በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ላለፉት 22 ዓመታት በመድረክ ላይ የቆየው ‹ባቢሎን በሳሎን› ቴአትር ከመድረክ ሊወርድ መሆኑ ተነገረ።
በተመልካች ብዛትና በገቢ በቴአትር ቤቱ ሪከርድ ይዞ የሚገኘው ይኸው ቴአትር፣ የፊታችን እሁድ መስከረም 29/2015 ለመጨረሻ ጊዜ ለዕይታ ይቀርባል ተብሏል።
በውድነህ ክፍሌ ተደርሶ በተስፋዬ ገብረሀና ዝግጅቱ የተከናወነው ትያትሩ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ለመድረክ የበቃው በ1992 ግንቦት ወር ላይ እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ። የተለያዩ ተዋንያንና ተዋንያትም ባለፉት 22 ዓመታት ውስጥ ተቀያይረው ተውነዉበታል።
የቴአትሩ ደራሲ ውድነህ ክፍሌ በማኅበራዊ ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ መሠረት፣ ቴአትሩ በፍቅሩ አምሳሉ አዘጋጅነት እና በትእዛዙ ከበደ ተርጓሚነት በኦሮሚኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ ከዓመት ላላነሰ ጊዜ በኦሮሚያ የባህል ማእከል ለዕይታ ቀርቧል።
‹ባቢሎን በሳሎን› በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክም ረጅም እድሜ ያስቆጠረ ሥራ ሆኖ ተመዝግቧል። አሁንም ተመልካቾች ያሉት ቴአትሩ፣ አሁን ላይ ከመድረክ ለምን እንደሚወርድ ግን በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም።
ደራሲው ውድነህ ክፍሌም በገጹ ላይ ይህን በሚመለከት ቴአትር ቤቱ ሲያሳውቀው እንደሚናገር ጠቅሶ፣ በሥራው ለተሳተፉ ሁሉ ምስጋናውን አቅርቧል። በዚህም ‹‹መድረክን፣ ያከበራችሁን ተመልካችን አክብራችሁ እስከዛሬዋ ሰዓት ዋጋ ለከፈላችሁ ሙያተኞች ላቅ ያለ አክብሮት አለኝ። ተስፋ ሳትቆርጡብን ሙያውን ላበረታታችሁ የቴአትር ተመልካቾች ክብረት ይስጥልን። ወደፊት በአዳዲስ ሥራ እንገናኛለን።›› ሲል መልዕክቱን አስፍሯል።
በተያያዘም ባሳለፍነው መስከረም 25 ቀን 2015 ‹የቴዎድሮስ ራዕይ› የተሰኘው ሙዚቃዊ ተውኔት ከመድረክ ተሰናብቷል። በጸሐፌ ተውኔት፣ አዘጋጅ እና ገጣሚ ጌትነት እንየው ተጽፎ የተዘጋጀው ይኸው ሙዚቃዊ ቴአትር፣ አንጋፋ የቴአትር ባለሞያዎችና የጥበቡ አፍቃሪያን በተገኙበት ነው በድምቀት ከመድረክ የተሰናበተው።
ቴአትር ቤቱ ከጥቅምት 2/2015 ጀምሮ በየሳምንቱ ረቡዕ የሚቀርብ ‹የአና ማስታወሻ› የተሰኘ ቴአትር እንደሚያቀርብ አስታውቋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015


