ኢሰመኮ የጋምቤላ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞቼ ከክልሉ ከተማ ለቃችሁ ውጡ ተብለዋል አለ

0
529

በጋዜጣው ሪፖርተር

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የጋምቤላ ክልል ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች እና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ከክልሉ ከተማ ለቀው እንዲወጡ ማስፈራራያ እንደደረሳቸው ገለጸ።

ኮሚሽኑ ‹በቡድን ሆነው የመጡ ሰዎች› ያላቸው አካላት መስከረም 25/2015 ወደ ኢሰመኮ ጋምቤላ ጽሕፈት ቤት በመግባት የተለያዩ የጥፋት ድርጊቶችን መፈጸማቸውንና በኮሚሽኑ ሠራተኞች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ማድረሳቸውን አስታውቋል።

‹በቡድን ሆነው የመጡ ሰዎች› የተባሉት አካላት በጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ የሚገኙ የተለያዩ የሰብዓዊ መብቶች ሥራዎችን በሚያከናውኑ ሌሎች ድርጅቶች ላይም ተመሳሳይ ጥፋት አድርሰው ድርጅቶቹ ‹ከከተማው ለቅቀው እንዲወጡ› ማስፈራራታቸውንም ኢሰመኮ መስከረም 26/2015 ባወጣው መግለጫ ገልጿል።

ኮሚሽኑ በመግለጫው በጋምቤላ ከተማ በብሔራዊ ሰብዓዊ መብቶች ተቋም እና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት በክልሉ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል በመሆኑ፤ የፌዴራል እና የክልሉ የጸጥታ አካላት በአፋጣኝ ሊያስቆሙ እንደሚገባ አሳስቧል።

ኢሰመኮ ሰኔ 7/2014 በጋምቤላ ከተማ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ወይም “ሸኔ” እና የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ፤ በጋምቤላ ክልል የጸጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ቡድኖቹ የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አስመልክቶ ያከናወነውን የምርመራ ሪፖርት መስከረም 18/2015 ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ኢሰመኮ ባወጣው ሪፖርት ከሰኔ 7 እስከ 9/2014 በክልሉ ሲቪል ሰዎች ላይ ግድያን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ገልጾ ነበር።

የሪፖርቱን ይፋ መደረግ ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ድረ ገጾች እና መገናኛ ብዙኀን የተሳሳተ፣ አነሳሽ እና ዛቻ ያዘሉ መረጃዎች ሲሰራጩ፣ እንዲሁም በኢሰመኮ ባልደረቦች ላይ ያነጣጠሩ የጥላቻ መልዕክቶች ሲዘዋወሩ መቆየታቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ጉዳዩን ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር መፍታት እንደሚቻል በማመን ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቦ መቆየቱን ገልጿል።

ኮሚሽኑ በክልል የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ያደረገውን የምርምራ ውጤት ይፋ ካደረገ በኋላ፣ የኮሚሽኑን የምርመራ ሪፖርት የክልሉ መንግሥት የማይቀበለው መሆኑን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ መግለጹ የሚታወስ ነው። በኮሚሽኑ ሠራተኞች እና በሌሎች የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ላይ የማስፈራራት ድርጊት የተፈጸመው፣ የክልሉ መንግሥት የኮሚሽኑን የምርመራ ሪፖርት ካጣጣለ በኋላ ነው።

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ኮሚሽኑ በሕገ መንግሥት የተቋቋመ ብሔራዊ የሰብአዊ መብቶች ተቋም መሆኑንና የኮሚሽኑ ሠራተኞችም በአዋጅ የልዩ መብት ጥበቃ የሚደረግላቸው በመሆኑ፣ ‹‹ይህንን ዓይነት በብሔራዊ ሰብዓዊ መብቶች ተቋም እና ሠራተኞች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለውና በክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ምልከታ የሚጥል በመሆኑ የፌዴራል እና የክልሉ መንግሥት ተባብረው በአፋጣኝ እንዲያስቆሙ ኮሚሽኑ በጥብቅ ያሳስባል›› ብለዋል። ኮሚሽነሩ አክለውም ኮሚሽኑ የክትትል እና የምርመራ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙት ጠቁመዋል።

ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 9/2014 የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ተጎጂዎች እና የተጎጂ ቤተሰቦች አሁንም ሟቾች የተቀበሩበትን ቦታ ለማወቅ እና ፍትሕ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ በመሆናቸው የኮሚሽኑ ምክረ ሐሳቦች በአፋጣኝ እንዲተገበሩም ኮሚሽነሩ በድጋሚ አሳስበዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here