የአእምሮ ጤና ችግር እንደሌሎች ሕመሞች ትኩረት እየተሰጠው አለመሆኑን የሥነ አእምሮ አማካሪዎች ገልጸዋል። ‹‹በርካታ ሰዎች ደብሮኛል…ጨንቆኛል….›› ሲሉ ይደመጣሉ። ይሁን እንጂ ወደ አእምሮ ጤና ባለሞያዎች ጠጋ ብሎ መፍትሔ የመቅሰም ልምድ ዝቅተኛ መሆንና የአማካሪዎች ውስንነት ለአእምሮ ጤና ችግር መባባስ መንስኤ መሆኑ እየተነገረ ነው።
ባሳለፍነው መስከረም 30/2015 በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የአእምሮ ጤና ቀን መከበሩ ይታወሳል። ይህን መነሻ አድርገውም የዘርፉ ባለሞያዎች ‹‹ዓለም ዐቀፍ ትኩረት ለአእምሮ ጤናና ደኅንነት›› በሚል ርዕሰ ጉዳይ ተነስተው ችግሩ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የበኩላቸውን በመግለጽ ሰንብተዋል።
ከዚሁ ጋር በተገናኘም አዲስ ማለዳ የአእምሮ እና የሥነልቦና አማካሪዎች ጋር ቆይታ አድርጋለች።
የሥነ ልቦናና ምክር የሚሰጡት ቴዎድሮስ ድልነሳው ከስምንት ሰው አንድ ሰው የአእምሮ ጤና ሕክምና እንደሚያስፈልገው የዓለም አእምሮ ጤና ፋውንዴሽን ጥናት እንደሚያሳይ ይናገራሉ።
‹‹ይህ ማለት ደግሞ በዓለም ውስጥ ከስምንት ቢሊዮን ሰው፤ አንድ ቢሊዮን ሰው የአእምሮ ጤና ክትትል ይፈልጋል ማለት ነው።›› ሲሉም በዝርዝር አስረድተዋል።
በርካታ ሰዎች ‹‹አእምሮዬ ተወጠረ። ዛሬ በጣም ደብሮኛል። በቃ የትም መሄድ፤ ምንም ማድረግ አልፈልግም›› ሲሉ ይደመጣሉ። አንዳንዶች ጭንቀት ሲያስቸግራው ወደ ጤና ተቋም ጎራ በማለት ፈንታ በአደንዛዥ እጽ እና በአልኮል መጠጥ ሲደበቁ ይስተዋላሉ።
ይህንኑ ተግባር በተመለከተም ቴዎድሮስ የሚከተለውን ብለዋል። ‹‹ከስምንት ቢሊዮን ሰው አንድ ቢሊዮን ሰው የአእምሮ ጤና ክትትል ቢያስፈልገውም፤ ሕክምና የሚያገኘው ሰው ደግሞ የዚህ አንድ ዐስረኛው እንኳ አይሆንም። ምክንያቱም ሰው የአእምሮ መረበሽ ሲሰማው ድባቴና ጭንቀት ስለሆነ የእኔ ችግር ነው ብሎ ከቤቱ ይቀመጣልና ነው››።
ሰው አብዛኛውን ጊዜ የአእምሮ ጤና ችግር አለ ብሎ የሚገነዘበው አንድ ሰው ልብሱን ሲጥል (ሲያብድ) እና አማኑኤል ሆስፒታል ሲገባ ብቻ መሆኑም ተነስቷል። በመሆኑም ሰው ለአእምሮ ጤና ያለው ግንዛቤ እምብዛም መሆኑ ነው የተጠቆመው።
የአእምሮ ጤና ማለት ሊያሳስበን የሚገባ የጤና ዓይነት ነው ያሉት ቴዎድሮስ፤ ሕዝብ አእምሮው ጤናማ ካልሆነ ኹሉም አካሉ ጤናማ እንደማይሆን በጀበና እና ማቶት መስለው ዳዊት ወንደማገኝ ያስቀመጡትን ማብራሪያ አንስተዋል።
የዳዊት ወንድማገኝ ማብራሪያም እንዲህ የሚል ነው፤ ‹‹ለምሳሌ ጀበና አለ። ጀበና ማቶት ላይ ይቀመጣል። በዓለም ውስጥ ያለው ማኅበረሰብ በጀበና፤ ማቶቱ በአእምሮ ጤና ቢመሰል። ማቶቱ እክል ካለበት ጀበናው ሲቀመጥ ይዋልላል፤ ይወድቅማል። አእምሮው ጤናማ ያልሆነ ሕዝብም እንዲሁ ነው።›› የሚል ምሳሌ መሆኑን ቴዎድሮስ አብራርተዋል።
በመሆኑም አእምሮ ሁሉንም አካል አንቀሳቃሽ ስለሆነ ጤና ሲያጣ አስተሳሳብም ኹሉም አካል ጤና ማጣቱ አይቀሬ በመሆኑ መንስኤዎቹን አጢኖ የአእምሮ ሕክምና ማግኘት እንዲሁም ወደ ጤና ተቋም ጎራ ማለት ግድ ይላል ነው የተባለው።
ጫሪ ምክንያቶች
ማንኛውም ዓይነት የጤና ችግር ያለምክንያት አይፈጠርም። የሥነ ልቦና ይሁን የአእምሮ እክሎችም የራሳቸው የሆኑ ጫሪ ምክንያቶች እንዳሏቸው የሥነ አእምሮ አማካሪዋ ቃልኪዳን ኃይሉ ይናገራሉ። ዋና ዋና ያሏቸውን አራት ነጥቦችንም እንዲህ አንስተዋል።
በሰውነት አካል ላይ በተፈጥሮ የሚመጣ የአእምሮ ውቅር መዛባት አንደኛውና የመጀመሪያው ነው። በተፈጥሮ የሚመጡ ምክንያቶችም በሆርሞን መዛባትና ሌሎች ምክንያቶች የሚከሰቱ እንደ ኦቲዝም ዓይነት ሕመም መሆኑን ቃል ኪዳን አብራርተዋል።
ሥራ ማጣት፤ የሥራ መደራረብ፤ በጦርነት ውስጥ ዘግናኝ ድርጊቶችን ማሳለፍ እና ሌሎች መሰል ክስተቶች አእምሮን ለጤና ችግር የሚዳርጉ በኹለተኛ ደረጃ የተጠቀሱ ምክንያቶች ናቸው። በተለይም ተመራቂ ተማሪዎች ሥራ ባለማግኘታቸው ሲጨናነቁና ሲበሳጩ ይስተዋላል። የሥነ አእምሮ አማካሪዋ በበኩላቸው፣ ይህን ክስተት የአእምሮ የጤና እክል እንዲገጥም ከሚያደርጉ ጫሪ ምክንያቶች መካከል ይገኝበታል።
ሌላኛውና ሦስተኛው ጫሪ ክስተት እንደ ጭንቀት ዓይነት በዘር የሚተላላፍ ሕመም ነው ተብሏል። ከስፕሪቹዋል (ከእምነት) ጋር በተያያዘ ሊመጡ የሚችሉ የአእምሮ ሕመሞችም አይጠፉም ብለዋል፤ ቃልኪዳን።
ጦርነትና የአእምሮ እክል
የአእምሮ ጤና እክል ከአስተሳሰብ ጋር እንደሚተሳሰርና በተለይም በጦርነት ወቅት ደግሞ የማኅበረሰቡ አስተሳሰብ የተዛባ ስለሚሆን የአእምሮ የጤና ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ተገልጿል።
የግለሰብ የአእምሮ ጤና ከማኅበረሰብ አስተሳሰብና የኑሮ ሁኔታ ጋር ይያያዛል ያሉት ቴዎድሮስ፤ ጦርነት ማኅበረሰብ በልቶና ጠጥቶ እንዳያድር፤ ደኅንነት እንዳይሰማው የሚያደርግና በዚህ ወቅት ደግሞ ላምልጥ ወይም ልጋፈጥ በሚል ውጥንቅጥ ያለፈ ሕዝብ አእምሮው ላይ እክል ሊገጥመው እንደሚችል አብራርተዋል።
ሰላም መደፍረስ ባለባቸው በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘን የሚገኙ ሰዎች ፍርሃት፤ ጭንቀት እንዲሁም አለመረጋጋት እንደገጠማቸው ይናገራሉ።
ባሳለፍነው ሳምንት በጋምቤላ እና ኦሮሚያ ክልል (በቄለም ወለጋ) አዋሳኝ በሆነችው በአንፊሎ ወረዳ ሙጊ ከተማ ውስጥ የኦነግ ሸኔ ከበባ አድጎ ነበር። የሙጊ ከተማ በታጣቂዎች መከበቧን ተከትሎ በ68 ኪሎ ርቀት የሚገኙ አንዳንድ የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ‹‹ታጣቂዎቹ ይመጡብናል›› በሚል ጭንቀት ቀድመው እየተናጡ ስለመሆናቸው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በምሥራቅ ወለጋ ኡኬ ከተማ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪ ‹‹ጎረቤቶቼ በታጣቂዎች ሲታረዱ አይቼ አእምሮዬ ተረበሸ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አእምሮዬ በትክክል ሥራውን እየሠራ አይመስለኝም። ጭንቀት እና ፍርሃት ጠፍሮ እንደያዘኝ ይሰማኛል።›› ብለዋል።
በሰሜኑ ጦርነት ቀጠና የነበሩ እና ያሉ ሰዎች በበኩላቸው ሕይወታችን በመከራ ተሞልቷል። ‹‹የጨነቀ ነገር አግኝቶናል።›› ሲሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማሉ።
በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ወረዳ ደጋማው ክፍል አምዴ አምባ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉ አንዲት እናት እንዲህ አሉ።
‹‹የሕውሓት ታጣቂዎች መጥተው ባልሽ የት ነው፣ መሣሪያውን የት ደበቀው ብለው ጠየቁኝ። ኧረ የት እንዳለ አላውቅም። መሣሪያም የለውም የሚል ምላሽ ሰጠሁ።›› አሉ። ከዚያ በኋላ የሆነውን ነገር ደግሞ ‹‹አንድ ታጣቂ ከጎሮሮዬ ጀምሮ እስከ ደረቴ ድረስ ቀስ እያደረገ አንገቴን በምላጭ ተለተለው። ደማሁ። በመጨረሻም ሳይገድለኝ ጥሎኝ ሄዴ። ከሕመሙ፣ ከደሙና ከቁስሉ በላይ ግን እስካሁን ድረስ አልቀረፍልሽ ያለኝ ፍርሃት ነው። አእምሮዬ እንደ እስከዛሬው አይደለም። ደኅንነት ርቆኛል።›› ብለዋል።
የሥነ አእምሮ አማካሪ ቃልኪዳን ኃይሉ በበኩላቸው ጭንቀት፤ ፍርሃት እንዲሁም በአጠቃላይ አንድ ሰው ደኅንነት አልሰማው ሲል አእምሮ ላይ የጤና እክል እንደሚያጋጥም ጠቁመዋል።
በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ችግር ሲያጋጥም ወደ የሥነ አእምሮ እና የሥነ ልቦና አማካሪዎች ጋር መገናኘትና ምክር ማግኘት ብሎም ወደ ጤና ተቋም ጎራ ብሎ ሕክምና መውሰድ ይገባል ሲሉ የመፍትሄ አቅጣጫ ሰጥተዋል።
የሥነ ልቦና አማካሪው ቴዎድሮስ ድልነሳው በበኩላቸው፣ በዚሁ ጉዳይም ሐሳባቸውን አካፍለውናል። ቴዎድሮስ በእርግጥ የአእምሮ ጤና እክል የሚገጥመው በጦርነት ቀጠና ውስጥ የነበረና ያለ ሰው ብቻ እንዳልሆነ ነው በመጀመሪያ የጠቀሱት። በጦርነት ውስጥ ሆኖ ጤናማ፤ ሰላም በሰፈነበት ቦታ ሆኖ ደግሞ የአእምሮው ጤና እክል ያለበት ሰውም እንደማይጠፋ አነሱ።
ይሁን እንጂ፣ ለአእምሮ ጤና እክል ጦርነት እንደ አንድ መንስኤ ሊሆን ይችላል ብለው፤ እንዲህ ዓይነት ሰዎች በፍጥነት ሥነ ልቦና ምክር ያሻቸዋል ነው ያሉት።
አብዛኛው ሰው የአእምሮ ጤና እክል ሲገጥመው ቀድሞ ወደ ሀይማኖት ቦታ ሲሄድ ይስተዋላል። ይህ መልካም ቢሆንም፤ የአእምሮ ጤና ሕመም ዓይነቱ ብዙ በመሆኑ በሕክምና ሊድን የሚችልበት አጋጣሚም አለ ነው የተባለው።
እንደ ቴዎድሮስ ገለጻ ከሆነ፤ ሕክምና ማግኘት ያለበት አንድ የአእምሮ ጤና ችግር የገጠመው ሰው፤ ቀድሞ ወደ እምነት ቦታ ሊሄድ ወይም ዝም ብሎ ከቤቱ ሊቀመጥ ይችላል። ይሁን እንጂ፣ እያደር ሕመሙ እየከረረ የሚመጣበት አጋጣሚ ሲፈጠር፤ ወደ ሕክምና መምጣቱ አይቀርም። ያኔ ግን ሊረፍድ ወይም በአጭር ጊዜ ውስጥ አእምሮው ወደ ነበረበት መመለስ ሲቻል ለረጅም ጊዜ ስቃይ ሊዳረግ የሚችልበት አጋጣሚ ይፈጠራል ሲሉ ገልጸዋል።
ተኝቶ መታከም የሚያስፈልገው የአእምሮ ሕመም አለ ያሉት ቴዎድሮስ፤ እንዲህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች ወደ ጤና ተቋማት የመሄድ ልምዳቸው አናሳ ከመሆኑም ባሻገር ተቋማትም ቢሆኑ ለአእምሮ ጤና ችግር ትኩረት ሲሰጡ አይስተዋልም ብለዋል።
ለአብነትም በአማኑኤል ሆስፒታል የነበረ አእምሮ ሕሙማን አልጋ በጦርነቱ ለተጎዱ ቁስለኞች ተብሎ እንደተወሰደ ጠቁመው፤ ይህ የሚያሳየው ለአእምሮ ሕመም እምብዛም ትኩረት እንደማይሰጥ መሆኑን ነው ብለዋል።
አንድ ሚሊዮን ሕዝብ ተኝቶ መታከም የሚያስገድደው የአእምሮ ሕመም እንዳለበትና ያለው አልጋ ግን ከ700 እንደማይበልጥ ይነገራል። በመሆኑም የአእምሮ ጤና ችግርን የአገር ትኩረት ልናደርገው እንደሚገባ ነው ቴዎድሮስ የገለጹት።
ሞት፤ የሰዎች መደፈር እና ሌሎች መሰል ድርጊቶች ለአእምሮ ጤና ችግር መንስኤ መሆናቸውንም ቴዎድሮስ ሳያብራሩ አላለፉም። ሆኖም ግን በተጓዳኝ ደግሞ የሰው ልጅ ማንኛውንም ዓይነት ችግር ተጋፍጦ የማለፍና የማሸነፍ ሙሉ አቅም አለው ነው ያሉት።
ሱዛን ጀፈርስ የተባሉ ጸሐፊ ‹‹ፍርሃትን አትፍራው›› በሚል መጽሐፋቸው በጦርነት ወቅት ጭንቀትና ፍርሃትን ለማስወገድ ማድረግ የሚገባው አንድ ነገር ብቻ ነው ይላሉ። ይኸውም፤ ችሎታንና በራስ መተማመንን እያዳበሩ በመምጣት በጉዞ ላይ የሚገጥመውን መጥፎ ነገር ኹሉ መቋቋም ነው።
በተያያዘም፤ ፍርሃትና ጭንቀትን ማስወገጃ ብቸኛው መንገድም መጋፈጥ ስለመሆኑ በመጽሐፉ ተብራርቷል።
ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሥነ ልቦና አማካሪዎቹ በተለይም ጦርነት ባለበት አካባቢ ተገዶ የመደፈር ድርጊት የተፈጸመባቸው ሰዎች ራሳቸውን ማጥፋት እንደሚቀናቸው ገልጸው፤ ራስን ማጥፋት የመሸነፍ ምልክት በመሆኑ ሊወገዝ እንደሚገባውም መክረዋል።
ራስን ማጥፋት
በጦርነት ወቅት ይቅርና በሰላሙ ጊዜም ሴቶች በወንዶች ‹‹ተደፈሩ›› የሚል ወሬ ለብዙዎቻችን ጆሮ እንግዳ ነገር አይደለም።
ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ሕጻናት እንዲሁም በእድሜ ትልቅ የሆኑ ሴቶች በቅርብ ቤተሰቦቻቸው የተደፈሩበት ጊዜም አለ። ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባበት 2012 ሚያዚያ ወር ቀጥሎ ባሉት አራት ወራት ብቻ 101 ሕጻናት በአባቶቻቸውም ጭምር መደፈራቸውን የአዲስ አበባ ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ በወቅቱ መግለጹ ለአብነት ተጠቃሽ ነው።
በ2014 በነበረው የኢትዮጵያ መንግሥትና የሕወሓት ጦርነት በ9 ቀናት ብቻ 70 ሴቶች እንደተደፈሩ መሰማቱም አይዘነጋም።
አሁን አሁን ደግሞ በተለይም ከጦርነት ጋር በተያያዘ ወንዶች ተገደው ተደፈሩ የሚል ሰበር ዜና እየተሰማ ነው። በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎች መልሶ የማቋቋምና ግንባታ ፈንድ ጽሕፈት ቤት ከሰኔ 2013 እስከ ታህሳስ 2014 ባካሄደው ጥናት 29 ወንዶች በታጣቂዎች እንደተደፈሩ ይፋ አድርጓል።
በሦስተኛው ዙር ጦርነትም ገና በጥናት ላይ የሚታወቅ ተመሳሳይ ችግር ስለመኖሩ እየተመላከተ ነው። ይህ ዓይነት ችግር የገጠማቸው አንዳንድ ሰዎችም ራሳቸውን ለማጥፋት ሲሞክሩ እየተደረሰባቸው መሆኑን በጦርነት ቀጠና ውስጥ የነበሩ ሰዎች ይናገራሉ።
ሰዎች ራሳቸውን ማጥፋት ቀና መንገድ የሚመስላቸው አእምሯቸው ልክ ስላልሆነና አስተሳሰባቸው ስለተዛባ መሆኑንም ምሁራን ይናገራሉ። የአእምሮ ጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ችግሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርስ ራሳቸውን ማጥፋት የሚቀናቸው በጭንቀትና በብስጭት አእምሯቸው ደኅንነቱን ሲያጣ አስተሳሰባቸው ስለሚዛባ መሆኑን ቴዎድሮስ ድልነሳው ተጨማሪ ሐሳብ ሰጥተዋል።
ይሁን እንጂ እንዲህ ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች ራስን ማጥፋት መቼም መፍትሄ ሆኖ እንደማያውቅ በመገንዘብ፤ ቤተሰቦቻቸውና የቅርብ ጓደኞቻቸው የተለያዩ እርዳታ በማድረግ፤ ከጎናቸው አለመራቅ እንዲሁም ወደ ሥነ አእምሮና ሥነ ልቦና አማካሪዎች ወስዶ ምክር እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል ሲሉ መክረዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015



