ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ኹለት ዓመታት 300 ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ነዋይ እንደሚያፈስ አስታወቀ

0
741

• እስካሁን 200 ሺሕ ደንበኞች አፍርቷል

በኢትዮጵያ የቴሌኮምዩኒኬሽን ዘርፍ የመጀመሪያው የግል ቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሰጪ የሆነው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ በሚቀጥሉት ኹለት ዓመታት እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር መዋዕለ ነዋይ ፈሰስ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንግሥት የቴሌኮም አገልግሎትን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረጉን ተከትሎ ጨረታውን ያሸነፈው ‹ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ› የተሰኘው የተለያዩ የውጪ ኩባንያዎች በጋራ የመሠረቱት ተቋም ሲሆን፣ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ አገልግሎቱን ለመጀመር ለኢትዮጵያ መንግሥት 850 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

በሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር አሁን ላይ አዲስ አበባን ጨምሮ በ11 ከተሞች የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን፣ አገር ዐቀፍ አገልግሎቱን ባሳለፍነው መስከረም 26/2015 ይፋ አድርጓል። ኩባንያው አገልግሎቱን ይፋ ባደረገበት ወቅት በሚቀጥሉት ኹለት ዓመታት ከ200 እስከ 300 ሚሊዮን ዶላር በዘርፉ ላይ መዋዕለ ነዋይ እንደሚያፈስ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዋር ሱሳ ተናግረዋል።

ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፤ ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የተቀላጠፈ የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት በቀሪ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አገልግሎቱን ለማቅረብ ኢንቨስት ማድረጉን እንደሚቀጥል ጠቁመዋል። ኩባንያው የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎቱን መስጠት የጀመረው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት፣ የመሠረተ ልማት በመጋራት መሆኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

በስምምነቱ መሠረት ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ኢትዮ ቴሌኮምን ታወርና ፋይበር በኪራይ መጠቀሙን አንዋር ገለጸዋል። ኩባንያው አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊ የሆነ የመሠረተ ልማት ኪራይ ውል ከኢትዮ ቴሌኮም በተጨማሪ እንደ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር ፈጽሟል።

የሳፋሪኮም ኔትወርክ በአሁኑ ጊዜ በድሬዳዋ፣ ሐረር፣ ሐረማያ፣ አዳማ፣ ባህር ዳር፣ ቢሾፍቱ፣ ሞጆ፣ ደብረ ብርሃን፣ አወዳይ፣ ጎንደር እና አዲስ አበባ የሚገኝ ሲሆን፣ አገራዊ ኔትወርክ ማስጀመሪያው ቀጥሎ እስከ ሚያዝያ 2015 ድረስ ተጨማሪ 14 ከተሞችን እንደሚያዳርስም አስታውቋል። ኩባንያው የጥሪ ማእከልን ያቋቋመ ሲሆን፣ የጥሪ ማእከል አገልግሎቱን በአምስት ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ ኦሮሚኛ፣ ሱማሊኛ፣ ትግሪኛ እና እንግሊዝኛ ለደንበኞቹ አገልግሎት እንደሚሰጥ አስታውቋል።

ኩባንያው ከቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎቶች በተጨማሪ በሞባይል ፋይናንስ የመሳተፍ ፍላጎት ያለው ሲሆን፣ በኬኒያ ታዋቂ የሆነውን “ኤም ፔሳ” የተሰኘው የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት በኢትዮጵያ ለመጀመር ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥያቄ ማቅረቡ ተነስቷል። ኩባንያው ሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት ፈቃድ ካገኘ፣ የሞባይል ፋይናንስ አገልግሎት እንደሚያስጀምር ተጠቁሟል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም ሳፋሪኮም አገር ዐቀፍ የቴሌኮም አገልግሎት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩንም ባከናወነበት መድረክ፣ ለኩባንያው በሞባይል የገንዘብ ዝውውር እንዲያከናውን መፈቀዱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ አስታውቀዋል።

ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ዐስር ዓመታት ከ8 ቢሊዮን ዶላር በላይ መዋዕለ ነዋይ የሚያፈስ ሲሆን፣ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ሳፋሪኮም ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ቮዳፎን ግሩፕ፣ ቮዳኮም ግሩፕ፣ ሱሚቶሞ ኮርፖሬሽን እና ብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት ያዋቀሩት ጥምረት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በሐምሌ 2013 ኹለተኛውን ሁለገብ የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለዚሁ ጥምረት ሰጥቶ አገልግሎት መጀመሩ ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here