ብሔራዊ ፈተናዎች አግባብ ባልሆነ መልኩ ከፈተና ቀናቸው በፊት ተሰርቀው ይወጣሉ የሚሉ ስሞታዎች ለበርካታ ዓመታት ዘልቀዋል። ግንቦት 22/2008 ግን ስሞታ ይመስል የነበረው ጉዳይ ዐይን ያፈጠጠ እውነት መሆኑ ተረጋገጠ።
በጊዜው የተሰጡት የእንግሊዘኛ እና የሒሳብ ትምህርት ፈተናዎች ቀድመው መውጣታቸው ተረጋግጦ ፈተናው እንዲቋረጥ ተደረገ። 12 ዓመትና ከዛ በላይ የለፉ ተማሪዎች፣ የልፋታቸውን ፍሬ የሚያዩበት ፈተና በእንዲህ ዓይነት ስርቆት ለተወሰኑ ተማሪዎች ፈተናነቱ ቀርቶ ቀደመው የያዟቸውን መልሶች ለመሙላት የሚገቡበት ሲሆኑ፤ በትክክለኛው መንገድ በተዘጋጁበት መጠን ለመመለስ ወደ ፈተና ለገቡት ደግሞ ሽብርን የሚፈጥር ሆነ።
በወቅቱ ተፈታኝ የነበረው ትንሳኤ አማኑኤል፣ ፈተናው ከመጀመሩ በፊት ተሰርቆ እንደወጣ ይወራ እንደነበርና ለመዘጋጀትም ተቸግሮ እንደነበር ያስታውሳል። ተጀምሮ ከተቋረጠው ፈተና በኋላ በተፈተኑት ፈተናም እምነት እንደሌለውና አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ውጤቶች በዝተው እንደነበር በማስታወስ ፈተናው በድጋሚ ቀድሞ ወጥቶ እንደነበር ማረጋገጫ ነው ብሏል።
ትንሳኤ 12 እና ከዚያ በላይ የሚሆኑ ዓመታትን ለፍተው፣ የልፋታቸውን ዋጋ የሚያገኙበትን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተናን አግባብ ባልሆነ መንገድ አግኝተው ከፍተኛ ውጤት ባመጡ ሰዎች ተበልጠው ከዓላማ መሰናከልን ያህል ልብ ሰባሪ ጉዳይ የሌለ ሲሆን፣ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት ችላ ያለው ጉዳይ ነበር ብሏል።
ከ2008 በፊትም በኋላም ፈተና እንዲደገም ያስቻሉ ስርቆቶች ባያጋጥሙም ፈተናዎች ተሰርቀው እንደወጡ የትምህርት ሚኒስቴርም ያመነው ጉዳይ ነው። ከእነዚህ የፈተና ስርቆቶች ውጪም በፈተና አስተራረምና ውጤት አሰጣጥ ጉዳይ ጥያቄዎች እንደሚነሱ የ2013 ፈተና ማሳያ ነው። እነዚህና ሌሎች ጉዳዮች ፈተና የሆኑበት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መግቢያ ፈተና የ2014 ተፈታኞችን በአዲስ መንገድ ለፈተና ለመቅረብ እንዲገደዱ አድርጓል።
‹‹እብደቱ የሚጀምረው በክልሎች መካከል ባለው አግባብ ያልሆነ ውድድር ነው።›› የሚሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) ‹‹‘የኔ ክልል ጥሩ እየሠራ ነው፣ ብዙ ተማሪዎችን አሳለፈ’ ለማለት የሚደረጉ የእኔ እበልጥ ፉክክሮች፣ የግል ትምህርት ቤቶች ገንዘብ በማሰባሰብና ለፈታኞች ጉቦ በመስጠት ያልለፉበትን ለማግኘት የሚደረጉ ጥረቶች ትምህርት መሆን ከሚገባው ውጪ አድርገውታል›› ብለዋል።
የፈተና አሰጣጡን ለማሻሻል የተወሰነው ውሳኔ
ባለፉት ዓመታት ችግሮችን ለመቅረፍና ዲጂታል በሆነ መንገድ ፈተናውን ለመስጠት ያልተሳኩ ዝግጅቶች ሲደረጉ ነበር የሚሉት ሚኒስትሩ፣ አንድ ሚሊዮን የሚሆኑ ታብሌቶችን ለማዘጋጀት እስከ አምስት መቶ ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግና ይህን እስካሁን ማሳካት እንዳልተቻል ገልጸዋል። እንደ ጊዜያዊ መፍትሄም ፈተናውን ከክልል ትምህርት ቢሮዎች ጋር ሳይገናኝ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ለማካሄድ እንደተወሰነና ተፈታኞች ወደ ዩኒቨርሲቲዎቹ ሄደው እንዲፈተኑ ማድረግ የፈተና ስርቆቶችን ማስቀረት ባይችል እንኳን እንዲቀንሱ እንደሚያደርግ እንደታመነበት ተናግረዋል።
በዚህም ፈተናው ብሔራዊ እንደመሆኑ መጠን በፌዴራል የትምህርት ተቋማት ውስጥ መካሄዱ የፌዴራል መንግሥት ቁጥጥር ለማድረግ ያመቸዋል ብለዋል።
በኹለተኛ ደረጃ ትምህርት የቢዝነስ ትምህርት መምህር ያሬድ አዲሱ እንደሚሉት፣ ምንም እንኳን የተማሪዎች የሥነልቦና ዝግጅት አጠያያቂ ቢሆንም፣ ፍትሀዊ የሆነ የፈተና አሰጣጥን ለማምጣት ትምህርት ሚኒስቴር የወሰነው ውሳኔ የተሻለ ውጤትን ማምጣት የሚያስችል ነው። በሚያስተምሩበት ትምህርት ቤትም ለ2 ሳምንታት የዘለቀ በመምህራን የሚመራ ክለሳና የሥነልቦና ዝግጅት የተደረገ ሲሆን ሞዴል ፈተናዎችን በመጠቀምም ተማሪዎቸ ይበልጥ እንዲዘጋጁ እያደረግን ነው ብለዋል።
ይህ የፈተና አሰጣጥ ተማሪዎች ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ከሳምንት የበለጠ ጊዜን በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዲያሳልፉ የሚያደረግ በመሆኑ፣ ተማሪዎች ለፈተናው ከሚያደርጉት የትምህርት ዝግጅት ባልተናነሰ በሥነልቦና መጠንከር እንደሚገባቸውም ተናግረዋል።
የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ አንዱ መንገድ ይሄው ነጻ የሆነና በእውቀት ብቻ ማለፍ የሚቻልበትን የፈተና ሥርዓት መዘርጋት መሆኑን የገለጹት ያሬድ፣ ይህኛው የፈተና አሰጣጥ ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል ብለው ባያስቡም የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ እንደሚያስችል አምናለሁ ብለዋል።
‹‹ከዘጠነኛ እስከ አስራ ኹለተኛ ክፍል የተማርነውን መፈተናችን ዝግጅታችንን ከባድ አድረጎብናል›› የምትለው የዘንድሮ ተፈታኟ ምህረት ዋስይሁን ናት፡፡ ምህረት ‹‹ምንም እንኳን የፈተናው አለመሰረቅ ጥቅሙ ለተፈታኝ ተማሪዎች ቢሆንም፣ በዩኒቨርሲቲዎች ለመፈተን ስንሄድ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥመን እንደሚችል እኔንና ጓደኞቼን አስጨንቆናል፡፡›› ትላለች።
‹‹ረዘም ያለ የዝግጅት ጊዜ የነበረን ቢሆንም አብዛኛውን ጊዜ በጭንቀት ነው ያሳለፍነው፡፡›› የምትለው ተማሪዋ፣ የአራት ዓመታት ትምህርቶችን ከዚህ በፊት የተፈተነ ስለሌለና ፈተናዎቹ ምን ዓይነት ሊሆኑ እንደሚችሉ አለማወቃቸውም ሌላው የጭንቀታቸው ምክንያት ነው ትላለች። ፈተናዎቹ በ12 የመፈተኛ ኮዶች መከፋፈላቸው ኩረጃን ማስቀረት እንደሚያስችል አምናለሁ ያለችው ምህረት፣ በመምህሮቿም ተመሳሳይ ነገር እንደተነገራት ገልጻለች።
በተማረችበት ትምህርት ቤት ለኹለት ሳምንት የዘለቀ ክለሳ ማድረጋቸውን ምህረት ታወሳለች። በዋናነት አስራ አንደኛና አስራ ኹለተኛ ክፍል የተማሯቸው ትምህርቶች ላይ አተኩረው መዘጋጀታቸውንም ጠቅሳለች። ‹‹ዩኒቨርሲቲ ብገባ ምን ዓይነት ሕይወት ሊያጋጥመኝ ይችላል የሚለውን ቀድሜ እንዳይ ያስችለኛል።›› ያለችውን ይህ አጋጣሚ በአግባቡ ለመጠቀምና ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንደምታስብም ተናግራለች።
ለፈተና ወደ ዩኒቨርሲቲዎች ሲሄዱ ማሟላት ያለባቸውና ይዘው መገኝት የሌለባቸው ተብለው የተገለጹት ነገሮች ላይ ምክንያታቸውን ብትረዳም፤ ለመተግበር ግን አስቸጋሪ የሆኑ ጉዳዮች እንዳሉ አንስታለች። ለአብነትም ስልክን ይዞ መግባት አለመቻሉን በማንሳት፣ ከተቻለ ከቤተሰብ ጋር መገናኘት የምንችልበት አማራጭ ቢፈጠር መልካም ነው ብላለች።
ከመስከረም 30/2015 ጀምሮ በመጀመሪያው ዙር የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችን በኹለተኛ ዙር ደግሞ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎችን ይዞ በኹለት ዙር እንደሚደረግ የተገለጸው ፈተናው፣ አገሪቷን ለተጨማሪ ወጪዎች የዳረገ ነው። ተፈታኞቹም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚቆዩበት ጊዜ የምግብና የመኝታ አገልግሎት እንደሚያገኙ ተነግሯል። የመፈተኛ ዩኒቨርሲቲያቸው ከሚኖሩበት ቦታ ከ50 ኪሎሜትር በላይ ለሚርቅ ተፈታኞች ደግሞ የወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤቶች የትራንስፖርት ወጪያቸውን እንደሚሸፍኑም ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
‹‹ወላጆቼ ለፈተና የተመደበኩበትን ዩኒቨርሲቲ በአካል ሄደው ዐይተውታል›› የምትለው ሌላዋ ተፈታኝ ናርዶስ በየነ ናት፡፡ ናርዶስ ‹‹የመፈተኛ ጣቢያዬ ከምኖርበት አካባቢ ቢርቅ ኖሮ ፈተናው ያመልጠኝ ነበር›› ብላለች። አሁንም ወላጆቿ ፍርሀት ያለባቸው ሲሆን፣ በመፈተኛ ጣቢያቸው ሄደው ያነጋገሯቸው የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ለወላጆቿ ያስረዷቸው ነገሮች እንድትፈተን እንድትወስን እንዳደረጓት ተናግራለች።
ይሁንና ወደ መፈተኛ ጣቢያቸው ሲሄዱ ሊያሟሏቸው ስለሚገቡ ነገሮች በወጣው መመሪያ ላይ ቅሬታ አለኝ ብላለች። ከቤተሰብ ጋር መገናኛ ስልክ ይዘው መግባት ቢችሉ ቤተሰብ ከጭንቀት ይገላገላል ብላ እንደምታስብ ገልጻ፣ በፈተና ቀናት ቤተሰቦቿ በፈተና ጣቢያው አቅራቢያ ሆነው ሁኔታዎችን ለመከታተል እንዳሰቡ ተናግራለች። ለፈተናው ለመዘጋጀት ጥሩ ጊዜ ነበረን ያለችው ናርዶስ፣ ግንቦት ወር 2014 ሰማሁት ያለችው ከዘጠነኛ እስከ አስራ ኹለተኛ ክፍል የተማሩትን ትምህርቶች የሚያካትተው የፈተናው ይዘት ግን ዝግጅቷን ፈታኝ እንዳደረገባት አልደበቀችም። ‹‹የቻልኩትን ያህል ጥረት አድርጌአለሁ›› ብላለች።
በጦርነት በተጎዱ አካባቢዎች ያሉ የ2013 ተፈታኞች ዳግም እንዲፈተኑ በተፈቀደው መሠረት ለመፈተን እየተዘጋጀ እንደንሆነ የተናገረው ቢንያም ደምል ሌላው አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው ተፈታኝ ተማሪ ነው። ‹‹ፈተናው ሳልፈተን አለፈኝ ከምል ብዬ ነው የምፈተነው ብሏል።
የፈተናውን ዝግጅት በቅርብ ጊዜ እንደጀመረ ገልጾ፣ ትምህርት ሚኒስትሩ ከተቻለ ሁሉንም ተፈታኞች ከክልላቸው ውጪ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲፈተኑ እናደርጋለን ብለው የተናገሩት ቃል ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ አገሪቷ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ለተፈታኞች ከባድ ይሆን እንደነበር ተናግሯል። የከተማና የዩኒቨርሲቲ ኑሮ አዲስ የሚሆንባቸው ተፈታኞች እንደሚኖሩ ባያጠራጥርም፣ ለጊዜው የድካማቸውን ዋጋ ለማየት የተሻለው አማራጭ ይሄ እንደሆነ እንደሚያምንም አሳውቋል።
የፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ መፈተናቸው በርካታ ጠቀሜታዎች አላቸው። ወላጆችም አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ልጆቻቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው ተናግረዋል። ፈተናዎች በሚጓጓዙበት ወቅትና በፈተናው ሰዓት የሚደረጉ የስርቆትና የማጭበርበር እንዲሁም የኩረጃ ሙከራዎች እንዳይኖሩና ካሉም ለማስቆም ከፍተኛ እድልን ይፈጥራል ብለዋል። ዋና ዳይሬክተሩ በተጨማሪም ተፈታኞች ዩኒቨርሲቲዎችን ቀድመው በአካል ማወቃቸው ለወደፊት የትምህርት ሕይወታቸው ጠቃሚ እንደሆነ ተናግረዋል።
ለቀጣይ ፈተናዎች
ብዙ ጥያቄዎች በሚነሱበት የአገራችን የትምህርት ሥርአት ውስጥ ይሄ የፈተና ጉዳይ በራሱ ፈተናነቱ እንዳለ ሆኖ ወደፊት ለሚታሰበው ዲጂታል የፈተና ሥርአትም ተማሪዎችን ከአሁኑ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ መምህር ያሬድ አዲሱ አሳስበዋል። ተማሪዎች ከቴክኖሎጂ ጋር ቀድመው መተዋወቅ እንዳለባቸው የሚያምኑት ያሬድ፣ የቴክኖሎጂ ትምህርቶችን በተለይ በገጠር ትምህርት ቤቶች በአግባቡ በመስጠት ፈተናዎችን በዲጂታል መንገድ መውሰድ የሚችሉ ተማሪዎችን ማብቃት ያስፈልጋል ብለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015



