መንግሥት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው፣ ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት ትኩረት ሰጥታ ከሠራችባቸው የልማት መስኮች መካከል የስንዴ ልማት አንዱ መሆኑን በተደጋጋሚ ያነሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የዘንድሮውን የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት በሶማሌ ክልል ባስጀመሩበት ወቅትም ኢትዮጵያ በተያዘው ዓመት የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንደምትጀምር ተናግረዋል።
በዚህም በተያዘው ዓመት በሚሊዮን ኩንታል የሚቆጠር የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ይቀርባል የተባለ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ወደ ኬንያ የስንዴ ምርት እንድትልክ የሚያስችል ስምምነትም ተደርሷል።
ስምምነቱ የተደረሰው በቅርቡ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በይፋዊ የሥራ ጉብኝታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ነው። የኬንያ ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀውም፣ የስንዴ አቅርቦት ስምምነቱ በኬንያ የተከሰተውን የምግብ ምርቶች የዋጋ ንረት ለማረጋጋት አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ይሁን እንጂ፣ በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በሚከሰት ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ጦርነትና ግጭቶች እንዲሁም በሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ሳቢያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ባሉበት ሁኔታ የስንዴ ምርት ለውጭ ገበያ ይቀርባል መባሉ ጥያቄ ፈጥሯል።
በፈረንጆች 2018 የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት፣ ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ተፈናቃይ ቁጥር በዓለም በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን ጠቅሷል። አያይዞም በእርስ በርስ ግጭት ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎች በላይ ከቀያቸው እንደተፈናቀሉና ይህም በዓለም አገራት ያልተለመደ ነው ብሎታል።
የፌዴራል አደጋ ስጋትና አመራር ኮሚሽን በቅርቡ እንደገለጸው ደግሞ፤ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ አፋርና ሶማሌ ክልሎች ብቻ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ተረጂዎች ይገኛሉ።
ስለሆነም፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተረጂ ባለበት፣ በየመጠለያ ጣቢያው የሚገኙ በርካታ ተፈናቃዮች ከመንግሥት ምንም ዓይነት እርዳታ እየቀረበልን አይደለም በሚሉበት ሁኔታ፤ ስንዴ ለውጭ ገበያ ይቀርባል መባሉ፣ ለፖለቲካ ፍጆታ ወይም ደግሞ ከውጭ በእርዳታም ይሁን በግዢ የሚገባውን ስንዴ መልሶ ለመሸጥ ታስቦ ሊሆን ይችላል የሚሉ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ።
በስንዴ እጥረት የዳቦ ዱቄት መወደዱ፣ የዳቦ ዋጋም መናሩ ይስተዋላል። በዚህ መሀል መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የኑሮ ውድትን ከማባባስ ያለፈ ፋይዳ እንደማይኖረው ነው ብዙዎች የሚገልጹት።
ምናልባትም ስንዴ ለውጭ ገበያ ይላካል የተባለው ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል። ይህም የገባውን ቀጥታ በማስወጣት ሊሆን ይችላል በማለት የሚናገሩም አልጠፉ።
ምናልባትም ፖለቲከኞች በቀን አንዴ እንኳን ጠግቦ መብላት የማይችል ሚሊዮን ሕዝብ መኖሩን ሳይዘነጉ እንዳልቀሩ ትዝብቶች ይቀርባሉ። ሕዝብ ዳቦ ማግኘቱ ሳይረጋገጥ፣ ገበያ ማረጋጋት ላይ በሰፊው ሳይሠራ ስለ ስንዴ የውጭ ገበያ መላክ ቀድሞ ማውራት ጉዳዩን ለፖለቲካ ፍጆታ ከማዋል የዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው ማሳያዎች አሉ።
ውሸት ብርቅ ያልሆነባቸው የፖለቲካ መሪዎች ባሉባት አገር፣ የስንዴ ፖለቲካ እንደ ነዳጁ መሆኑ አይቀርም በማለት ነገሩን ለማጣጣል የሞከሩም ብዙዎች ናቸው። በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን የመጡ ሰሞን ኢትዮጵያ ድፍድፍ ነዳጅ ማውጣት ልትጀምር መሆኑንና ከነዳጅ የውጭ ሽያጭ በዓመትም ብዙ ገቢ እንደምታገኝ ተናግረው እንደነበር ያወሳሉ። ይሁን እንጂ የአንድ ሰሞን ወሬ ከመሆን ሊዘል አልቻለም።
በኢትዮጵያ ስንዴን እንደዋና ምግብ መጠቀም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመምጣቱ ይነገራል። በተለይም ከሕዝብ ብዛት እና ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የስንዴ ፍጆታ በየዓመቱ እንደሚያሻቅብ ነው የሚገለጸው።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዋሲሁን በላይ አንድን ምርት ወደ ውጪ ገበያ ለመላክ የግድ መትረፍረፍ የለበትም ሲሉ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለአስቸጋሪ የሰብዓዊ ድጋፍ ከዩክሬንና ሌሎች አገራት እርዳታ እየጠበቀች ያለች አገር ሆና ሳለ፣ የአገር ውስጥ የዋጋ ንረቱም አሳሳቢ ደረጃ ላይ በደረሰበት ሁኔታ ስንዴ ተርፏት ነው ወይ ለጎረቤት አገር (ኬንያ) ለመላክ ያቀደችው የሚለውን አንስተዋል።
አገሪቱ ስንዴ ለመላክ የሚያስችል ሁኔታ ላይ ነች የሚለውን ጥያቄ አንስተውም፣ የስንዴ እጥረት ለመኖሩ የዳቦ ዋጋ መናር ማሳያ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ስለሆነም፣ ‹‹ለሰብዓዊ ድጋፍ ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ ከውጭ ሊገባ እንደሚችል ይታወቃል። ከዚህ ይልቅ ግን ስንዴን በበቂ ሁኔታ አምርቶ መጠቀምና የአገር ውስጥ የዋጋ ንረቱን ማረጋጋት የሚለው በመርህ ደረጃ ያስኬዳል›› ነው ያሉት።
አክለውም፣ ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በርካታ ድክመቶች ያሉበት በመሆኑ፣ ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሸመታዎችን ያካሂዳል። እንደ መድኃኒት፣ ነዳጅ፣ የግንባታና የትምህርት ቁሳቁሶች እንዲሁም ሌሎች መሠረታዊ ፍጆታዎችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሬ በመፈለግ ሊሆን ይችላል፤ ስንዴ ወደ ውጪ ለመላክ የታቀደው።›› በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል።
ስንዴን ለውጭ ገበያ በማቅረብ መሠረታዊ ፍጆታዎችን ማስገባት ምክንያታዊ ሊሆን ይገባል። ነገር ግን ምርትን ወደ ውጪ በመላክ የተገኘውን ገቢ ከዚህ ውጭ ለሆነ አገልግሎት የሚውል ከሆነ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ቀውስ እንደሚፈጥር ነው የጠቆሙት።
ሆኖም ከውጭ ንግድ በሚገኝ ገቢ ላይ ብዙ የአጠቃቀም ጉድለቶች እንደሚታዩ እና ይህንን ማስተካከልም እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ስንዴን ወደ ውጭ ገበያ ለመላክ ከባድ ነው ያሉት ባለሙያው፣ ስንዴ ልኮ መልሶ ስንዴ የሚገዛ ከሆነ ጥያቄ ያስነሳል ብለዋል።
ትንሽ የምርት ዓይነቶችን በጥቂት መጠን ለውጭ ገበያ በማቅረብ ላይ ባለችው ኢትዮጵያ፣ ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ የተያዘውን ዕቅድ መሳካትም ቀላል እንዳልሆነ ሳይጠቅሱ አላለፉም። በመሆኑም ሚሊዮን የምግብ ተረጂዎች ባለቡት አገር ስንዴን ለውጭ ገበያ ለመላክ ማቀድ የሚጋጭ ነገር ስለመሆኑ በስፋት ትችቶች እየቀረቡ ነው።
የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት አቅም
አብዛኛው የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ከዝናብ ጋር የተገናኘ እንደሆነ ይጠቀሳል። በቅርቡ ግን ቆላማ አካባቢዎችም በመስኖ ስንዴ እንዲያለሙ እየተደረገ ነው። መንግሥት እንደሚለው በተለይ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ የስንዴ ምርት መጠን እያደገ ነው።
የግብርና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመላክተው በ2012 በመኸር እርሻ ከ53 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት የተገኘ ሲሆን፣ በ2013 ደግሞ ከ57 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ በላይ ተመርቷል።
በበጋ መስኖ የስንዴ ልማት በ2012 የምርት ዘመን በ20 ሺሕ ሄክታር መሬት 700 ሺሕ ኩንታል ምርት ሲገኝ፣ በ2013 ሺሕ ሄክታር መሬት ከ3 ሚሊዮን ኩንታል የላቀ ምርት ተገኝቷል።
በ2014 የምርት ዘመን ደግሞ ስንዴ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ያስችላል የሚል ተስፋ የሰጠና በኹለት ዙር በተደረገ የበጋ መስኖ ልማት ከ600 ሺሕ ሄክታር በላይ በሆነ መሬት ከ24 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል።
በ2014/2015 በአገር ዐቀፍ ደረጃ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት ከ50 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ለማምረት እቅድ ተይዟል። በመኸር ምርት ደግሞ 100 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት መሰብሰብ የሚያስችል የስንዴ ማሳ መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሰሞኑ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ ‹‹ራሳችን ጠግበን ‹‹Ethiopia Aid›› ብለን ጎረቤቶቻችንን መርዳት አለብን›› ሲሉም ተደምጠዋል።
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከፍተኛ የስንዴ ምርት ያላት መሆኗ ይነገራል። በአገሪቱ በየዓመቱ የስንዴ ምርት መጠን የሚጨምር ቢሆንም፣ ካለው ፍላጎት ጋር መመጣጠን እንዳልቻለ ነው የሚታወቀው። በዚህ የተነሳም በየዓመቱ አንድ አራተኛው የኢትዮጵያ ስንዴ ፍላጎት ከውጭ የሚገባ ሲሆን፣ ሩብ ያህሉ ደግሞ በእርዳታ እንደሚቀርብ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በቢሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ በየዓመቱ ከ10 ሚሊየን ኩንታል በላይ ስንዴ ከውጭ ታስገባለች ነው የሚባለው። በኢትዮጵያ ከአራት ሚሊዮን ሄክታር በላይ በመስኖ መልማት የሚችል መሬት እንዳለም ይታመናል። ካላት የቆዳ ስፋት 60 በመቶ የሚሆነውም ቆላማና ከደጋ ወንዞች በሚመጣ የደለል አፈር የተሞላ በመሆኑ ለምርት ምቹ መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ሲገልጹ ይሰማል።
ከኹለት ዓመት በፊት (2012) የአገሪቱ ዓመታዊ የስንዴ ፍላጎት 65 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከዚህ ውስጥ 48 ሚሊዮን ኩንታሉ በአገር ውስጥ ምርት የሚሸፈን ሲሆን፣ ቀሪውን 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ስንዴ ለማሟላት እስከ 700 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ታደርጋለች።
ሆኖም የስንዴ ምርት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ ከውጭ ምንዛሬ እንዲሁም ከበሽታ አምጪነት ጋር ተያይዞ ቅሬታዎች ይቀርባሉ። መንግሥትም በፈረንጆች 2023 ስንዴ ከውጭ ማስገባትን ለማቆም እየሠራሁ ነው ማለቱ ይታወሳል።
የስንዴን ምርትና ምርታማነት በአገር ዐቀፍ ደረጃ ለማሳደግ ምርጥ የስንዴ ዝርያዎችን፣ የተሻሻለ የሰብል አያያዝ ዘዴን፣ የማዳበሪያ ግብአት እንዲሁም ምርጥ ፀረ-ተባይና በሽታ መቆጣጠሪያ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚጠይቅም ይታወቃል።
ከዐስር ዓመት በፊት የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው፣ አፍሪካ በየዓመቱ 38 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለመግዛት 12 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ ታደርጋለች። ይህ አኃዝ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ መጠን ማደጉ ነው የሚገለጸው።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015


