የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች አብዛኞቹ መሠረታዊ የሚባሉ ግብዓቶችን ያላሟሉ መሆናቸው ሲነገር ይሰማል። በተለይ በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ግዛቶች የሚገኙ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች በጣም የተጎሳቆሉ እንደሆኑ ይታያል። ከመካከላቸው ትምህርት ቤት ለመባልም ደረጃውን የማያሟሉ እንደሚገኙባቸው በምስል ጭምር መረጃዎች ሲወጡ የነበረበት ሰሞን ነበር።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው የሰሜኑ ጦርነት፣ የደቡብና ምሥራቁ ድርቅ እንዲሁም የኑሮ ውድነት ቋፍ ላይ የነበረውን የትምህርት ተደራሽነትን ወደ ገደል እንደከተተው የሚናገሩ አሉ። ከድጡ ላይ ሲንሸራተት የነበረው የትምህርት ጥራትም ከማጡ አረንቋ ገብቶ መንቀሳቀስ እንዳይችልም ያደረጉት በርካታ ምክንያቶች ነበሩ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የትምህርት ጥራትንም ሆነ ተደራሽነትን ለማሳደግ በሚል የተወሰዱ እርምጃዎች የተወሰኑት ፍሬ ሲያፈሩ የተወሰኑት ደግሞ ባክነው መቅረታቸው ይነገራል። ከፍተኛ በጀት እየተመደበ ዘመናዊ ትምህርት ቤቶችን እልም ባሉ ገጠሮች ጭምር ለመገንባት የተያዙ እቅዶች በተወሰኑ ክልሎች ላይ በከፊል ውጤታማ ሲሆኑ፣ በተለይ ድርቅና ጦርነት ባለባቸው ደግሞ ችግሩ መባባሱ ሲዘገብ ቆይቷል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም በአማራ ክልል በዳስ ውስጥ የሚማሩበት፤ የዛፍ ጥላን ትምህርት ቤት የሚሉ፣ መቀመጫና መማሪያ የሌላቸው በርካታ ትምህርት ቤቶች እንዳሉ አንድ ሰሞን የፖለቲካ ፍጆታ ማሟያ ተደርገው በምስል ጭምር ከቀረቡ በኋላ አብዛኛው ከተሜ ችግሩን በከፊልም ቢሆን ለመረዳት ችሏል።
በከተማ ብዙ አማራጭ እያየ የሚያስተምር ወላጅ የመብዛቱን ያህል፣ ረጅም ተጉዘውም በበቂ ሁኔታ ልጆቻቸውን ማስተማር የማይችሉ ወላጆች መኖራቸውን የተረዳ የማኅበረሰብ ክፍል የእርዳታ እጁን ለመዘርጋት ጊዜ አልወሰደበትም ነበር። በርካታ ባለሀብቶች በግላቸውም ይሁን በቡድን አልያም ገንዘብ በመለገስ የተለያዩ ትምህርት ቤቶችን ማስገንባታቸውን ስንሰማ ቆይተናል።
ይህ ቢሆንም ግን አሁንም በርካታ ትምህርት ቤቶች ትምህርት አቋርጠዋል፤ የተወሰኑ ተማሪዎቻቸው እጅጉን ቀንሰዋል። አንዳንዶች ደግሞ ይበልጥ ለችግር ተዳርገው አማራጭ ያጡ ተማሪዎቻቸውን አንበትንም ብለው ባላቸው አቅም ያስተናግዳሉ።
በጦርነቱ የወደሙትን መልሶ ለመገንባት የሚያስፈልገውን የትየለሌ ገንዘብን ከማግኘት ይልቅ፣ ጦርነቱ ተባብሶ በቀጠለበት ኹኔታ በጀት እየታጠፈ ወደ ጦር ግንባር መወሰዱ ይበልጥ ችግሩን አወሳስቦታል።
በገጠሪቱ የኢትዮጵያ ክፍል አንድ ወላጅ አራትና አምስት ልጆችን አስተምሮ ለቁምነገር ለማብቃት ይቅርና፣ አንድ ልጅን እንኳን ሁሉን አሟልቶ ለማስተማር አቅም ምን ያህል እንደሚፈትነው በቅርብ ያየውና በውስጡ ያለፈ ይረዳዋል።
የገጠሩ ነዋሪ በግብርና ሥራው አልያም በከብት ጥበቃ የሚረዱትን ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ የሚያየው ፍዳ እንዳለ ሆኖ፣ በመከራ ያስተማራቸው ልጆቹም ለውጤት እንዳይበቁ ከሰሞኑ እንደታየው የፖለቲካውም ሆነ የጊዜው አስተሳሰብ የሚያሳድረው ተፅእኖን ለሚገነዘብ ሰው እየሆነ ያለው ነገር እጅግ ያሳዝናል።
ሆዳቸው ባዶ ሆኖ ትምህርት ለመማር ሲሉ ርቀት ያለው መንገድን በእግር ተጉዘው በጉስቁልና ተምረው የሚመለሱ ታዳጊዎችን ለመመልከት፣ መውጫና መግቢያ ሰዓታቸው ላይ በእነዚህ የገጠር ትምህርት ቤቶች አቅራቢያ ተገኝቶ መመልከቱ በቂ ነው።
አዲስ ማለዳ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ በግሸን ጎጥ ተገኝታ በቀበሌው ከሚገኙ አራት ትምህርት ቤቶች በተማሪ ቁጥርም ሆነ በአቅም የተሻለ ነው የተባለውን የመንበረ ፀሐይ ቁጥር አንድ ትምህርት ቤትን ተመልክታለች።
ትምህርት ቤቱ በግሸን አምባ ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ ከመሰሎቹ በተሻለ አጥርና መማሪያ ክፍሎች ያሉት ነው። የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር ዘውዱ ፍስኃን አግኝታም ስለትምህርት ቤቱ ኹኔታ ጠይቃለች።
ከ350 በላይ መደበኛና 80 የሚሆኑ ቅድመ መደበኛ ተማሪዎችን የሚያስተናግደው ይህ ትምህርት ቤት በ2005 ነበር አንደኛ ደረጃ ሙሉ ሳይክል ትምህርት ቤት ተብሎ እስከ ስምንተኛ ክፍል እንዲያስተምር የተደረገው። አማራጭ መሠረታዊ ትምህርት ጣቢያ ተብሎ በ1996 ከመመሥረቱ በፊት በአካባቢው ምንም ዓይነት ዘመናዊ ትምህርት ቤት አልነበረም። እንደ ርዕሰ መምህሩ ገለጻ ዳር ላይ ከሚታዩ የጭቃ ቤቶች በስተቀር ምንም አልነበረውም።
ትምህርት ቤቱ በርካታ የሚባሉ ችግሮች አሉበት ያሉን ዘውዱ፣ አንገብጋቢው መማሪያ ቁሳቁስ መሆኑን ጠቁመዋል። ከሌሎች የአካባቢው ትምህርት ቤቶች በተሻለ ብዙ ተማሪ የሚያስተናግደው፣ ዓመታዊ የግሸን ደብረ ከርቤ ማርያም በዓልን ለማክበር የሚመጡ ሰዎች ትምህርት ቤቱን ስለሚደጉሙት እሱን ተማምነው በድጋፍ ለመማር እንደሚመጡ ያስረዳሉ።
በአካባቢው የሚኖረው ማኅበረሰብ እጅግ የተጎሳቆለና ችግር ላይ ነው ያለው የሚሉት ርዕሰ መምህሩ፣ ጦሙን እያደረ ለልጆቹ የትምህርት መሣሪያዎችንም ሆነ አልባሳትን ማሟላት የሚቸገር ነው። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ባሉ ችግሮች ሳቢያ ተፈናቅሎ በአካባቢው የሰፈረም በርካታ ስለሆነ፣ ልጆቻቸውን መሠረታዊ የመማሪያ ቁሳቁሶችን አሟልቶ ለማስተማር እንደሚከብዳቸውም ተናግረዋል።
አቅም ያለው የተሻለ ቦታ ልኮ እንደሚያስተምር የተናገሩት እኚህ በአካባቢው ለ26 ዓመታት ያገለገሉት ርዕሰ መምህር፣ ሰባ አምስት በመቶ የሚሆነው ወላጅ ድጋፍ ካላገኘ ልጆቹን አስፈላጊውን አሟልቶ ማስተማር የማይችል ችግረኛ እንደሆነ ይናገራሉ።
ከ2000 ጀምሮ የኑሮ ውድነት መባባሱ ችግሩን እያደራረበበት ቢመጣም፣ ከድርጅቶችም ሆነ ከበጎ አድራጊ ግለሰቦች ለትምህርት ቤቱ በየዓመቱ የሚመጣ ድጋፍን ተማምነው ልጆቻቸውን የሚያስተምሩት ብዙ ናቸው። ደብተር እርሳስና እስኪርቢቶን ጨምሮ የተለያዩ አልባሳትን ስለሚያገኙ ልጆቻቸውን ለመላክ አይቸገሩም ነበር።
ዘንድሮ ግን የመማሪያ ቁሳቁስ እጅግ በመወደዱ ምክንያት ይረዷቸው የነበሩት አካላት ችግሩን በማስረዳት አብዛኞቹ ባዶ እጃቸውን መምጣታቸውን ዘውዱ ተናግረዋል። ምን ይሻላል ብለው እኛን ቢያማክሩንም፣ ትምህርት ቤቱ በእርዳታ ያስጀመረውን ሕንፃ ለማስቀጠል የተበደረውን 35 ሺሕ የግለሰብ እዳ መክፈል ተስኖት እንደሚገኝ አስረድተዋል።
ዓመቱ ሲጀመር ድጋፍ ያገኛሉ ብሎ ሳይዘጋጅ ሲጠብቅ የነበረው ወላጅ ዱብ እዳ ይሆንበታል ያሉ ሲሆን፣ ያለደብተር ምን ላይ ማስታወሻ እንደሚይዙ የሚያሳስብ ነው ብለዋል። ጉዳዩን ይበልጥ ያወሳሰበው ደግሞ የመማሪያ መጻሕፍት ገና ስላልደረሰላቸው የሚያነቡትም ሆነ የሚያስታውሱበትና የሚፈተኑበት ነገር አይኖራቸውም ሲሉ ስለመጪ ጊዜው ያላቸውን ስጋት ተናግረዋል።
የመምህራን ሞጁል ብቻ ደርሷል ያሉ ሲሆን፣ መምህሩ ብላክ ቦርድ ላይ ቢጽፍም ሆነ በቃል ቢያነቡ ማስታወሻ መያዝ ወይም በቶሎ መጻሕፍት ደርሰው ካላነበቡ ችግሩ ይበልጥ ይወሳሰባል ባይ ናቸው።
ለ350 ተማሪ 86 ዴስክ ነው ያለን የሚሉት ዘውዱ፣ ሦስትና አራት ማስቀመጡ እንዳለ ሆኖ ቅድመ መደበኛ የሆኑ ከ80 በላይ ተማሪዎችን መሬት ላይ ኬንዳ አንጥፈን ነው የምናስተምራቸው ብለዋል። ያለማስደገፊያና መቀመጫ እንዲሁ መሬት ሆነው መማሩ እንዳለ ሁኖ መጻፊያና መማሪያ መጻሕፍት ከሌላቸው ወላጆችም ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ እንዳይቸገሩ ያላቸውን ስጋት አስረድተዋል።
ከቦታው ገደላማነት አኳያ አስፈላጊው አጥር እንኳን ስለሌለ በእረፍት ከመምህራኑ ጋር ሲጠብቁ እንደሚቆዩ የሚያስረዱት እኚሁ ርዕሰ መምህር፣ የትምህርት ቤቱ ችግር መጠነ ሰፊ ነው ይላሉ። በኅብረተሰቡ ተሳትፎና በለጋሾች የተጀመረውን የመማሪያ ክፍሎች ግንባታ ማጠናቀቅ የተሳነው ትምህርት ቤት መሆኑን በማስረዳት የመምህራኑንም ብሶት አስረድተዋል።
የመምህራኑ ደሞዝ በአጃቢ መምጣት ካቆመ ከኹለት ዓመት ወዲህ ደሞዝ ለመውሰድ ለቀናት በሚፈጅ ጉዞ በርካታ ወጪ አውጥተው ከተማ ሄደው ደሞዛቸውን ያገኙ የነበረ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የግል ባንክ ቅርንጫፍ በመክፈቱ መጉላላታቸው እንደቀነሰ ይጠቅሳሉ። የመምህራን ሥልጠናና አበል በትምህርት ቤቱ ይከፈል የሚል መመሪያ ስላለ ወጪያቸውን ሸፍኖ ለመላክ የሚቸገር ትምህርት ቤት፣ የተማሪዎቹን ችግር ለመቅረፍ አቅም አይኖረውም ብለዋል።
ምንም ቢሆን መማሪያ ቁሳቁስ ባይሟላም ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ከመላክ እንዳይቆጠቡ የመከሩት ዘውዱ፣ መንግሥትም ሆነ አቅሙ ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ድርጅቶች የመማሪያ ቁሳቁስ በጣም መወደዱን ተመልክተው ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል። በገጠር ያሉ ትምህርት ቤቶችን በማገዝ ወላጆችንም በማበረታታት ወደ ከተማ የሚፈልሰውን ታዳጊ ቁጥር መቀነስ እንደሚቻልም ያምናሉ።
ትምህርት መሠረታዊ ጉዳይ እንደመሆኑ ሁሉም ባለበት የሚማርበት ደረጃውን የጠበቀ መስፈርት መዘጋጀት እንዳለበት ምሁራን ይስማማሉ። ፊንላንድን የመሳሰሉ በትምህርት ጥራት ላይ ልዩ ትኩረት የሚሰጡ አገራት የግል ትምህርት ቤትን እስከመከልከል የሚደርስ ውሳኔን አስተላልፈዋል። ልጆች ትምህርት የማግኘት መብት ብቻ ሳይሆን፣ እኩል መስፈርትን በሚያሟሉ ትምህርት ቤቶች በመማር እድላቸው ተመጣጣኝ መሆን እንዳለበት ያምናሉ። ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ አፍሪካ አገራት ሁሉንም ለማመሳሰል አስቸጋሪ ቢመስልም፣ ማመጣጠንና ተቀራራቢ ለማድረግ መጣር እንደሚገባ ግልፅ ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015


