በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን በምትገኘው ዴራ ከተማ በካርታ ላይ ካርታ እንደሚሰጥና ይህም ብዙዎችን እያማረረ መሆኑን ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የግንባታ ባለሙያ መሆናቸውን ገልጸው ሥሜ አይጠቀስ ያሉ የዴራ ከተማ ነዋሪ፣ የከተማዋ መሬት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በአንድ ቦታ ላይ ተመሳሳይ የይዞታ ካርታዎችን በመሥራቱ ብዙዎች እየተማረሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በቅርቡም ከውጪ አገር በተላከለት ገንዘብ ቦታ የገዛ የቅርብ ሰው፣ ሕጋዊ ካርታ የያዘና መሬቱ የኔ ነው የሚል ሌላ አካል በመምጣቱ ግለሰቡ ለብዙ ችግር መጋለጣቸውን አንስተዋል።
ይህ ችግር ስር የሰደደ መሆኑን በማንሳትም፣ በቀላሉ የሚነገር አይደለም ያሉት ባለሙያው፣ አንድ ሰው የሚገዛውን ቦታ ከዚህ በፊት የተሠራ ካርታ መኖር አለመኖሩን አረጋግጦ ለመግዛት እንኳን ቢሮክራሲው ሰፊ በመሆኑና ብዙ መጉላላት ስላለው ይህን የሚያደርግ አካል የለም ነው ያሉት።
የከተማዋ የመሬት አስተዳደር ሕጋዊ አካል ባለበት ችግር የተነሳ ባለሙያዎች መሬት በሚሸነሽኑበት ጊዜም ከባለሙያ የማይጠበቅ ሥራ ይሠራሉ። በዚህም ልኬቱን በማዛባት መሬት በማትረፍ ለራሳቸው ይሸጣሉ በማለት ነዋሪዎች ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ከመሬት ጋር ተያይዞ ባሉ ውስብስበ ችግሮች እስከ አሁንም ተደራጅተው የቤት መሥሪያ ቦታ የሚጠብቁ ብዙዎች ለረዥም ጊዜ ቦታውን ማግኘት እንዳልቻሉ ነው የተናገሩት።
በሌላም በኩል ነዋሪዎቹ በርካታ የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሉብን ብለዋል። ለአብነት ብለውም ለወጣቶች የሚመጣ ፈንድ የነበረ ቢሆንም ይህ ግን ለወጣቶች ሳይደርስ በአመራሮች እጅ ገብቶ ይቀራል ሲሉ ነው ያነሱት።
እንዲሁም ወጣቶች የራሳቸውን አዲስ የሥራ ፈጠራ ሐሳብ ይዘው ለሚመለከተው አካል ሲያቀርቡ፣ የተሰየመው ሕጋዊ አካል ወጣቶች ያቀረቡትን ሥራ አዋጭነት ከተረዳ በኋላ ለራሱ ሰው አሳልፎ በመስጠት ብዙ ወጣቶች በደል እንደተፈጸመባቸው አንስተዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞም የጥቃቅንና አነስተኛ አደራጅ አካል ሰፊ ችግር አለበት ነው ያሉት።
የአርሲ ዴራ ከተማ ከንቲባ ኑራ ሁሴን ከከተማዋ ነዋሪዎች በቀረቡ ቅሬታዎች ዙሪያ ለአዲስ ማለዳ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በከተማችን ካርታ በካርታ ላይ መስጠት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ብዙ አሉ ሲሉ ተናግረዋል።
ሆኖም ከችግሮች ውስጥ በተለይም በካርታ ላይ ካርታ መስጠትን በተመለከተ የተፈቱ መኖራቸውን በመጥቀስ፣ ገና ያልተፈቱም አሉ ነው ያሉት።
ለከተማ አስተዳደሩ ቅሬታዎች ይቀርባሉ ሲሉ የገለጹት ከንቲባው፣ ‹‹ሆኖም ከሚመለከተው አካል ጋር ሆነን እንፈታለን። በዚህ ዓመት ግን በካርታ ላይ ካርታ የተሠራ ወንጀል የለም።›› ብለዋል።
‹‹ከእነዚህ ችግሮች ብዙዎቹ ባለፉት ዓመታት የተፈጠሩ ናቸው። ያልተፈቱትን ለመፍታትም እየተሄደበት ነው›› ካሉ በኋላ፣ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን ችግሮች እየቀነሱ መሆኑን ተናግረዋል።
ለወጣቶች የሚቀርበውን ፈንድ በተመለከተ በሰጡት ምላሽ ‹‹የሚቀርብ ብዙ ፈንድ የለንም። የሚመጣውን ደግሞ ለተደራጁና መስፈርት ለሚያሟሉ እየሰጠን ነው። ከዚህ ውጪ ቅሬታ ያለው በአካል መጥቶ ማቅረብ ይችላል።›› ብለዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015


