በኹለት ዙር በሚሰጠው የ2014 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች የዩንቨርሲቲ መግቢያ ፈተና፣ በመጀመሪያው ዙር ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ተፈትነዋል።
ይሁን እንጂ በአማራ ክልል ከነበሩ አራት የፈተና ማእከላት ከ12 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች ፈተናውን አቋርጠው መውጣታቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል። ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች ከትምህርት ሥርዓት ባፈነገጠ መልኩ ‹አንፈተንም› ብለው በገዛ ፈቃዳቸው ጥለው እንደወጡ ቢገልጽም፣ የተለያዩ አካላት ጉዳዩ ከዚህም ያለፈ መሆኑን ሲያነሱ ይስተዋላል።
በመሆኑም በጉዳዩ ላይ ከሚነሱ ውዝግቦች መካከል ተማሪዎች ፈተናውን ጥለው የወጡት መኮራረጅ ባለመቻላቸው ነው ወይስ የሌላ አካል የፖለቲካ መጠቀሚያ በመሆናቸው ነው የሚለው ነው።
ተማሪዎች ‹በማኅበራዊ ሚዲያ ፈተናው ተሰርቆ ወጥቷል፣ ሌሎች ፈተናውን ቀድመው ሠርተው እኛ በጥብቅ ቁጥጥር መፈተን የለብንም› የሚል ተቃውሞ ማሰማታቸውን ቅርበት ካላቸው አካላት መገንዘብ ተችሏል።
ፈተናው ከተጀመረበት እለት አንስቶ በተለይ ከ13 ሺሕ በላይ ተከታዮች ባለው የቴሌግራም ገጽ የዘንድሮ ፈተና ጥያቄዎች በፎቶ ተደግፈው ሲለቀቁ እንደነበር አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።
ትምህርት ሚኒስቴርም ይህ ችግር አጋጥሞ እንደነበር እና ፈተና እየተሰጠ እያለ አንድም ኹለትም ፈተና የሚለጥፉ የቴሌግራም ገጾች እንደነበሩ ገልጿል።
ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተማሪ ፈተና ጥሎ የወጣው ከደብረ ታቦር ዩንቨርሲቲ ነው። ሆኖም በቦታው የሚኖሩ አንድ የተማሪ ወላጅ ‹‹አብዛኞቹ ተማሪዎች ፈተናውን አቋርጠው የወጡት በምንም ሳይሆን ‹ካልኮረጅን አንፈተንም› በማለት ነው። በዚህ እርግጠኛ ነኝ›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ጥቂቶቹ ደግሞ ከፖለቲካ ጋር አያይዘውት ነበር። እርግጠኛ ባልሆንም ከዘመነ ካሴ ችሎት ጋር በተገናኘ ያልተፈተኑ ተማሪዎች መኖራቸውን ሲወራ ሰምቻለሁ ነው ያሉት። ስለሆነም፣ በሌሎች ተማሪዎች ጫና ሳይፈተኑ የቀሩ በመኖራቸው ትምህርት ሚኒስቴር ውሳኔውን እንደገና ያየዋል የሚል ተስፋ አለኝ ብለዋል።
በደብረ ማርቆስ ዩንቨርሲቲ እንዲሁ በርከት ያሉ ተማሪዎች ፈተናውን አቋርጠው የወጡ ሲሆን፣ ከዚሁ ጋር በተገናኘ አስተያየታቸውን የሰጡ መምህር በርካታ የክልሉ አክቲቪስቶች፣ ፖለቲከኞችና ተቋማት ነገሩ እንዳናደዳቸውና ተገቢ እንዳልሆነ ሲገልጹ ሰምቻለሁ።
ነገር ግን ልጆች ናቸው። ዛሬ የሚያደርጉት ነገር ነገ ምን እንደሚያመጣባቸው በደንብ አይገነዘቡም። ከዚህ አንጻር የተደረገ በቂ ሥራ አለ ብዬ አላምንም። ጥለው መውጣታቸውን ከማራገብና ድርጊቱን ከመኮነን ባለፈ ብስለት በተሞላበት አካሄድ ችግሩን ለመቆጣጠር የተደረገው ሙከራ አናሳ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ሆኖም ግን የዩንቨርሲቲ አመራሮች፣ ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች በዩንቨርሲቲዎች ተማሪዎችን ሲለምኑና ሲያረጋጉ እንደነበር ሳይጠቅሱ አላለፉም።
በክልሉ ከተፈታኝ ተማሪዎች ጋር በተገናኘ በየዓመቱ ተጠባቂ ችግር እንዲኖርና ተማሪዎችም ፍርሃት እና ጭንቀት እንዲያድርባቸው በማድረግ ኪሳራ እንዲደርስባቸው የሚሠራ አካል አለ። በዘንድሮ ተፈታኞችም በኹሉም ክልሎች ያልተፈጠረ ችግር በአማራ ክልል ብቻ የተፈጠረው የዚሁ ሴራ ሰለባ በመሆናቸው ነው ሲሉም አንድ ሌላ መምህር ዕይታቸውን አጋርተዋል።
አንዳንዶች ፈተናው ከብዷቸው መፈተን ባልቻሉ ተማሪዎች እና የፈተና ጥያቄውን መውጣት ዐይተው ጭንቀት በተፈጠረባቸው ተማሪዎች አማካኝነት ችግሩ እንደተፈጠረ ይናገራሉ። ሎሎች ደግሞ 12 ዓመት የደከሙ ጎበዝ ተማሪዎች ጭምር ክፉኛ ተረብሸዋል በማለት ድርጊቲን የኮነኑ ሲሆን፣ ችግሩን መኮረጅ ባለመቻላቸው እንከን ከፈጠሩ ልጆች ጋር አያይዘውታል።
ተማሪዎች ያለኩረጃ ውጤት እንደማያመጡ ገምተው እንጂ፣ በራሳቸው መተማመን ቢችሉ ኖሮ ይፈተኑ ነበር በማለት ከዚህ በኋላ እድል ሊሰጣቸው አይገባም የሚሉም አሉ።
ይሁን እንጂ፣ ጉዳዩ የተማሪዎችን ሕይወት ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የቤተሰቦቻቸውንም የዘመናት ድካም ከንቱ የሚያስቀር በመሆኑ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባ ጥያቄዎች እየቀረቡ ይገኛል። አሁንም በማኅበራዊ ሚዲያ የሚደርስባቸው ውርጅብኝ ችግሩን የሚያቃልል ሳይሆን፣ የታዳጊዎች የነገ እጣፈንታ እልባት እንዳያገኝ የሚያደርግ መሆኑ እየተገለጸ ነው።
በፈተና ስርቆትም ሆነ በሌላ የጎላ ችግር ባልተፈጠረበት ሁኔታ ተማሪዎች ስሜታዊ እንዲሆኑ እና ተረጋግተው እንዳይፈተኑ በማኅበራዊ ሚዲያውና ግዴለሽ በሆኑ አካላት ጫና ውስጥ ገብተው ነበር የሚሉም ብዙዎች ናቸው።
ከመቅደላ አምባ ዩኒቨርሲቲ 1 ሺሕ 700፣ ከደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ 1 ሺሕ 226፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ 2 ሺሕ 711 እንዲሁም ከደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ 7 ሺሕ 150 ተማሪዎች በጠቅላላው 12 ሺሕ 787 ተማሪዎች ፈተናቸውን ሙሉ ለሙሉ ወይም ውስን ፈተናዎችን በመውሰድ ጥለው መውጣታቸው ነው የተነገረው።
ትምህርት ሚኒስቴር በመጀመሪያው ዙር ፈተና ያጋጠሙ ቁልፍ ችግሮችን የገለጸ ሲሆን፣ በቂ ቅድመ ገለጻ (ኦረንቴሽን) ባለማግኘት ወይም በማወቅም ጭምር የተከለከሉ ቁሶችን ይዘው የመጡና ይዘው የተገኙ ተፈታኞች መኖራቸው አንዱ ነበር ብሏል።
ነፍሰጡር እና እመጫት ተፈታኞች በሌላ ዙር እንደሚፈተኑ አስቀድሞ ቢገለጽም፣ በዚህኛው ዙር ለፈተና መምጣታቸውን እንደ ሌላ ችግር በመጥቀስ፣ በፈተና አዳራሽ በጋራ ካልሠራን ብለው ከፈተና አስፈጻሚዎች ጋር ግብ ግብ የፈጠሩ ተፈታኞች ማጋጠማቸውንም አመላክቷል።
እንዲሁም ከተሰጣቸው መመሪያና ከፈታኝ የማይጠበቅ ተግባር ላይ የተሳተፉ የፈተና አስፈጻሚዎች እንዳጋጠሙም ነው የገለጸው።
በትራንስፖርት እጥረት ምክንያት ዘግይተውና አምሽተው በዩኒቨርሲቲዎች የደረሱ መኖራቸው ሌላኛው ችግር ሲሆን፣ ተማሪዎች ስልክ እንደሌላቸውና ፈተና ቢወጣ እንኳ እንደማያገኙ እየታወቀ ፈተና እንለጥፋለን የሚሉ ‹‹የቴሌግራም ገጾች›› ማጋጠማቸውና ፈተና ካለቀ ወይም በመሰጠት ላይ እያለ አንድም ኹለትም ገፅ መለጠፋቸው በፈተና አሰጣጡ ላይ ችግር የፈጠረ እንደነበር አመላክቷል።
በተለይም በደብረ ታቦር ዩኒቨርሲቲ ተፈታኞች ኃይል በተቀላቀለበት መልኩ ሁከት በመፍጠራቸው፣ የአንድ ተማሪ ሕይወት ሲያልፍ በፈተና አስፈጻሚዎችና በጸጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል።
ፈተና ጥለው የወጡትን ተማሪዎች በተመለከተም ፈተና መፈተን እንደማይፈልጉ አሳውቀው ግቢ ለቀው የወጡ በመሆናቸው በቀጣይ መፈተን የማይችሉ መሆኑን ነው ያሳወቀው።
ሆኖም ግን ግቢውን ለቀው ባለመውጣት ቀጣይ ፈተናዎችን የወሰዱና በመሀል ከፍላጎታቸው ውጭ በሆነ መንገድ አንድ ፈተና ሳይፈተኑ የቀሩ ተማሪዎች በሚቀጥለው ዙር ፈተና የሚፈተኑ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።
የተከለከሉ ነገሮችን ደብቀው ይዘው ለመግባት የሞከሩ ተማሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ከፈተና የተሰናበቱ ሲሆን፣ ያልተገባ ነገር ሲፈጽሙ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ፈታኞችም በሕግ ቁጥጥር ውስጥ ሆነው ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል ነው የተባለው።
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ፣ በማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ በጥቂት ማእከላት የተፈጠረው ችግር የወላጆችንና የመምህራንን እንዲሁም አጠቃላይ የማኅበረሰባችንን ልፋት መና ያስቀረ ነው ሲል ገልጿል።
ተማሪዎች በራሳቸው አቅም ብቻ ተማምነው ወደ ፈተና ማእከላት እንዲመጡ ቢሮው የጠየቀ ሲሆን፣ በዚህ መንገድ መፈተን ያልፈለገ ተማሪ ወደ ማእከላት ባይመጣ ይመረጣል ነው ያለው።
ከጥቅምት 08/2015 ጀምሮ 120 ሺሕ ለሚጠጉ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ለሚሰጠው ፈተናም በቂ የጸጥታ ዝግጅት ስለተደረገ ምንም ዓይነት ስጋት የለም ተብሏል።
በአማራ ክልል ባለፈው ዓመት ባልተለመደ ሁኔታ በርካታ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አለማምጣታቸው የሚታወስ ነው። ዘንድሮም ከ12 ሺሕ በላይ የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፍ ተማሪዎች ፈተና ማቋረጣቸውን ተከትሎ ብዙዎች ይህ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑንና የአንድ ትውልድ አካል በመሆናቸው፣ ዛሬ ሳይሆን ነገ ለሚፈጠረው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሲባል ትምህርት ሚኒስቴር ድጋሜ አይፈተኑም በሚል ያሳለፈውን ውሳኔ እንደገና እንዲያጤነው በርካቶች ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት በርካታ ችግሮች እንዳሉበት በተደጋጋሚ ይነሳል። በፈተና አሰጣጥ ወቅት በየዓመቱ የሚከሰቱ ችግሮችም የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ትልቅ ድክመት ማሳያ ተደርገው ሲወሰዱ ይስተዋላል።
በኦስትሪያ ለጥቂት ጊዜ በመምህርነት ሙያ ሲያገለግሉ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ግለሰብ፣ የአገራችን ትምህርት ሥርዓቱ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር እጅግ የወረደ መሆኑን በመጥቀስ በኦስትሪያ ተማሪዎች ዘንድ ያዩትን እንደምሳሌ በማንሳት አጋርተዋል።
‹‹ፈተና በምፈትንበት ወቅት የፈተና ጥያቄውን በፍላሽ ይዤ እንድታባዛው ለጸሐፊዋ ሰጠኋት። እሷም በኢሜል እንጂ በፍላሽ መላክ እንደማይቻል ስትነግረኝ የምታጭበረብረኝ መስሎኝ ሰጋሁ። በኋላም በኢሜል ልኬላት የተባዛውን የጥያቄ ወረቀት እንድትሰጠኝ ስጠይቃት ፈተናውን ከተማሪዎች ለአንዱ ልጅ እንደሰጠችውና ወደ ክፍል እንደተላከ ነገረችኝ።
እኔም ገርሞኝ ወደክፍል ስገባ ተማሪዎች የጥያቄ ወረቀት ተሰጥቷቸው ቁጭ ብለው እየጠበቁኝ ነበር። እኔን የፈለጉኝ ሰዓት እንድይዝላቸውና እንዳስጀምራቸው ነው። ፈተናውን ከጸሐፊዋ ተቀብሎ የወሰደውን ተማሪ የሰጠውን መልስ ሳየው ብዙ ስህተት አለበት። ለምን ቀድሞ ጥያቄዎቹን እንዳላየ ስጠይቀውም የፈተና ጥያቄ ማየት አይቻልም እኮ አለኝ።
ባደጉ አገራት ሕጻናት ራሳቸውን በራሳቸው መምራት ይችላሉ። እኛም ቀስ በቀስ እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ይኖርብናል›› በማለት ከገጠመኛቸው በመነሳት ሐሳባቸውን ገልጸዋል።
ተማሪዎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ኩረጃን እንደበጎ ነገር የሚመለከቱ በመሆናቸው፣ በየትኛውም የፈተና ወቅት ለማጭበርበር ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉ ይነሳል። በዚህ ሁኔታ ያለፉ ተማሪዎች ከትምህርት በኋላ ባለው የሥራ ሕይወታቸውም ሙሰኞች እንደሚሆኑ ነው የሚታሰበው።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015



