መግቢያ
ከከተማ እስከ ክፍለ አገር ያለው ማኅበረሰብ ትራንስፖርት በእጅጉ እንዳማረረው ሲናገር ይደመጣል። በከተማው የከተሙ ሰዎች ደግሞ ሚዛን የሚደፋው ቅሬታቸው ከመንገድ መጨናነቅ መዘጋጋት ጋር በተያያዘ ነው።
የአዲስ አበበ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ ከትራንስፖርት ክፍያ ይልቅ በመንገድ መዘጋጋት የሚባክው ጊዜ በዕለት ተዕለት ተግባራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል። የመንገድ መዘጋጋት በሌሎች በርካታ የክልል ከተሞችም ጭምር የሚስተዋል ችግር ቢሆንም በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ጎልቶ ይታያል።
በክፍለ አገር በኩል የሚነሳው ቅሬታ የትራንስፖርት እጥረት እና ከእጥፍ በላይ የሆነ የታሪፍ ጭማሬ መሆኑን ተጓዦች በተደጋጋሚ ይገልጻሉ። ከከተማ ወደ ክፍለ አገር እንዲሁም ከክፍለ አገር ወደ ከተማ የሚጓዙ መንገደኞች በበኩላቸው፣ ከተሽከርካሪ እጥረት በተጨማሪ በሹፌሮች ፍላጎት ብቻ ከእጥፍ በላይ የሚጨመረው ታሪፍ ለዘመናት ያልተፈታ ችግራቸው መሆኑን ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ከምንም በላይ በመንገድ መጨናነቅ ምክንያት በትራንስፖርት ጉዞ ላይ ሆነው የሚባክነው ጊዜ ዘርፈ ብዙ ችግር እያስከተለባቸው መሆኑን በቅሬታ ያነሳሉ።
ቅሬታ
ከትራንስፖርት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን ባሉ ቦታዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲሰነዘር ይሰማል። ችግሩን ማኅበረሰቡ ብቻ ሳይሆን ምሁራንም የሚጋሩት ሲሆን፤ ጉዳዩን ተንተርሰውም መንስኤውንና መፍትሄን ለማመላከት ሞክረዋል። ችግሩን በተመለከተ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተለያዩ ምሁራንን ጨምሮ የትራንስፖርት ተገልጋዮች ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዮሐንስ በላይ ከእሁድ ውጪ ባሉት ኹሉም ቀናት ከአባዶ ወደ መገናኛ አልፎ አልፎም ወደ መርካቶ እየተዘዋወሩ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ቤተሰብ እንደሚያስተዳድሩ በቅድሚያ ገለጹ። አክለውም በትራንስፖርት ዙሪያ የሚስተዋለውን ችግር በምልከታቸው መሠረት አብራርተዋል።
ዮሐንስ ከገቢያቸው አንጻር ተመራጭ የትራንስፖርት ዓይነት አንበሳ እና ሸገር የብዙኀን ማመላለሻ የከተማ አውቶብሶች እንደሆኑ ይናገራሉ። የዚህ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ ከሆኑም ሦስት ዓመት አስቆጥረዋል። የከተማ አውቶብሶች የሚያስከፍሉት ዋጋ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን የማኅበረሰብ ክፍል ያማከለ ስለመሆኑ አመስግነው፤ በሰልፍና በጉዞ ላይ የሚያባክኑት ጊዜ ግን ሥራቸውን በእቅዳቸው መሠረት እንዳያከናውኑ መሰናክል እንደሆነባቸው ለአዲስ ማለዳ ግልጸዋል።
‹‹አንዳንዴ ከተማ ውስጥም ቢሆን ትራንስፖርት ከመጠበቅ በእግር መጓዝ ሰዓትን ለመቆጠብ የተሻለ አማራጭ ከሆነበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። ለምሳሌ በተለይም ከቀኑ 10 ሰዓት በኋላ ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ መንገዱ ዝግ ስለሚሆን በትራንስፖርት 10 ደቂቃ ለሚጠይቅ መንገድ ኹለት ሰዓት እጓዛለሁ። ለአብነትም ከመገናኛ እስከ ኡራኤል ቤተክርስትያን ድረስ 10 ደቂቃ በትራንስፖርት ተጉዤ አውቃለሁ። ከዕለታት በአንደኛው ቀን ግን በእግሬ በመጓዝ የ30 ደቂቃ መንገድ መሆኑን አረጋግጫለሁ።›› ሲሉ ልዩነቱን አብራርተዋል።
አክለውም፤ በዛን እለት በእግራቸው አንሄድም ብለው ትራንስፖርት ውስጥ የነበሩ የሰፈራቸው ሰዎች መንገድ በመዘጋጋቱ አንድ ሰዓት ተኩል ገደማ እንዳባከኑ አስታውሰዋል። ይህ ሁሉ ችግር የተከሰተው መኪና ጠፍቶ ሳይሆን በመንገድ መጨናነቅ ሲሉ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ መዘጋጋት በየእለቱ የሚስተዋል ችግር ከሆነ ውሎ አድሯል። ነዋሪዎች ለችግሩ በይበልጥ ተጋላጭ ስለመሆናቸው ኹነቱን በጥልቀት የተከታተሉ የፖለቲካ ምሁራን በበኩላቸው ጉዳዩን የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።
በትራንስፖርት ከሚያልቀው ወጪ በተጨማሪ ተሳፋሪዎች በጉዞ ላይ እያሉ የሚባክነው ጊዜ ስለሚያይል የሚመለከተው አካል መፍትሄ ሊሰጥበት ይገባል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ አብዱ አያሌው ናቸው።
በአዲስ አበባ ውስጥ በትራንስፖርት መጨናነቅ ምክንያት ለምሳሌ 20 ደቂቃ መጠናቀቅ የሚችለው መንገድ እስከ አንድና ኹለት ሰዓት ድርስ የሚጨርስበት ጊዜ ብዙ ነው ይላሉ ተንታኙ። በተያያዘም የትራንስፖርት መጨናነቅ ለማኅበረሰቡ ከኑሮ ውድነት ተጨማሪ ሌላኛው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኗል ሲሉ ገልጸዋል።
በመሆኑም በመጀመሪያ የችግሩን መንስኤ በትኩረት ተመልክቶ መፍትሄ መስጠት ያስፈልጋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ለመንገድ መጨናነቅ ዋና ዋና የሚባሉ መንስኤዎችንም ተሳፋሪዎችም ሆኑ ምሁራን በዝርዝር ተናግረዋል።
መንስኤ
ለመንገድ መጨናነቅ የተለያዩ ምክንያቶች ስለመኖራቸው ችግሩን በተደጋጋሚ የተመለከቱ ተሳፋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በገለጻቸው መሠረት፤ የነዳጅ ማደያዎች መንገድ ዳር መሆናቸው፤ የቤት መኪናዎችና የከተማ አውቶብሶች የሚንቀሳቀሱበት ወቅት ተመሳሳይ መሆን፤ አብዛኛዎቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከዋና መንገድ ላይ መሆናቸው ለመንገድ መዘጋጋት ቀንደኛ መንስኤዎች ናቸው።
የመንገድ መዘጋጋት ለሥራ የሚውል ጊዜን ስለሚሻማ አንገብጋቢ ምላሽ እንደሚሻ የገለጹት የፖለቲካ ተንታኙ አብዱ አያሌው በበኩላቸው፣ ለችግሩ መከሰት ምክንያቱ ምንድን ነው ለሚለው ሐሳባቸውን አካፍለዋል።
‹‹የቤት መኪናዎች የሚጭኑት የሰው ብዛት አነስተኛ ነው። የሚጓዙት ግን እስከ 70 ሰው ድረስ ከተሳፈረበት የከተማ አውቶብስ ጋር በመጋፋት ነው። የቤት መኪና መኖር ይበል የሚያስብል ጉዳይ ይሁን እንጂ በመንገድ ላይ የሚያስከትለው ችግር ግን መስተካከል አለበት።›› ብለዋል አብዱ።
በአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ መዘጋጋት በተለይም ጠዋትና ማታ ላይ ሆኖ ይስተዋላል። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ጠዋትና ማታ የሥራ መግቢያና መውጫ ወቅቶች መሆናቸው ነው።
አዲስ ማለዳ በሸገር የከተማ አውቶብስ ያገኘቻቸው ዮርዳኖስ አስማማው የተባሉ አባት በበኩላቸው፣ በመንገድ መዘጋጋት ብዙ ጊዜ እየባከነ ነው የሚለውን ሐሳብ ሳያቅማሙ ተስማምተዉበታል።
እንዲህ ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል፤ ‹‹በትራንስፖርት ላይ ተሆኖም ጊዜ እየባከነ ያለው በተለይም የቤት አውቶሞቢሎች መንገዱን ስለሚዘጋጉት ነው። በመሆኑም የከተማ አውቶብሶችና የቤት ተሽከርካሪዎች የሚንቀሳቀሱበትን ወቅት ለተወሰነ ሰዓት እንዲለያይ ማድረግ ተገቢ ነው።››
በሌላ በኩል ለመንገድ መጨናነቅ እንደ መንስኤ የተነሳው የነዳጅ ማደያዎች ዋና መንገድ ዳር መሆንና አገልግሎቱን የሚሹ ተሽከርካሪዎች ሌሎች እንዳያልፉ መንገድ መዝጋታቸው ነው። የነዳጅ እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት በርካታ ተሽከርካሪዎች መቆሚያቸው ዋና ድልድይ ላይ ሆኖ ይስተዋላል።
በተለይም ነዳጅ በሚጠፋበት ወቅት ተሽከርካሪዎች መንገዱ ላይ ተሰድረው ማኅበረሰቡ በእግሩ ለመጓዝ የተገደደበት ጊዜ ጥቂት አይደለም።
አንዳንድ ተሳፋሪዎች በበኩላቸው ነዳጅ በሚጠፋበትም ሆነ ተሽከርካሪዎች ነዳጅ በሚያስሞሉበት ወቅት ሕዝቡ ለችግር ተጋላጭ የመሆን እድሉ የከፋ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። ከጅቡቲ ተነስተው ወደ አዲስ አበባና ወደተለያዩ የክልል ዋና ከተሞች መድረስ የነበረባቸው 200 ነዳጅ ጫኝ ቦቴዎች ከአዲስ አበባ ውጪ በየሰፈሩ ተደብቀው መገኘታቸውን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን በ2014 ሰኔ ወር መገባደጃ ማሳወቁ የሚታወስ ይታወሳል።
ያ ወቅትም ሆነ ነዳጅ ከመጣ በኋላ እና በፊት ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ለማስሞላት የሚጠብቁት ወረፋ ለተሳፋሪዎች የትራንስፖርት ፍሰት አስቸጋሪ ስለመሆኑ ያስታወሱ ቅሬታ አቅራቢዎችም አሉ። የታክሲ ሹፌሮች በበኩላቸው የመንገድ መጨናነቅን በተመለከተ አስተያየት ሰጥተዋል።
ዳዊት ብርሃኑ የተባሉ የታክሲ ሹፌር በበኩላቸው፣ በመንገድ መዘጋጋት የሚባክነው ጊዜ ለታሪፍ መጨመር ምክንያት መሆኑን አልደበቁም። በተያያዘም ‹‹በተለይም የቤት አውቶሞቢሎች ከተሳፋሪዎች የሚጠብቁት ብር እምብዛም ብዙ አይደለም። ካልተሠራ አይበላምና ቢሮ ለመግባትም በመኪናቸው መንቀሳቀስ ግድ ይላቸዋል። ሆኖም በይበልጥ ጠዋት እና ማታ አብዛኛውን መንገድ ዝግ እንዲሆን ስለሚያደርጉ ለጊዜ መባከን ብቻ ሳይሆን ከትራንስፖርት በሚያገኙት ገቢ ቤተሰብ ለሚያስተዳድሩ የታክሲ ሹፌሮችም የኢኮኖሚ ቀውስ እንዲከሰት ምክንያት ናቸው።›› ሲሉ ዕይታቸውን ለአዲስ ማለዳ አካፍለዋል።
በጥቅሉ ተሳፋሪዎች በትክክል እንዲገለገሉ፤ የታክሲ ሹፌሮች ከሚያደርጉት የታሪፍ ጭማሪ እንዲታቀቡ እንዲሁም ኹሉም ሰው በመንገድ መጨናነቅ ምክንያት ጊዜውን ሳያባክን ውሎ እንዲገባ የመንገድ ሥርዓት ላይ ማተኮር ይገባል ባይ ናቸው።
በሌላ በኩል ለመንገድ መጨናነቅ መንስኤ ነው የተባለው አብዛኛዎቹ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በአውራ ጎዳና ዳር መሆናቸው ነው። የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች አውራ ጎዳና መንገድ ላይ መሆናቸው ኃላፊዎች በግልጽ ቦታ ለማኅበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ቢረዳም ለመንገድ መዘጋጋት ግን ምክንያት ነው ሲሉ ተሳፋሪዎች ቅሬታ ያነሳሉ።
እንደ ቅሬታቸው ከሆነ፤ ከፍተኛ ተቋማት አካባቢ ተሽከርካሪ ስለሚበዛ መንገድ የመዘጋጋቱ እድል ይሰፋል። የማጣኔ ሀብት ባለሙያዎች በበኩላቸው በመንገድ መጨናነቅ ምክንያት ተሳፋሪዎች በትራንስፖርት ውስጥ ሆነው የሚያባክኑት ጊዜ ኢኮኖሚያቸው ላይም አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው እየገለጹ ነው።
ተሳፋሪዎች በትራንስፖርት የሚያባክኑት ጊዜ በኢኮኖሚቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያስከትላል የሚሉት የምጣኔ ሀብት አማካሪው ያሬድ ይታፈሩ ናቸው።
ለመንገድ መጨናነቅ ወይም መዘጋጋት ምክንያቱ የተሽከርካሪ ማነስ ወይስ የመንገድ መጥበብ? የሚሉ ጥያቄዎች ሲሰነዘሩ የሚሰማ ሲሆን፤ ያሬድ ይህንኑ ጥያቄ በተመለከተም ለችግሩ ዋነኛ ምክንያት የመንገድ ሥርዓት አለመኖር፤ የመንገድ መጥበብ እንዲሁም የተሽከርካሪ ማነስም ሊሆን ይችላል ብለዋል።
የፖለቲካ ተንታኙ አብዱ በበኩላቸው ‹‹ባለው ተሽከርካሪ የመንገድ ሥርዓቱን ማስተካከል ይገባል። አብዛኛውን ጊዜ ሕዝቡ እየተጉላላ ያለው በትራንስፖርት እጥረት ብቻ ሳይሆን በመንገድ መጨናነቅ ነው›› ብለዋል።
ይሁንና የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ምሁራን በተለይም ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የሚያስፈልገው ተጨማሪ ተሽከርካሪ ብቻ ሳይሆን የመንገድ ሥርዓት ማስተካከልም ለሚስተዋለው ችግር መፍትሄ እንደሚሆን አቅጣጫ ሰጥተዋል።
መፍትሄ
በመንገድ መጨናነቅ ለሚስተዋለው የጊዜ ብክነት ተጨማሪ ተሽከርካሪዎችን ከመግዛት ባሻገር የመንገድ ሥርዓትና ቅያሬ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሁ የምጣኔ ሀብት አማካሪው ያሬድ መክረዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጷጉሜ 4/2014 የአገልጋይነት ቀንን ምክንያት በማድረግ 110 አዳዲስ የአንበሳ አውቶቢሶችን፣ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ በማድረግ ሥራ ማስጀመሩ ይታወቃል።
በተያያዘም የትራንስፖርት ዘርፉን ለመደገፍ በሚቀጥሉት ሦስት ወራት 250 አዳዲስ አውቶቢሶች ወደ አገልግሎት የሚገቡ መሆናቸውን የአዲስ አበበ ከተማ ከንቲባ መግለጻቸው በወቅቱ ተጠቅሶ ነበር።
ኹሉም የማኅበረሰብ ክፍል በሚባል ደረጃ በድርጊቱ ደስ እንደተሰኙ ሐሳባቸውን ሲያንሸራሽሩ ተስተውለዋል። የኢኮኖሚ ባለሙያው በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩን ድርጊት እሰየው ብለዋል። በተያያዘ ግን በቀጣዮቹ ሦስት ወራት 250 ተሽከርካሪ ብቻ መግዛት ሳይሆን፤ የመንገድ ሥርዓቱንም ማስጠበቅ ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።
አማካሪው በተያያዘም ጠቅለል አድርገው መፍትሄ ይሆናሉ ያሏቸውን ኹለት ፍሬ ነገሮች አስቀምጠዋል። በዚህም የከተማ አውቶብሶች፤ ታክሲዎች ከቤት መኪናዎች ጋር በተለያየ ሰዓት የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ መንገዶችን እንዲገነቡ ማድረግ አንደኛውና የመጀመሪያው የመፍትሄ ሐሳብ ነው ብለዋል።
ራይዶች፤ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም ላዳዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለሕዝቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻል ሌላኛውና ኹለተኛ ነጥብ ነው። በተለይም የከተማ አውቶብሶችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች የሚጓዙበትን መንገድ የተለያየ እና ቀልጣፋ ማድረግ ይገባል ሲሉም ምክረ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015



