ያልተመዘገቡት 13 ሚሊዮን ተማሪዎች!

0
1944

እድገትን በተጠማች አገር ሰላም መሠረታዊ የመሆኑን ያህል ትምህርትም ከፍተኛ ድርሻ አለው። ሠለጠነ በሚባለውና ዓለም እንደ አንድ መንደር ሆና በምትታይበት በዚህ ጊዜ፣ የተማረ ኃይል አገርን በብዙና በተለያየ መንገድ፣ በከፍተኛ መጠን ሊያገለግል እንደሚችልም አያጠራጥርም።

ጦርነት እና አለመረጋጋት በነገሠባት የአሁኗ ኢትዮጵያ፤ ከታጎሉ ጉዳዮች መካከል ትምህርት አንዱና ዋነኛው ነው። ባለፉት ኹለት ዓመታትና ከዛም በላይ እንደ አዲስ ትምህርት ለመጀመር መመዝገብ ሲኖርባቸው ያልተመዘገቡ እንዲሁም ደግሞ ከትምህርታቸው ተፈናቅለው ወጥተው ዳግም ያልተመለሱ ልጆች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው። የፈረሱና ያልተገነቡ ትምህርት ቤቶች በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ናቸው።

ይህ ዛሬ ላይ ነባራዊ ክስተት ብቻ የሚመስል ጉዳይ ለነገ ከክስተትና እውነትም በላይ ከባድ የቤት ሥራ እንደሚሆን አያጠራጥርም። ይህም በአንድ አገር ማኅበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዎና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሚኖረው ተጽእኖ በቀላል የሚገመት አይሆንም። ይህንን በሚመለከት ባለታሪኮችንና ባለሞያዎችን በማናገር፣ ዘገባዎችንም በማጣቀስ የአዲስ ማለዳው ሳሙኤል ታዴ ተከታዩን ሐተታ ዘ ማለዳ አሰናድቷል።

የ12 ዓመት ታዳጊዋ ምንትዋብ በጋሻው (የአባቷ ሥም የተቀየረ) ከሰሜን ወሎ ዞን ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣቸው። ምክንያቱ ደግሞ በጦርነቱ የተነሳ በባለፈው ዓመት አባቷን ስላጣችና እዚያ ለመኖር አስቸጋሪ ሁኔታዎች በመኖራቸው ነው።

ምንተዋብ ባለፈው ዓመት በ2014 የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የነበረች ሲሆን፣ ትምህርት ላይ የነበሩ ሌሎች ታናናሽና ታላቅ እህት ወንድሞችም ነበሯት። ይሁን እንጂ በአባታቸው ሞት ምክንያት ቤተሰባቸው እንደ ወትሮው መቀጠል አልቻለም።

ትልቁና የመጀመሪያው ወንድ ልጅ ከስምንተኛ ክፍል አቋርጦ የቀን ሥራ እየሠራ ለመኖር ወደ ደሴ ገብቷል። የእነምንትዋብ እናት ቀሪ ኹለት ልጆቻቸውን ይዘው በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ነው የሚኖሩት። ምንትዋብ ደግሞ ከእናቷ እህት (አክስቷ) ጋር ለመኖር ወደ አዲስ አበባ መጥታለች። አዲስ አበባ የመጣችው ትምህርቷን ለመቀጠልና የተሻለ ኑሮ ለመኖር አይደለም።

አክስቷ አነስተኛ ቤት ውስጥ ‹‹ኑ ቡና ጠጡ›› ስለምትሠራ እዚያ ስኒ በማጠብ እና አንዳንድ ሥራዎችን በማገዝ ለመኖር በማሰብ ነው።

ታዲያ የትምህርቷስ ነገር ለሚለው ደግሞ ባለፈው ዓመት አቋርጣው የቆየችውን ትምህርት ዘንድሮም እንደተቋረጠ ይከርምና በሚቀጥለው ዓመት ከተወለደችበት አካባቢ አምስተኛ ክፍል ስለመድረሷ ማስረጃ በማምጣት አዲስ አበባ በማታ ለመማር ታስቧል።

‹‹ይህም በእኔ ጥረት የሚሆን እንጂ የእሷ የልጅነት ህልም የተሟጠጠው አባቷ ሲሞትና ቤተሰባቸው እንዳልነበረ ሲሆን ነው።›› ትላለች፤ ወጣቷ የምንትዋብ አክስት።

በምንትዋብ ፊት ስለጦርነት ማውራት የተከለከለ ነው። ያደገችበትን ሰፈር መጥራትም ሆነ ስለትምህርት ቆይታዋ፣ በጥቅሉ ከዚህ በፊት ስለነበራት አኗኗርም እንዲሁ በማንሳት ማስታወስ አይቻልም። ይህ ከሆነ በድንገት እንባዋ ይፈሳል። አንዴ ማልቀስ ከጀመረች የሚያስቆማት የለም።

ስለዚህም አክስቷ፣ የምንትዋብ ሕይወት የብዙ ታዳጊዎችን ሕይወት እንደሚወክል በመግለጽ፣ የእሷ እንዲህ መሆን ከእሷ በላይ እኔን ነው እየጎዳኝ ያለው ትላለች።

‹‹እንደጓደኞቿ ቀን ቀን በስነ ሥርዓት መማር ነበረባት። አባቷን አጥታለች፣ ቤተሰባቸው ፈርሷል። ኹለት ዓመት ትምህርት አቋርጣለች። በዚህ እድሜዋም በማታ መርሃ ግብር እንድትማር ማሰባችን አንገት የሚያስደፋ ነው። በእርግጥ በሕይወት የሌሉ ሰዎችና መማር ያልቻሉ ሕጻናትም በርካታ በመሆናቸው መኖሯንና የማታም ቢሆን ብትማር እድል እንደሆነ ላስረዳት እየሞከርኩኝ ነው።›› ትላለች የምንትዋብ አክስት።

ሆኖም በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ የምንትዋብ ኑሮ ሳይታሰብ ወደ አዲስ አበባ ተቀይሯል። የእሷ እኩዮች በመጪው ዓመት ሰባተኛ ክፍል ሲደርሱ እሷ አምስተኛ ክፍል እሱንም በማታ ለመማር ሙከራ ታደርጋለች። በዚህ ሁኔታ የምንትዋብ የነገ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል አክስቷም፣ ራሷ ምንትዋብም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ መረዳት ይቻላል።

በተለይ በሰሜኑ ጦርነት የተነሳ የምንትዋብ ዓይነት ዕጣ ፈንታ የገጠማቸው፣ አለፍ ሲልም ወላጆቻቸውን አጥተው ለአሳዳጊ ድርጅቶች የተሰጡ፣ አካላዊና ጾታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው፣ የሞቱና ተፈናቅለው የት እንዳሉ የማይታወቁ፣ ባሉበት ሆነውም መማር የማይችሉ እልፍ ታዳጊዎች መኖራቸው በሰፊው ሲነገር የቆየ ጉዳይ ነው።

ትምህርት የተሻለ አገርን ለመመሥረት ካለው አስተማማኝ መሣሪያነት የተነሳ፣ ብዙ አገራት ነጻ የመማር እድል ከመስጠት ጀምሮ ትውልዳቸውን ለማስተማር ብዙ ሲደክሙ ይታያል። በተቃራኒው ደግሞ ቀላል በማይባሉ አገራት ትምህርት ለሥሙ በሚባል ሁኔታ ሥምን ለመጻፍ ወይም ለማንበብና ለመጻፍ፣ ከፍ ሲልም ለመቀጠር በሚመስል ዓላማ በወረደ ጥራት ሲሰጥም ይታያል።

ሆኖም በአንድ አገር የተሻለ የትምህርት ሥርዓት ለመዘርጋት የተዋጣለት ስርዓተ ትምህርት፣ ሰላም፣ በቂ ጥሪት እና ለክትትል የሚሆን ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።

ድህነት እና ድንቁርና የጀርባ አጥንቷ ሆኖ በሽብር በምትታወሰዋ አፍሪካ ግን፣ የትምህርት ነገር በየዓመቱ እየባሰ በሚሄድ ሁኔታ የአኅጉሪቱ ውድቀት የሆነ ነው የሚመስለው። በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ታዳጊዎች መማር ሳይችሉ ሲቀር ወይም የጀመሩትን ትምህርት ለማቋረጥ ተገደዱ የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ ይስተዋላል።

የ2015 የትምህርት ዘመን ሲጀመር አብረው ያልጀመሩ በርካታ ትምህርት ቤቶች መኖራቸው ይታወቃል። በጦርነትና ግጭቶች የተነሳም የበርካታ ትምህርት ቤቶች መውደም፣ የጸጥታ ችግር፣ የወላጆች መፈናቀል እና ልጆቻቸውን ለማስተማር አቅም ማጣት እንዲሁም ድርቅ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በርካታ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደሚያደርጋቸው ነው የሚገለጸው።

አዲስ ማለዳ ባለፈው ዓመት ሕወሓት ከምሥራቅ አማራ አካባቢዎች ለቆ በወጣበት ወቅት በቦታው ተዘዋውራ ባገኘችው መረጃ መሠረት፣ ሕወሓት ወረራ ባደረገባቸው ስምንት ዞኖችና 87 ወረዳዎች 1 ሺሕ 145 ትምህርት ተቋማት ውድመትና ዘረፋ ተካሂዶባቸዋል።

በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመማሪያ ሕንጻዎች፣ ቤተ ሙከራዎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የትምህርት ግብዓቶችና ሌሎች ቁሳቁሶች በድምሩ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ውድመት ደርሶባቸዋል።

በዚህ የተነሳም ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል እጅግ ፈታኝ ሁኔታ ያጋጠማቸው በመሆኑ በ2014 የትምህርት ዘመን በአማራ ክልል ብቻ ኹለት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች የዚህ ችግር ሰለባ ሆነው ከትምህርት ገበታ እርቀዋል ሲል ክልሉ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

እነዚህ ትምህርት ቤቶች በፍጥነት መጠገንና ወደነበሩበት ሁኔታ መመለስ መቻል ፈታኝ መሆኑን መንግሥትም በተደጋጋሚ የገለጸ ሲሆን፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎችም እንዲሁ ባለፈው የትምህርት ዘመን ብቻ በርካታ ተማሪዎች ትምህርት ሳያገኙ ከርመዋል።

13 ሚሊዮን ተማሪዎች!

የዘንድሮው የትምህርት ዘመን አዲሱ ስርዓተ ትምህርት የሚተገበርበት ነው ቢባልም፣ እስካሁን ያላጋጠመና ለትምህርት ዘመኑ በጣም ከባድ ነበር ከተባለው ከ2014 የሚብስ በሚመስል ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ለመማር ያልተመዘገቡበት ዓመትም ነው።

ትምህርት ሚኒስቴር ከቀናት በፊት ይፋ እንዳደረገው ለ2015 የትምህርት ዘመን በአገሪቱ 29 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመዝገብ ታልሞ የነበረ ቢሆንም፣ ሊመዘገቡ የቻሉት ግን 16 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸው።

ይህም በዓመቱ ይመዘገባሉ ተብሎ ከታቀደው 55 ነጥብ 6 በመቶ ብቻ እንደሆነ ታውቋል። ቀሪ 45 በመቶ ገደማ መማር የሚችሉ ተማሪዎች ለመማር የሚያስችላቸውን ምዝገባ አላከናወኑም። ይህንም እንደ አገር ሲታይ በጣም ትልቅ ቁጥርና ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ ነው ብለውታል ብዙዎች።

16 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተማሪዎች ብቻ ናቸው የተመዘገቡት የተባለውም እስከ ጳጉሜ 5/2014 ሲሆን፣ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት እስከ መስከረም 20/2015 ተጨማሪ ተማሪዎችን ሊመዘግቡ ይችላሉ የሚል ተስፋ ተቀምጦ ነበር።

ሆኖም አዲስ ማለዳ በታሰቡት 20 ቀናት ውስጥ ምን ያህል ተጨማሪ ተማሪዎች ተመዘገቡ የሚለውን ለማወቅ የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮምዩኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አመለወርቅ ህዝቅኤልን ደውላ ጠይቃለች። ሥራ አስፈጻሚዋ ጥያቄውን ከተቀበሉ በኋላ የሚመለከተው አካል መረጃ እንዲሰጥ አደርጋለሁ ቢሉም ተግባራዊ ባለማድረጋቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።

ጦርነት ድጋሜ ባገረሽባቸው አፋርና አማራ ክልል አካባቢዎች፣ በኦሮሚያ ክልል በወለጋ እንዲሁም በሌሎች በተለይ የጸጥታ ችግር ባለባቸው የኢትዮጵያ ክፍሎች የተማሪዎች ምዝገባ አልተከናወነም።

13 ሚሊዮን የብዙ አገራት ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር ነው። በኢትዮጵያ መማር እየቻሉ ሳይማሩ የሚከርሙ 13 ሚሊዮን ገደማ ታዳጊዎች መኖራቸው በነገ የአገሪቱ እጣ ፈንታ ላይ የሚያስከትለው መዘዝ ቀላል እንደማይሆን እሙን ነው።

ማኅበራዊ ቀውስ

የሥነ ልቦና ምሁራን እንደሚሉት የትምህርት ሥርዓት መዳከም የሚያስከትለው ማኅበራዊ ቀውስ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም። ባልተማረ ማኅበረሰብ ዘንድ የስብዕና ቀውስ የተለመደ ክስተት ይሆናል። ይህም ከዚህ በፊት የነበሩ መልካም እሴቶች እንዲጠፉና በአጠቃላይም በሕግና በሥርዓት መመራት ቀርቶ፣ ከመጠን በላይ የተዳከመ ማኅበረሰብ እንዲፈጠር ያደርጋል።

በዚህ ወቅም በየከተሞች ዐስር ዓመት ያልሞላቸው በርካታ ሕጻናት የክብደት መለኪያ ሚዛን ይዘው ሲንከራተቱ ይታያል።

ይህ ድርጊት በአገሪቱ ላለው ግጭት፣ ድህነት እና የቤተሰብ ውድቀት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፣ ታዳጊዎች ትምህርት ቤት ገብተው የነገ ችግር ፈቺ መሆን ሲገባቸው ዛሬ በዚህ መልኩ ችግር ሲፈራረቅባቸው መታየቱ ያለውን የትምህርት አፈጻጸም ዝቅተኛነት የሚገልጽ መሆኑም ይነሳል።

በጥቅሉ የተማረ ማኅበረሰብ ከድህነትና ድንቁርና የመላቀቅ እድሉን ስለሚያገኝ፣ በራሱ የሚተማመን፣ ሥልጡን፣ ፍትሃዊና የተረጋጋ ጤናማ ማኅበረሰብ እንዲሆን ያስችለዋል የሚሉ ጠንካራ መላምቶች አሉ።

ኢኮኖሚያዊ ቀውስ

ለአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ እድገት ወሳኙ ሚና የሚጫወተው እውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ሲኖር እንደሆነ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይመሰክራሉ። ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች የሠለጠነ የሰው ኃይል እንደሚያስፈልጋቸው እንዲሁም በየጊዜው በፈጠራ የታገዘ የኢኮኖሚ ግስጋሴ መኖር እንዳለበት ይታመናል።

ሆኖም የአንዲት አገር ኢኮኖሚ ይበልጥ ዋጋ የሚኖረው እኩልና ፍትሃዊ የትምህርት እድል ባገኙ ዜጎቿ የተገነባ ሲሆን እንደሆነም የዘርፉ ምሁራን እሳቤ ነው።

በአንድ አካባቢ የሚኖር ማኅበረሰብ ወይም በማንነቱ አልያም በጾታና በሌሎች ምክንያቶች የትምህርት እድል ተነፍጎት፣ ገሚሱ ባገኘው የተሻለ የትምህርት እድል የአገር ኢኮኖሚ ሊገነባ እንደማይችል ነው የሚጠቀሰው። ይህም የተማረው ቢገነባም ያልተማረው ክፍል የተገነባውን ከማፍርስ ወደኋላ እንደማይል ስለሚታመን ነው።

በግልጽ እንደሚታየው የተሻለ የትምህርት ሥርዓት ዘርግተው በየዓመቱ በርካታ ወጣቶችን አሠልጥነው ወደ ሥራ የሚያሰማሩ አገራት፣ ከዚህ በተቃራኒ ደካማ የትምህርት ሥርዓትና ዝቅተኛ ተደራሽነት ካለባቸው አገራት በተሻለ ፈጣን ምጣኔ ሀብታዊ እድገት እያስመዘገቡ ነው።

በዚህ የተነሳም በርካታ አገራት ለትምህርት ዘርፉ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ ፈስስ ሲያደርጉ ይስተዋላል።

ስለሆነም ማንኛውም ታዳጊ የመማር መብት ያለው መሆኑ የማያሻማ ጉዳይ ቢሆንም፣ ያልተማረ ማኅበረሰብ የበዛባት አገር ነገም እንኳንስ ትምህርት ለማስተማር፣ በልቶ ለማደርና ወጥቶ ለመግባት የማይቻልበት ሁኔታ ስለሚፈጥር መማር ላልቻሉ ወገኖች ትልቅ ትኩረት መስጠት እንደሚገባ በርካቶች ያሳስባሉ።

ፖለቲካዊ ቀውስ

ባልተማረ ማኅበረሰብ ውስጥ ዴሞክራሲ በቀላሉ ሊያድግ እንደማይችል ነው የሚታሰበው። ስለዚህም ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በስፋት ይጣሳሉ። የዳበረ የፖለቲካ ባህልም ላይኖር ይችላል።

ትምህርት የተንሸዋረረ የፖለቲካ እሳቤን ለማስተካከል ቁልፍ መሣሪያ መሆኑ ይገለጻል። ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው እንዲወጡ፣ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር እንዲኖር በጥቅሉ የሕግ የበላይነት ገዥ እንዲሆንና ፍትህ እንዲሰፍን ትምህርት አይተኬ ሚና እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ይህ ሳይሆን ቀርቶ በርካታ ዜጎች መማር ባልቻሉበት ሁኔታ ውስጥ ሊኖር የሚችለው አስተዳደራዊ ሥርዓት ግን አግላይ እና ፈላጭ ቆራጭ ሊሆን እንደሚችል እምብዛም አያጠራጥርም።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር ሰለሞን በላይ (ዶ/ር) ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ አሁን የሚታየው አጠቃላይ ችግርም የኢትዮጵያ ችግር ነጸብራቅ ነው የሚል ሐሳብ አላቸው።

‹‹ትምህርት ለአንድ አገር ዋና ነገር ነውና አንድ አፍታ ቁጭ ብሎ በመነጋገር መሠረታዊ ችግሮችን መፍታት ያስፈልጋል›› ነው ያሉት።

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች መማር አለመቻላቸውም አገሪቱ አስቀድሞ በትምህርት ዘርፉ መክሰር የደረሰባት ሌላ ኪሳራ መሆኑን በማውሳት፣ ይህም ቀጣይ የሚመጣውን ትውልድ የእድገት እና የሰላም አቅጣጫውን የሚያሳጣ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።

ብዙ የትምህርት ተቋማት ከአቅም በታች መሆናቸውን የአገሪቱ የትምህርት ስርዓት ከቆመ ቀርነት ተላቆ በየጊዜው ተደራሽነቱንና አቅሙን የሚያሳድግ፣ ለማኅበረሰቡ ችግሮችም ምላሽ የሚሰጥ መሆን እንዳለበት ምሁራን ይገልጻሉ።

ኢትዮጵያ ከሰሀራ በታች ካሉ አገሮች የወረደ የከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነት እንዳላት ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። በዚህ ዓመትም በትምህርት ዓመቱ መጀመሪያ ለመማር ከተመዘገቡት ከ16 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ውስጥም ብዙዎች ሊያቋርጡ እንደሚችል የሚገመት ነው።

በኹለት ዓመታት ውስጥ ብቻ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች መውደማቸው ይታወቃል። ለዚህም መንግሥት ትምህርት ቤቶችን በተሻለ ጥራት እገነባለሁ በሚል እንቅስቃሴ በተለይ በአፋርና በአማራ ክልል ጦርነቱ ጉዳት ባደረሰባቸው አካባቢዎች የትምህርት ተቋማቱን በድጋሜ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ ይታያል።

ይሁን እንጂ አሁን ባለው አገራዊ ሁኔታ የመሠረት ድንጋይ ከማስቀመጥ ባለፈ ትምህርት ቤቶች በቶሎ ተገንብተው ለአገልግሎት ይደርሳሉ ወይ የሚለው የብዙ ሰዎች ስጋት ነው።

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በጦርነት እና በተለያዩ ግጭቶች በአፋር፣ አማራ፣ ቤንሻንጉል፣ ኦሮሚያ እና ደቡብ ክልሎች የወደሙ ከ1 ሺሕ 300 በላይ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት ከ80 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸው አይዘነጋም።

ይህም በአገሪቱ ካለው የኢኮኖሚ ድቀት አንጻር 80 ቢሊዮን ብር በጀት ይዞ የወደሙ ትምህርት ቤቶች በቀላሉ ተገንብተው ለአገልግሎት ይደርሳሉ የሚለውን ተስፋ የሚያጨልም እንደሆነ ይነሳል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናትን ጉዳይ የሚከታተለው ክፍል ዩኒሴፍ በቅርቡ ይፋ እንዳደረገው፣ በዓለም ላይ እድሜያቸው እስከ ዐስር ዓመት የሆኑ ሕጻናት መካከል ወደ ኹለት ሦስተኛ የሚጠጉት ቀላል ጽሑፍ እንኳ ማንበብ እና መረዳት እንደማይችሉ ናቸው። አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደም ዓለም ዐቀፋዊ የትምህርት ኪሳራና የትውልድ ጥፋት ሊከተል እንደሚችል ተቋሙ አስታውቋል።

ቀድሞውንም የተዳከመውን የትምህርት ስርዓት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰት ችግሩን በዓለም አቀፍ ደረጃ አባብሶታል ነው ያለው። ሕጻናት መሠረታዊ የማንበብ እና የሒሳብ ክህሎቶች እንዲኖራቸውና አቅማቸውን እንዲጠቀሙ ለማድረግ ዓለም ዐቀፍ ጥረት እንዲደረግም ጥሪ አቅርቧል።

ኹሉም ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ ማድረግ፣ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት እንዲልኩ ማድረግ፣ የመማር ማስተማር ሥራዎችን በመደበኛነት መገምገም፣ ለትምህርት ቅድሚያ መስጠት፣ ሕጻናት ለመማር ዝግጁ እንዲሆኑ የሥነ-ልቦናና ማኅበራዊ ጤና ደኅንነትን ማዳበር የሚሉ እርምጃዎችን መንግሥታት እንዲወስዱም ይፈለጋል።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከዐስር ስድስት የሚጠጉ ሕጻናት በድህነት ምክንያት ትምህርት በአግባቡ የማያገኙ እንደሆኑና በዐስር ዓመት እድሜያቸው ቀላል ፅሁፍ ማንበብ እና መረዳት አይችሉም ሲል ነው ዩኒሴፍ ያስገነዘበው።

መማር ተስፋና እድል ነው፤ አስፈላጊም ነው። ትምህርት የወደፊት እጣ ፈንታቸውን ይወስናል። ልጆችን ለትምህርት ማስመዝገብ በታዳጊዎች ሕይወት ውስጥ ዋና ምዕራፍ ነው። ከጀመሩ በኋላም እንዳያቋርጡ ተከታታይ እገዛ ማድረግ ይገባል። ደግሞ መብታቸው ነው ይላል ተቋሙ።

ባለፈው ዓመት 2014 የትምህርት ዘመን ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች በኢትዮጵያ በተፈጠረው ሰብአዊ ቀውስ የተነሳ ከትምህርት ውጭ መክረማቸውን ዩኒሴፍ ይጠቁማል።

እንዲሁም በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከኹለት ሚሊዮን የሚልቁ ሕጻናት በፅኑ ድህነት (extreme poverty) ውስጥ ስለሚኖሩ፤ የመማር መብታቸውን አሰልቺና በዝባዥ ለሆኑ የጉልበት ሥራ አሳልፈው ይሰጣሉ ነው ያለው።

ሥማቸውን እንዲጠቀስ ፈቃደኛ ያልሆኑና በደብረ ብርሃን ከተማ ባሉ መጠለያ ጣቢዎች በአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅት አማካኝነት በተፈናቃዮች በአስተባባሪነት የሚሠሩ ግለሰብ፣ በመጠለያ ጣቢያዎች በርካታ ታዳጊዎች እንደሚኖሩ አንስተው ብዙዎች ስምንተኛ ክፍል ሆነው እንኳን በአማርኛ ሥማቸውን የማይጽፉ ናቸው ይላሉ።

ይህ የሆነው ቀድሞ በኖሩበት አካባቢ በተደረገ ፖለቲካዊ ጫና መሆኑን በመጥቀስ አሁን ላይ ታዳጊዎችን ለማስተማር እየተደረገ ያለውን ጥረት ጠቁመዋል።

በዚህም ልጆቹን ድንኳን ውስጥ ለማስተማር የታቀደ ሲሆን፣ ይህ ግን ከመማሪያ ቁሳቁሶች ግብአት እስከ አስተማሪ ድረስ ሙሉ ለማድረግ ሰፊ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑና ለተፈናቃዮች ቅድሚያ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ማሟላት ስለሚገባ ልጆች መማር በሚገባቸው ልክ ሊማሩ እንደማይችሉ ነው የተናገሩት።

ቢያንስ ማንበብና መጻፍ እንዳይረሱ እንዲሁም በቀጣይ ሁኔታዎች ተመቻችተው ከመጠለያ ጣቢያዎች የሚወጡበት ጊዜ ሲመጣ ትምህርታቸውን ለመቀጠል እንዲችሉ መሆኑን አንስተዋል።

አገርን የማዘመንና በኹሉ ነገር የማበልፀግ ጅማሮ የሚገኘው በትምህርት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። የወደፊቷ ኢትዮጵያን ለመተንበይ የዛሬውን የትምህርት ሁኔታ መመልከት በቂ ነው የሚሉ አሉ። ትምህርት የሰላም፣ የመቻቻልና የዘላቂ ልማት መሠረት መሆኑም በጽኑ ይታመናል።


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here