እርማትና ተጨማሪ ማብራሪያ

1
2318

አዲስ ማለዳ በቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14/2015 እትሟ ‹በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪ በ20 ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑ ተነገረ።› በሚል ርዕስ የፊት ገጽ ዜና ይዛ መውጣቷ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ዩኒቨርሲቲው በዜናው ላይ ቅሬታ እንዳለው ለጋዜጣዋ ዝግጅት ክፍል አሳውቋል። ቅሬታው በዋናነት ‹ዜናው ሚዛናዊ አይደለም› የሚል ነበር። አዲስ ማለዳ ዘገባውን ሚዛናዊ ለማድረግ ተቋሙ በድረ-ገፁ ላይ ባስቀመጠው ስልኮች ላይ በተደጋጋሚ በመደወል የሚመለከታቸውን የሥራ ኃላፊዎች ለማነጋገር ጥረት አድርጋለች። ነገር ግን ይህ ሙከራዋ እንዳልተሳካ በዜናው ላይ ገልጸናል።

ምንም እንኳን ዜናውን ለአንባብያን ለማድረስ በሚታወቅ የሚዲያ አሠራር ምክንያት የጊዜ እጥረት የነበረብን ቢሆንም፣ የተቋሙን አመራሮች ለማግኘት ተጨማሪ ጊዜ ወስደን በጉዳዩ ላያ ያላቸውን አስተያየት ማካተት ተገቢ እንደነበር እናምናለን። ይህን ሳናደርግ ዜናውን ለአንባቢያን በማቅረባችን ዩኒቨርሲቲውንም፣ አንባቢያንንም ይቅርታ እንጠይቃለን።

በተጨማሪም፣ ጉዳዩ በዜናው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ዩኒቨርሲቲው አውቆ፣ ተቋሙ በዘረጋው ሥርዓት በኩል እውቅና ተሰጥቶት ትምርህታቸውን በተቋሙ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ገብተው ላልተማሩ ሰዎች 20 ሺሕ ብር ስለከፈሉ ብቻ ዲግሪ እየተሰጣቸው እንደሆነ የሚመስል አንድምታ ዜናው እንደፈጠረ ተረድተናል። ነገር ግን በምርመራችን እንዳረጋገጥነው ይህ ስህተት ነው። ዩኒቨርሲቲው ይፋዊ በሆነ መንገድ ሳያውቀውና እውቅና ሳይሰጠው በተቋሙ ሥም የሚዘጋጁ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን አንዳንድ ሰዎች 20 ሺሕ ብር በመክፈል እያሠሩ መሆኑን አዲስ ማለዳ በምርመራዋ አረጋግጣለች። የዜናችን ርዕስ ከዘገባው መሠረታዊ ጭብጥ በወጣ መልኩ ዩኒቨርሲቲው በ20 ሺሕ ብር ዲግሪ እየሸጠ እንደሆነ አንድምታ በሚፈጥር መልኩ መሠራቱ ስህተት ስለሆነ ዩኒቨርሲቲውንም፣ አንባቢያንንም ይቅርታ እንጠይቃለን።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የያዙ ሰዎች በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ በስፋት ተቀጥረው ሥራ ላይ የሚገኙ መሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ በዜና አውታሮቹ እንዳስነገረ ይታወቃል። እነዚህ በሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ሥራ የያዙ ሰዎች ከሕክምና እስከ ትምህርት ተቋማት ውስጥ በስፋት እንደተሰገሰጉም አንባቢያን እንዲያውቁት አዲስ ማለዳ ታስገነዝባለች።

ይህም አገርን ለሙስናና ብልሹ አሠራር፣ እንደዚሁም ለከፍተኛ የሀብት ብክነትና ኢ-ፍትሃዊነት እንደዳረገ ግልጽ ነው። በአገራችን የተንሰራፋው ሐሰተኛ የሰነድ ዝግጅት ከትምህርት ዘርፍ በዘለለ በንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድ ዝግጅት በስፋት እየተከናወነ ያለ ነው። በሐሰተኛ የቤትና መሬት ባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ፣ የመኪና ሊብሬና ሌሎችንም የንብረት ባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነዶች ምክንያት ለከፍተኛ ኪሳራ የተዳረጉ ዜጎች እንዳሉ የአደባባይ ምስጢር ነው። አዲስ ማለዳ ይህን መሰል ጉዳዮችን በስፋትና በጥልቀት መርምራ ሕዝብን የማሳወቅ ግዴታዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል በዚህ አጋጣሚ ታሳውቃለች።

አዲስ ማለዳ ለማኅበረሰብ ለውጥ (Social Transformation) ተግታ የምትሠራ ሚዲያ ናት። ለጋዜጠኝነት መርህ፣ የሥነ ምግባር እሴትና ሙያ ኃላፊነት ተገዢ የሆነችና በሥራዎቿም አቅም በፈቀደ መጠን ሚዛኗን ጠብቃ የምትሠራ ጋዜጣ ናት። በዘገባዎቿ ሁሉ ሚዛናዊነትን ማእከል አድርጋ ተልዕኮዋን አጠናክራ እንድትወጣ የመረጃ ምንጮቿ፣ እንደዚሁም የሚመለከታችሁ ግለሰቦችና ተቋማት መረጃን በፍጥነትና በተሟላ መንግድ ለጋዜጠኞቻችን የመስጠት ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ በድጋሜ አደራ ትላለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28

አስተያየት

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here