የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ200 ሚሊዮን ብር በጀት የከተማውን የመሬት አስተዳደር ሥርዓት በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
በ2010 የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት መስተጓጎሎች እሰካሁን ቢጓተትም፣ በቢሮው በተወሰደ እርምጃ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ እየተሠራ መሆኑን ምክትል ኃላፊ ሀርጋሞ ሀማሞ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በዚህ ፕሮጀክትም ኹሉም የክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮዎች የሚታቀፉ ሲሆን የወረቀትና የመሬት ልኬት መረጃዎች ዲጂታል በሆነ መንገድ እንዲተዳደሩ እንደሚደረግ ታውቋል።
በሦስት የአገር ውስጥና የውጭ አገር ተቋራጮች እየተሠራ በሚገኘው ፕሮጀክት በስምንት ክፍለ ከተሞች የኔትወርክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ የተከናወነ ሲሆን፣ ከእነዚሁ ክፍለ ከተሞች ውስጥም አምስቱ የደንበኞች ወረፋ መጠበቂያ ሥርዓትን ተግባራዊ አድርገዋል። እነዚህ ክፍለ ከተሞችም ንፋስ ስልክ፣ ቂርቆስ፣ አዲስ ከተማ፣ ቦሌ እንዲሁም የካ ክፍለ ከተሞች ናቸው።
ሌሎች ሦስት ክፍለ ከተሞች ደግሞ ተመሳሳይ የደንበኞች ወረፋ መጠበቂያ ሥርዓትን ተግባራዊ ለማድረግ እየሠሩ ሲሆን፣ በቀሪ ሦስት ክፍለ ከተሞች ደግሞ የኔትወርክ መሠረተ ልማት ዝርጋታ በመሠራት ላይ እንደሆነ ሀርጋሞ ገልጸዋል።
ይህ ፕሮጀክት ሲጠቃለልም እያንዳንዱ የቢሮው አገልግሎት በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራርን የሚከተል ሲሆን፣ በክፍለ ከተማ እንዲሁም በከተማ ደረጃ የሚሠሩ እያንዳንዱ ሥራዎች የሚመዘገቡና ማእከላዊ በሆነ የመረጃ ቋት ውስጥ የሚቀመጡ ይሆናል ተብሏል።
ይህን ፕሮጀክት በዚህ የበጀት ዓመት አጋማሽ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ የገለጹት ሀርጋሞ፤ የሶፍተዌር ዲዛይን ሥራው በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ቀሪ ለሆኑ ሥራዎችም የውጪ አገር ምንዛሬ እንደሚያስፈልግና ይህ የውጪ ምንዛሬ በቶሎ ከተገኘ ወደ ሙከራ ሥራ መግባት እንደሚቻልም አክለው ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ እንዲሁም በቦሌ ክፍለ ከተማ መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ውስጥ የመጀመሪያው የመሬት አስተዳደር ሥርዓት እየተዘረጋ ሲሆን፣ ይህም ከተጠናቀቀና የሙከራ ሂደቱ ከተከናወነ በኋላ ወደ ኹሉም ክፍለ ከተሞች የመጨረሻውን ሶፍትዌር የማስገባት ሥራ እንደሚሠራ ለመረዳት ተችሏል።
ምንም እንኳን ፕሮጀክቱ ከተጀመረ አራት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ አብዛኛው ሥራዎች ግን የተሠሩት ባለፈው አንድ ዓመት እንደሆነ ሀርጋሞ ገልጸዋል። የዲጂታል የአሠራር ሥርዓቱን ወደ ሥራ ከማስገባት ጎን ለጎን ብቁና ምስጉን የሰው ኃይል እንዲኖር በማሰብ ቢሯቸው እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በዚሁ መሠረትም ሠራተኞችን የማሠልጠኛ ማንዋሎች የተዘጋጁ ሲሆን፣ በአሰራሩ መሠረት መሥራት የሚችሉና ከብልሹ አሠራር የጸዱ ሠራተኞችን ለማብቃት ይሠራል ብለዋል።
ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ በ2010 የተያዘለት በጀት 200 ሚሊዮን ብር ቢሆንም በአሁናዊ የውጪ ምንዛሬ ንጽጽር መሠረት ይህ የገንዘብ መጠን ከፍ ሊል እንደሚችል የገለጹት ሀርጋሞ፣ ሥራው በታቀደው ልክ የሚሄድ ከሆነ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአምስቱ ክፍለ ከተሞች የተሠሩ የወረፋ መጠበቂያ ሥርዓቶች ከዋናው ሶፍትዌር ጋር ተናብበው መሥራት የሚችሉ ተደርገው የተሠሩ ሲሆን፣ ለደንበኞች የሚሰጡ አገልግሎቶች ፈጣን እንዲሆኑ የሚያስችል መሆኑን ሀርጋሞ ተናግረዋል።
በቅርቡ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ የወረፋ መጠበቂያ እና ዲጂታል የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን በሠራተኞቹ አሠርቶ ማስመረቁ ይታወሳል።
ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015



