ኦሮሚያ ክልል በውሉ መሠረት ክፍያው ለተጠናቀቀ መሬት ድጋሚ ክፍያ እየተጠየቀ ነው ተባለ

0
920

በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ የመኖሪያ ቤት ግንባታ መሬት ለማግኘት የተደራጁ 480 ሰዎች በውላቸው መሠረት ለካሳ የሚሆን የመሬት ክፍያ ቢያጠናቅቁም ለሦስተኛ ጊዜ ክፈሉ እየተባሉ ስለመሆናቸው አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

ለቤት ግንባታ የሚሆን መሬት ለማግኘት ከተደራጁት 480 ሰዎች መካከል 96ቱ መምህራን ናቸው። መምህራኑ እንደሚሉት ከሆነ፤ በውላቸው መሠረት እያንዳንዱ ሰው ለአርሶ አደሮች ካሳ ተብሎ ከሰባት ዓመት በፊት ሰባት ሺሕ ብር ለዶዶታ መሬት አስተዳደር ከፍሏል። እያንዳንዱ ሰው ሰባት ሺሕ ብር ከፍሎ ከጨረሰ በኋላም መሬቱ እንደሚሰጣቸው ውላቸው እንደነበር ይናገራሉ።

ነገር ግን መሬት አስተዳደሩ ለካሳ የሚሆን ብር ለኹለተኛ ጊዜ እንዲከፍሉ መምህራኑን በመጠየቁ፤ እያንዳንዱ ሰው 19 ሺሕ 200 ብር በድጋሚ ለመክፈል ተገዷል። ይህ በእንዲህ እያለ ለሦስተኛ ጊዜ 25 ሺሕ ብር ክፈሉ ተብለናል ሲሉ ነው ቅሬታቸውን የገለጹት።

ለሦስተኛ ጊዜ ክፍያ ጠይቀዋል የተባሉት የዶዶታ ወረዳ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት እና የመሬት አስተዳደር እንደሆኑና የተደራጁትን ሰዎች ብር ክፍሉ ያሉት ለካሳ የሚሆን ነው እንዳሏቸው ጠቅሰዋል።

በውላቸው መሠረት ክፍያ ቢያጠናቅቁም መሬት ሊሰጠቸው ሲገባ ድጋሚ ለካሳ ብር ክፈሉ የተባሉት በአራት ቡድን ከተጀራጁት 96 መምህራን በተጨማሪ ሌሎች ተመሳሳይ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች መኖራቸውም ተመላክቷል።

384ቱ ተመሳሳይ ቅሬታ ያላቸው ሰዎች በበኩላቸው፣ በመጀመሪያ እያንዳንዱ ሰው ለካሳ የሚሆን 35 ሺሕ ብር ከፍሎ መሬት ለመቀበል እየተጠባበቁ ነበር። ሆኖም ግን መሬቱን ማግኘት በሚገባቸው ወቅት እንደገና እያንዳንዱ ሰው 25 ሺሕ ብር እንዲከፍል መዘጋጃ ቤት እየጠየቀ ነው ተብሏል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በገለጹት መሠረት እስካሁን እስከ 16 ሚሊዮን ብር ቢከፍሉም መሬታቸውን ግን እንዳልተቀበሉ ነው ማወቅ የተቻለው።

ለወረዳው መሬት አስተዳደርና ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ለምን ድጋሚ ክፍያ እንደሚጠየቁ ጥያቄ ሲያቀርቡም ‹‹ብራችሁ ተበልቷል። የበላውም ከእኛ በፊት የነበረ አስተዳደር ነው። ስለዚህ አሁን ለካሳ ክፍያ የሚሆን ብር የለንም ጨምሩና እንሰጣችኋለን።›› ስለመባላቸውም ተናግረዋል።

አቤቱታ አቅራቢዎቹ፤ ጉዳዩን ለአርሲ ዞን አሳውቀው፤ ዞኑ በድጋሚ መክፈላቸው ስህተት ስለመሆኑ ገልጾ መሬታቸው እንዲሰጣቸው የሚል ደብዳቤ አስይዞ ወደ ወረዳው እንደመለሳቸው አንስተዋል።

የግንባታ መሬት ለማግኘት የተደራጁት ሰዎች እንደሚሉት ለዞኑ ካሳወቁ በኋላም የዶዶታ ወረዳ መሬት አስተዳደር አሁንም መሬታቸውን ሊሰጣቸው ፈቃደኛ አለመሆኑን ነው።

መሬት አስተዳደሩ መሬታቸውን መስጠት ባለበት ወቅት ለኹለተኛና ሦስተኛ ጊዜ ክፍያ የሚጠይቃቸውም የቀድሞ ኃላፊዎች ብሩን ለግል ጥቅማቸው ስላዋሉት አርሶ አደሮች ካሳ ባለማግኘታቸው መሆኑን አብራርተዋል።

በመሆኑም፤ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የቀድሞ ኃላፊዎች ብሩን ለግል ጥቅም ቢያውሉም ለካሳ የሚሆን ብር በውላቸው መሠረት ከፍለው በማጠናቀቃቸው መሬቱን ማግኘት ይገባናል ባይ ናቸው።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከወረዳውን መሬት አስተዳደር ምላሽ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ስልካቸውን ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምላሻቸውን ማሳካት ሳይሳካ ቀርቷል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ በጠቆሙት መሠረት እንዲጠየቅላቸው የፈለጉት የዴራ ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ኑራ ሑሴንን ሲሆን፤ እሳቸውም ስልካቸውን ለማንሳት ፈቃደኛ አልሆኑም።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here