በአፋር ክልል ከጦርነት ጋር በተያያዘ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚሆን የመድኃኒትና የውኃ እጥረት ከፍተኛ መሆኑን የክልሉ አደጋ ስጋት አመራርና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።
ኮሚሽኑ በድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት የተነሳ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን የሚደርሱ የክልሉ ዜጎች የምግብ አቅርቦት ክፍተት አለባቸው ያለ ሲሆን፣ በተለይ የመድኃኒት፣ የውሃ እንዲሁም የመጠለያ ችግሩ ግን የከፋ ነው ብሏል።
የአፋር ክልል አደጋ ስጋት አመራርና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን ኮሚሽነር መሐመድ ሁሴን፣ ከክልሉ ሕዝብ 77 በመቶ ያህሉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በጦርነት፣ ድርቅና ጎርፍ ምክንያት የምግብ ዋስትናው አደጋ ውስጥ የገባ መሆኑን ጠቅሰው፣ የመድኃኒትና የውኃ እጥረቱ ግን መቶ በመቶ በሚባል ሁኔታ ችግሩ አልተቀረፈም ነው ያሉት።
የጤና ችግሩን ለማቃለል ተንቀሳቃሽ የጤና ማዕከላትን በማቋቋም የመድኃኒት ስርጭትና በሽታ የመከላከል ሥራ በተወሰኑ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት እንዲሁም በመንግሥት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም፣ አሁንም ከፍተኛ ችግር እንዳለ ያሳያል ብለዋል።
አካባቢው ሞቃታማና ደረቅ መሆኑን ተከትሎም፣ ከፍተኛ የውኃ እጥረት በመኖሩ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ውኃ በተሽከርካሪ ለማድረስ እየተሞከረ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም ችግር በጣም የከፋ እንደሆነ ተናግረዋል።
ስለዚህ ማኅበረሰቡ የተለያየ ዓይነት የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ የሚሻ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፣ ችግሩ ከክልሉ አቅም በላይ ነው። በተለይም በጤና፣ በውኃ እንዲሁም በሴቶች እና ሕጻናት ምገባ ዙሪያ የጎላ ክፍተት አለ። የዓለም ዐቀፍ ተቋማት ተሳትፎም አናሳ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
በውኃ፣ መድኃኒት እና መጠለያ እጥረቶችም ተፈናቃዮች ለተለያዩ የጤና እና የሥነልቦና ቀውስ እየተዳረጉ መሆኑን ገልጸው፣ የምግብ አቅርቦት በአንጻራዊነት የተሻለ መሆኑን አመላክተዋል። በዚህም ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ጋር በመተባበር በጦርነቱ ለተፈናቀሉ 650 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ምግብ እየቀረበ ይገኛል ነው ያሉት።
በተለይ በክልሉ ፈንቲ ረሱ እና ኪልበቲ ረሱ ዞኖች ላይ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ተደጋጋሚ ጥቃት በማዳረሱ ከፍተኛ ቀውስ ማስከተሉን ገልጸዋል። ሕወሓት በአፋር ክልል ባደረሰው ተደጋጋሚ ጥቃትም የአሁኑ አራተኛ ዙር ወረራ ነው ሲሉ ጠቅሰው፣ በዚህ ዙር ብቻ ከ160 ሺሕ በላይ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ አንስተዋል።
ለትግራይ ክልል ቅርበት ባላቸው በርሃሌ፣ አብአላ፣ ያሎ እና መጋሌ በተሰኙ የአፋር ክልል ወረዳዎች የሚኖሩ ዜጎች ሕወሓት በክልሉ በከፈተው አራተኛው ዙር ጦርነት በስፋት መፈናቀላቸው ተገልጿል።
የተፈናቀሉ ዜጎች በተደጋጋሚ ወደ ቀያቸው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም፣ ጦርነቱ ሙሉ ለሙሉ ሊቋጭ ባለመቻሉ ለሦስተኛ እና አራተኛ ጊዜ መፈናቀላቸውም ነው የተመላከተው።
ማኅበረሰቡ ከቀዬው በመፈናቀሉ የሚደርስበት ችግር የከፋ በመሆኑ፣ ወደ መኖሪያ ቦታው መመለስ ይፈልጋል። ሆኖም ግን በመሀል የተወሰነ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ የሚቆይ ቢሆንም፣ ግጭቱ ተመልሶ በማገርሸት ሕዝቡ ለተደጋጋሚ መፈናቀል እየተዳረገ ነውም ተብሏል።
በዚህም አብዛኛው የክልሉ ነዋሪ ከፍተኛ የሆነ ቀውስና ተደጋጋሚ ችግር ውስጥ ያለ ማኅበረሰብ መሆኑ ተመላክቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015



