የሴቶች የእኩልነትና የመብት እንዲሁም የፍትሕ ጥያቄ እንደቀላል የሚታይበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። አንዳንዶችም የሴቶች የሆኑ እነዚህ ጥያቄዎች ሰብአዊ ጥያቄ ሳይሆኑ እንዲሁ ዘመን ያመጣቸው ጥያቄዎች እንደሆኑ ይቆጥሯቸዋል። ግን ሰብአዊ ጥያቄዎች ናቸው።
ልዩነትና እኩልነትን በተመለከተ የተዛባ ዕይታ እንዳለ አዲስ ማለዳ በተለያየ አጋጣሚ ታዝባለች። ልዩ ልዩ መሆን ከእኩል መሆን ጋር ያለው ተዛምዶ ላይም እንከኖችን ዐይታለች።
ሴትና ወንድ ልዩነት አላቸው። ይህም በተፈጥሮ ከአፈጣጠራቸው የመጣ፣ ለየአንዳንዳቸው የተሰጠ ነው። በዚህም ተፈጥሮአዊ የሆነ የየራሳቸው ድርሻ አላቸው። በሌላ በኩል ደግሞ እኩል ናቸው። አንዳቸው ከሌላቸው አያንሱም፣ አይበልጡም። ኹለቱም ሰው ናቸው። በተፈጥሮ የተሰጣቸው ድርሻም የተለያዩ አደረጋቸው እንጂ የሚያበላልጣቸው አይደለም።
ይህ መሠረታዊና በጉዳዩ ላይ ሐሳብ የሚሰጥ ሁሉም ሰው ሊረዳው የሚገባ ነጥብ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በማኅበረሰብ ውስጥ ሴቶችን የማሳነስ፣ ድርሻቸውን የመናቅና የማቅለል፣ ‹አይችሉም!› ብሎ አቅምና ችሎታቸውን እንዳያሳዩ የሚያደርጉ አመሎች በተደጋጋሚ ታይተዋል፤ ይታያሉም።
ይህ ዕይታ ከወንዶች አንጻር ብቻ የሚነሳ አይደለም። ወይም እንዲህ ያለው ዕይታ ወንዶች ጋር ያለ ነው የሚል አመለካከት እንደውም ከባድ ስህተት ነው። ይልቁንም እንደ ማኅበረሰብ ‹የተለመደ› በመሆኑ ሴቶችም የዚህ አካል መሆናቸው ግልጽ ነው። ‹አንቺ ሴት አይደለሽ!?› እያሉ ሴቶች ማድረግ በሚችሉትና ሊሄዱ በሚፈልጉት መንገድ እንዳይሄዱ በመከልከል ሴቶች ራሳቸው ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ። ‹እንደ ሴት…› በምትለዋ ሐረግ በሚጀምር ሐሳብም ለምሳሌ ‹ምን እንደ ሴት ኩሽና ለኩሽና ትላለህ? ምን እንደ ሴት ትፈራለህ…› ወዘተ የመሰሉ ሴቶችን አሳንሰውና ደካማ አድርገው የሚስሉ ጥቂት አይደሉም።
ከዛም በላይ አንገት መድፋትና አለመናገር ለሴት ልጅ ጥሩ መገለጫ እንደሆነ ተስሏል። በዚህም የተነሳ አንዲት ሴት የሚደርስባት የቃልም ሆነ አካላዊ ጾታዊ ትንኮሳና ጥቃት የሚመዘነው ሴቷ ‹ካደረገችው› ወይም ‹ልታደርግ ከምትችለው› ተብሎ ከታሰበው ግብረ መልስ አንጻር ነው። ‹ለምን ሳቅሽለት! ለምን ዝም አትይውም ነበር! ለምን ፊት ሰጠሽው! ለምን ዋሸሽው!› ወዘተ የሚል ጥያቄ ሲከተል ይስተዋላል።
በተለያየ ጊዜ በመገናኛ ብዙኀን በይፋ ወጥተው በተሰሙና በሴቶች ላይ በደረሱ ጥቃቶች ዙሪያ እነዚህ ጥያቄዎች ሲነሱ ይስተዋላል። ‹አሲድ ደፋባት› ከሚለው ዜና ስር ‹የደፋባት ስለከዳችው ነው› የሚል አስተያየት ወይም ምላሽ ይቀርባል። ‹ተደፈረች› ለሚለውም ‹አለባበሷና ምሽት ውጪ መገኘቷ› የሚል ለጥቃት አድራሽ ከለላ የሚመስል ሐሳብ ይታከልበታል።
እነዚህ ሁሉ ቀላል የሚመስሉና በየጊዜው ሲነሱ ‹ደግሞ እነዚህ ፌሚኒስቶች ጀመራቸው!› ተብሎ በፍረጃ የሚጠቃለሉ ጉዳዮች፣ ዛሬ በብዛት ለምናየው በሴቶች ላይ ለሚደርስ አሰቃቂ ጥቃት አንዱ ምክንያት ነው።
በቅርቡ አዳናይት ይሄይስ የተባለች የ17 ዓመት ልጅ ታሪክ ተሰምቷል። ፍትሕ ሚኒስቴር ባወጣውና እስከ አሁን አሰባሰብኩት ባለው መረጃም፣ ጥቃቱን በአዳናይት ላይ የፈጸመው ግለሰብ ከ10 ዓመቷ ጀምሮ አስገድዶ መድፈርና ጾታዊ ትንኮሳ ያደርስባት እንደነበር ጠቅሷል። ከሰባት ዓመታት በኋላ ለፖሊስ ጥቆማ መድረሱን ተከትሎ ነው ግለሰቡ በስለት ወግቶ ሕይወቷ እንዲያልፍ አድርጓል።
የዚህች የ17 ዓመት ልጅ የሰባት ዓመታት ዝምታ እና ጉዳዩ ይህን ያህል ዓመት ታፍኖ ለመክረሙ ምክንያቱ ማኅበረሰብ ጋር ያለው የአመለካከት ክፍተት ነው። ጥቃት ሲደርስ አውጥታ ከመናገር ይልቅ በደል ካደረሰባት በላይ እርሷ ተሸማቅቃ እንድትቆይ የሚያደርገውም ይኸው የማኅበረሰብ ዕይታ፣ ብያኔና ፍረጃ አግባብ ያለመሆን ነው።
አንዲት ሴት ልጅ ጭር ባለ መንገድ ብቻዋን እንዳትሄድ የሚያሰጋት እንደወንዶች የሌባ ዝርፊያ ብቻ ሳይሆን ሊደርስባት የሚችል ጾታዊ ጥቃት ነው። ሰዓቱ ጨለምለም ሲል በታክሲ ውስጥ ስትሳፈር፣ ሊፈጸም ከሚችለው ዝርፊያ በተጓዳኝ በታክሲ ውስጥ ያለውን የጾታ ስብጥር ልብ ብላ ታያለች። መንገድ ላይ ከፊቷ የሚመጣም ሆነ ከኋላዋ የሚራመድን ወንድ እንቅስቃሴ በንቃት ትከታተላለች።
ሁሏም ሴት እንዲህ ባለ መንገድና ስሜት ላይ ናት ማለት አይደለም። ነገር ግን ቤት ይቁጠረው ብለን ልንጠቅሰው የምንችል፣ እንደ አዳናይት የልጅነትና የዝምታ የሆኑ፣ ጥቃትንና በደልን የመሸከም ሰባት ዓመታት ውስጥ እያለፉ ያሉ ሴቶች እልፍ ናቸው።
በአዲስ ማለዳ እምነት እንዲህ ያሉ ጥቃቶች ቢያንስ በቁጥር እንዲቀንሱ ለማድረግ የማኅበረሰብ አመለካከት መሻሻልና መለወጥ አለበት። ለእናት ትልቅ ክብር አለኝ በሚልና አገሩን ጨምሮ መኖሪያ ቀዬውን ሳይቀር በሴት አንቀጽ በሚጠራ ማኅበረሰብ ውስጥ፣ የሚታየው እውነት ግን ለየቅል ነው።
አዲስ ማለዳ ፍትሕ ስትጠይቅ በአዳናይት ላይ ስለተፈጸመው ተደራራቢ ወንጀል ብቻ ሳይሆን፣ ማኅበረሰቡ እንዲህ ያለውን ወንጀል እንዲፈጸም የነበረውን ድርሻ በመጠቆም ብሎም ከተፈጸመ በኋላ በዝምታ ስለማሳለፉም ነው። ፍትሕ እንፈልጋለን ስትል የምትጠይቀውም በደረሰባቸው ጾታዊ ጥቃት ሕይወታቸው ስለጠፋ ብሎም ከባድ ሕይወትን እንዲገፉ ስለተገደዱ እህቶቻችን ብቻ ሳይሆን፣ አሁንም ያንን ተሸክመው በዝምታ በየቤታቸው ስለሚገኙትም ጭምር ነው።
ፍትሕን የምንጠይቀው ከመንግሥትና ከሕግ አካላት ብቻ ሳይሆን ከማኅበረሰቡም ጭምር ነው። ምክንያቱም በዝምታ ውስጥ ሆነው፣ ጾታዊ ጥቃት ተሸክመው ያሉ ሴቶችም ፍትሕን የሚሹትና ሊያገኙ የሚችሉት ከማኅበረሰቡ ነው።
የሕግ አፈጻጸም ጉዳይ ተነስቶ ተገቢ ፍርድ እየተሰጠ አይደለም የሚል ቅሬታ እንደሚነሳው ሁሉ፣ ጥቃት ደርሶባቸው በይፋ ራሳቸውን የገለጡ ሴቶች ላይም የሚደርሱ ዘለፋዎችና ማኅበራዊ ሽሙጦች ፍትሕን ያዛንፋሉ። የሕግ አካላትን ፍትሐዊ እንዲሆኑ እንደምንጠይቅ ሁሉ፣ ማኅበረሰቡም ፍትሐዊ እንዲሆን እንለምናለን። ፍትሕ ለአዳናይት! ፍትሕ በዝምታ ውስጥ ላሉ እህቶቻችን!



