“ግሸን እንደ እድሜዋ በዚህ ደረጃ መገኘት አልነበረባትም”

0
1108

ኢትዮጵያ በቅርስ እንዲሁም በታሪክ እንድትጎላ ካስቻሏት ሀብቶቿ መካከል በርካቶቹ የሚገኙት በሀይማኖት ተቋማት ውስጥ ነው። የሚጎበኙ ጥንታዊና የኪነሕንጻ ጥበብ የሚታይባቸው ስፍራዎችም ሆኑ አስደናቂና ዘመናት የተሻገሩ ድንቅ ታሪኮች አብዛኛውን የሚነሱት ከሀይማኖት ተቋማት ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ ሲነገርም በተለይ ከክርስትና እና ከእስልምና ሀይማኖት ጋር የተያያዙ እልፍ ታሪኮች ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንም እንዲህ ያለውን ትሩፋት ለኢትዮጵያ ካላበሱ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናት። አዲስ ማለዳ በመስከረም ወር መጨረሻ ግድም ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን አቅንታ ነበር። ከአንድ ሺሕ ዓመት በላይ ታሪክ ባለው በዚህ ቤተክርስትያን ውስጥ ምን አለ ስትልም የደብሩ አስተዳዳሪ ጋር ጎራ ብላ ጠይቃለች።

ወቅቱ ዓመታዊው ክብረ በዓል የሚከበርበት እንደመሆኑ፣ የአዲስ ማለዳው ቢንያም አሊ ከግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተክርስትያን አስተዳዳሪ አባ ለይኩን ወንድይፍራው ጋር ተከታዩን አጠር ያለ ቆይታ አድርጓል።

ግሸን ደብረ ከርቤ በጠቅላላ አሁን ያለችበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

ከቦታው ታሪካዊነትና ጥንታዊነት አኳያ አሁን ባለበት ደረጃ መምሰል ወይም አሁን ባለው መልክ መገኘት አልነበረበትም። ከ1 ሺሕ 500 ዓመት በላይ ታሪክ አለው። ከዛም አልፎ በሥነፍጥረት ጨምሮ ታሪክ ያለው ታላቅ ቦታ ነው። 1 ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ቆይታ ግሸን እንደእድሜዋ በዚህ ደረጃ መገኘት አልነበረባትም።

ከዛ ውጪ አሁን ጥሩ እንቅስቃሴዎች አሉ፤ ተስፋም አለው። ለምሳሌ ከተስፋዎቹ መካከል መንገድ አንዱ ነው። መንገድ ለዚህ ቦታ ትልቁና ወሳኝ ነገር ነው። ‹የመንገዱስ ነገር አይወራ› እየተባለ እየተዘመረ፣ የመንገዱ ክፋት እየተነገረ ነው የቆየው።

መንገዱ 19 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው፣ ስፋቱ 17 ሜትር የሆነ፤ የመኪናዎች መውጫና መውረጃ እንዲሁም ማቆሚያ (ፓርኪንግ)፣ የእግረኞች መንገድ ያለው የመንገድ ግንባታ ነው አሁን የተጀመረው። ከመገንጠያ ጀምሮ 6 ኪሎሜትር የቆረጣ ሥራ ተሠርቷል። አገር ሰላም ከሆነና ባለበት ከቀጠለ ከአንድ ዓመት በኋላ የተሻለ ሥራ እናያለን።

ከዛ ውጪ ግቢ ውስጥ ስንመለከት ቤተ መዘክር (ሙዝየም) አልነበረም፤ አሁን ተሠርቷል። ደረጃውን የጠበቀ ነው። ከጸጥታና መሰል ጉዳዮች አኳያ ምንም እንኳ የውስጥ ዝግጅት ቢቀረውምና ቅርሶቹን ለማስገባት ባይቻልም፤ የአጥር ሥራ ተጠናቋል። ቤተ መዘክሩ ከአገራችን ብሎም በክልላችን ካሉ ሙዝየሞች አንደኛ እንደሆነ የክልላችን ባህልና ቱሪዝም ባለሞያዎች አረጋግጠውልናል።

ሦስተኛ የእንግዳ ማረፊያ አልነበረንም። አሁን ያለው ኹለት ዓመት ያስቆጠረ ነው። ከዛ በፊት የነበረውን የሚያውቁ ሰዎች ያውቁታል። ይህኛው በአንድ ዓመት ከሦስት ወር ነው የተሠራው። 500 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈ ነው። 25 ክፍሎች አሉት። ቅዱሳን እና ብጹአን አባቶች ሲመጡ የሚያርፉበት፣ እንግዳ የምንቀበልበት ነው።

ከዛ ውጪ የቅዱስ ሚካኤል ቤተክርስትያን አለ። በጣም ግዙፍ ነው። በጥራትና በውበት ለየት ባለ መልኩ በገዳማውያን አባቶች እየታነጸ ያለ ቤተክርስትያን ነው። ከዚህ ከዚህ አንጻር ሲታይ አሁን ያለበት ደረጃ ይህን ይመስላል።

የገቢያችሁ ሁኔታ ምን ይመስላል?

እኔ እዚህ ከመጣሁ አምስት ዓመት ሆኖኛል። ከገቢ አንጻር ጥሩ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ እንደመጣሁ (2011) ጥሩ ነው የነበረው፣ 17 ሚሊዮን ብር ገብቶ ነበር። ከዛ በቀጣይ ዓመት ወደ 21 ሚሊዮን ደርሶ ነበር። በኮሮና 15 ሚሊዮን ወርዶ  አምና 10 ሚሊዮን ነው የገባው። እየቀነሰ ነው ያለው። የአሁኑን አናውቅም ግን እየተሻለ እንደሚመጣ ተስፋ እናደርጋለን።

ከችግሩም አንጻር እስከ ነሐሴ 30 ደሞዝ ከፍለን የመስከረም ወር ደሞዝ በአሁኑ ሰዓት የምንከፍለው አልነበረንም። 2014 ነሐሴ ደሞዝ ከፍለን መስከረም ምንም አልነበረንም። በመስከረም የሚመጣውን ሕዝብ ተስፋ አድርገን፣ በየሚድያው ቀስቅሰን ሕዝባችን መጥቶ በደስታ አክብረናል። የዓመት ደሞዛችንን እንደ ደሞዝ፣ ለመነኮሳቱም የሚመጣው ሕዝበ ክርስትያን ልብሳቸውን ጉርሳቸውን እንደሚሰጣቸው ተስፋ እናደርጋለን።

በግሸን አቅራቢያና አካባቢውስ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል?

በአጠቃላይ አምባሰልን የምትመግበው ግሸን ናት። እንደ ቤተክርስትያንም፣ እንደ ግልም። ግማሹ ቤት አከራይቶ፣ ግማሹ ነግዶና ጠላ፣ እንጀራ፣ ሻይና ዳቦ ሸጦ፤ ሌላው ተሸክሞ፤ በጣም ደካማው ደግሞ ለምኖ አምባሰል ከተማ ያሉ በአጠቃላይ በዚህ መንገድ ይጠቀማሉ። ደካሞች ለምነው፣ ጉልበት ያላቸው ተሸክመው፣ አቅም ያላቸው ነግደው የሚያተርፉበት፣ ባለሀብቶች ደግሞ ካላቸው ሀብት መጽውተው እዚህም መጥተው ፈሰስ አድርገው በቱሪዝም መልክ የሚጠቀሙበት ነው።

ግሸን ላይ እስከ አሁን የነበሩት አድባራት አምስት ናቸው። ቅርብ ቀን ከኹለት ዓመት በፊት ታች በረሃው ውስጥ አስፈንጣሪ አቡነ ገብረመንፈስ ቅዱስ የሚባል ቤተክርስትያን አለ። አገልጋይ በመጥፋቱ ምክንያት ተዘግቶ የነበረ ነው። እና ጽላቱ ወደ ግሸን መጥቶ ይግባ፣ ሰበካችን ግሸን ነው ብለው ሲያቀርቡ፤ በዘመናችን እንዴት ቤተክርስትያን ይዘጋል ብለን አሁን ስድስተኛ ሆኖ እንዲተዳደር አድርገናል። ዘጠኝ ሠራተኞችን መድበን እያስገለገልን እንገኛለን።

በአጠቃላይ አምባሰል ትልቁ ችግር ቁስ ወይም ነዋያተ ቅዱሳት ሳይሆን የሰው ችግር ነው። ቤተክርስትያን አገልጋይ የለም። ድሮ ግሸን ለኢትዮጵያ ቀርቶ ለዓለም ሊቃውንት የሚወጡባት ቦታ ነው የነበረችው። ሊቃውንት ብቻ ሳይሆኑ ነገሥታት እዚህ ተምረው ነው የሚወጡት። እነ አፄ ዘርዓ ያዕቆብ፣ አፄ በዕደማርያም፣ አፄ ናዖድ እና ሌሎችም ብዙ የኢትዮጵያ ነገሥታት እዚህ ቦታ መጥተው ተምረው ነው የአገር መሪ፣ የሃይማኖት መሪ ይሆኑ የነበረው። አሁን ግን ይህን ማስቀጠል አልተቻለም። ካለው ወቅታዊ ጉዳይ አንጻር።

መምህራን አሉ፣ ተማሪዎች ግን ሊኖሩ አልቻለም። የሚማሩበት መንገድ ስላልተመቻቸላቸው ማለት ነው። ይህ የሰው እጥረት በገጠር አካባቢ ያለ ነው እንጂ ግሸን ላይ አይደለም። በግሸን በአጠቃላይ 300 አገልጋይ አለ።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here