀየር ሐሳብ እንዳላት የገለጸችው ወጣቷ፣ ስኳር በዚህ ደረጃ ተወዶ ስታይ የመጀመሪያዋ እንደሆነ ትናገራለች።
አዲስ ማለዳም አዲስ አበባ ውስጥ ተመሳሳይ ምልከታ ባደረገችባቸው የጀበና ቡና የሚሸጥባቸው ቦታዎች ላይ የስኳር ዋጋ መናር ጉዳይ ሻይና ቡና የማቅረብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችና ደንበኞቻቸውን ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል። በዚህ ዋጋ መናር ምክንያትም በአንድ ሲኒ የጀበና ቡና ላይ ከኹለት እስከ አምስት ብር ጭማሪ እንዲኖር እንዳደረገ አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
በቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ገነት ገብረጊዮርጊስ፣ ስኳር መግዛትን እንደ ቅንጦት እየተመለከትኩት እገኛለሁ ባሉበት ንግግራቸው፣ ከሸማች ማኅበር በኹለት ወር አንድ ኪሎ ከግማሽ ስኳር እንደሚያገኙ ይናገራሉ። ይህም በየወሩ ሊደርሳቸው ይገባ ከነበረው ሦስት ኪሎ እጅጉን ያነሰ ነው ብለዋል። በዚህም ምክንያት ከቸርቻሪ ነጋዴዎች አንድ ኪሎ ስኳርን በአንድ መቶ ኻያ ብር ለመግዛት እንደተገደዱ ተናግረዋል። ይህም ከሸማች ማኅበር ከሚገዙበት የአንድ ኪሎ አርባ ስድስት ብር ዋጋ አንጻር እጅግ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚኖሩት ነፃነት ዓለሙ ደግሞ፣ አባል በሆኑበት የሸማች ማኅበር ከዚህ በፊት በአንድ ሰው በወር አንድ ኪሎ ታስቦ ለስድስት ቤተሰቦቻቸው በወር ስድስት ኪሎ ስኳር ይወስዱ እንደነበር ተናግረዋል። ይሁንና ከጥር ወር 2014 ጀምሮ የስኳር አቅርቦት እንዳልነበረና በሰኔ እና ነሐሴ ላይ በፊት ይሰጣቸው ከነበረው ስድስት ኪሎ በግማሽ ቀንሶ ሦስት ኪሎ ብቻ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል። ከሸማች ማኅበር ከሚገዙበት የአንድ ኪሎ ስኳር አርባ አምስት ብር ዋጋ በላይ ከቸርቻሪ ነጋዴዎች እስከ ሰማንያ ብር ዋጋ ሲገዙ የቆዩ ቢሆንም፣ በቅርብ ጊዜያት ግን አንድ ኪሎ ስኳር አንድ መቶ ዐስር ብር ደርሷል ብለዋል።
ለሸማች ማኅበራት የሚደርሰው የስኳር አቅርቦት ከተሻሻለ ዋጋውን ለመቆጣጠር እድል የሚፈጥር ቢሆንም፣ በሕገ-ወጥ መንገድ በቸርቻሪዎች የሚሸጠውን ስኳር ወደ ሕጋዊ መንገድ ማምጣት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎች መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሠራበት አሳስበዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቁምነገር እውነቱ እንዳረጋገጡት፤ የስኳር አቅርቦት ችግር እንዳለ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ጥቆማ ደርሶታል። ይህንንም በመመልከት ፈጣን ምላሽ ለመስጠት በመሥራት ላይ እንደሚገኙ የጠቆሙት ቁምነገር፣ የአቅርቦትና ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት ይሠራል ብለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015



