በ2014 በጀት ዓመት በአገር ዐቀፍ ደረጃ ከአምስት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የንፁሕ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ መሆናቸውን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶክተር ኢንጂነር) በ2014 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ 5.3 ሚሊዮን ዜጎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመደረጉ የሀገራዊ የውሃ ሽፋን 3.97 በመቶ ጨምሯል ብለዋል። በአገሪቱ የንፁሕ መጠጥ ውሃ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ ይታያል ያሉት ሚኒስትሩ፣ የመጠጥ ውሃ እጥረት በተለይም ለኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች አጀንዳ መሆን አልነበረበትም ብለዋል።
ለንፁሕ መጠጥ ውሃ እጥረት አንዱ ምክንያት የውሃ ሃብት አጠቃቀም ላይ ያለው ዝቅተኛ ግንዛቤ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ በሌላ በኩል በኅብረተሰቡ ዘንድ የጠባቂነት መንፈስ መኖሩ ሁኔታውን አደገኛ እንደሚያደርገው አብራርተዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ የተገነቡ የመጠጥ ውኃ ጣቢያዎችን የመንከባከብ፣ የመቆጠብና በኃላፊነት የመጠቀም ግዴታን በማስረጽ ኅብረተሰቡ ውሃና የውሃ ተቋማትን በኃላፊነት መያዝና ማስተዳደር የሚችልበት አግባብ መፍጠር እንደሚገባ ገልፀዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015


