ከትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ወደ አምቦ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ ተማሪዎች የመመረቂያ ጊዜ ተራዝሞብናል አሉ

0
1039

ከትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ወደ አምቦ ዩኒቨርሲቲ በጊዜያዊነት የተመደቡ ተማሪዎች የመመረቂያ ጊዜያቸው ለአንድ ዓመት በመራዘሙ ቅሬታ እንዳደረባቸው ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

በትግራይ ክልል አራቱም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የመደበኛ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የነበሩ 10 ሺሕ 164 ተማሪዎች በጦርነቱ ምክንያት ከሐምሌ እስከ ነሐሴ 2013 ድረስ በሰመራ በኩል ወደ ኮምቦልቻ እና አዲስ አበባ መመለሳቸው ይታወቃል።

ከ10 ሺሕ 164 ተማሪዎች ኹለት ሺሕ 355 ከአዲግራት፤ ሦስት ሺሕ 668 ደግሞ ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የተመለሱ ናቸው። ከእነዚህ መካከልም ከአንድ ሺሕ በላይ የሚሆኑት ትምህርት ሚኒስቴር በገባው ቃል መሠረት በጊዜያዊነት ወደ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ተመድበው ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ።

ትምህርት ሚኒስቴር በጦርነቱ ምክንያት ከትግራይ ክልል አራቱም ዩኒቨርሲቲዎች ተቀብሎ ሲያመጣቸው ሰላም በሰፈነባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበው ትምህርታቸውን እንደሚከታተሉና ከአቻዎቻቸው ጋር እኩል እንደሚያጠናቅቁ አሳውቋቸው እንደነበር ተማሪዎቹ ያስታውሳሉ።

ሆኖም ግን ለመመረቅ አንድ ዓመት ጭማሪ እንደተደረገባቸውና ኹለት ዲፓርትመንት ብቻ እንዲመርጡ በመገደዳቸው ቅሬታ እንዳደረባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ፤ ትምህርታቸውን ከአቻዎቻቸው (ባቻቸው) ጋር እኩል ለማጠናቀቅ ክረምቱንም ጭምር እንደሚማሩ ቃል የተገባላቸው ቢሆንም፤ ክረምቱን መማር ባለመቻላቸው አንድ ዓመት እንደተጨመረባቸው ገልጸዋል። ተማሪዎቹ ለዩኒቨርሲቲው ቅሬታቸውን አቅርበናል ያሉ ሲሆን፤ ለክረምት የሚሆን በጀት እንደሌለው አሳውቆናል ብለዋል።

በመሆኑም፤ ትምህርታቸውን በ2014 ማጠናቀቅ ሲገባቸው ወደ 2015፤ በ2015 ማጠናቀቅ የነበረባቸው ደግሞ ወደ 2016 እንደተራዘመባቸው የገለጹት ተማሪዎቹ፤ ትምህርት ሚኒስቴር ግን በወቅቱ በቂ በጀት እንደሚመድብላቸውና የመመረቂያ ጊዜያቸው ለአንድ ሳምንት እንኳ እንደማይዘገይ ገልጾላቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ከሌላ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ ጓደኞቻቸው ለአብነትም ቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ቃል በተገባላቸው መሠረት በ2014 እንደተመረቁም ተማሪዎቹ ተናግረዋል።

በአንቦ ዩኒቨርሲቲ በጊዜያዊነት የተመደቡና በቅርቡ የተመረቁ ተማሪዎችም ቢሆኑ ከአቻዎቻቸው (ባቾቻቸው) ጋር በ2013 መመረቅ ሲገባቸው የአንድ ዓመት ጭማሪ ተደርጎባቸው በ2014 ለመመረቅ እንደተገደዱም ተብራርቷል።

በ2013 በነበሩት ተማሪዎች የደረሰው ችግር በእነርሱም ላይ እየተደገመ በመሆኑ ትምህርት ሚኒስቴር መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል።

አምቦ ዩኒቨርሲቲ፣ ትምህርት ሚኒስቴር በጀት እንዲበጅት ጠይቁና እናስተምራችኋለን የሚል ምላሽ እንደሰጣቸውም ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል። ከዩኒቨርሲቲው ባገኙት ምላሽ መሠረት ችግሩ ያለው ከዩኒቨርሲቲው ሳይሆን ከትምህርት ሚኒስቴር መሆኑንም ተማሪዎቹ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ የተነሳው ቅሬታ ዲፓርትመንት ምርጫን በተመለከተ ሲሆን፤ በዚህም ተማሪዎቹ ከኮምፒውቴሽናል እና አግሪካልቸር (ግብርና) ዲፓርትመንት ውጭ መምረጥ አለመቻላቸው ነው።

ተማሪዎቹ፤ ከኹለት ዲፓርትመንት በላይ የመምረጥ ዕድል ማግኘት ያልቻሉት፣ ዲፓርትመንት የመረጡት አምቦ ዩኒቨርሲቲ ነባር ተማሪዎችን ቀድሞ ካስመረጠ በኋላ በመሆኑ ነውም ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ ለማግኘት የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አመለወርቅ ህዝቅኤልን የጠየቀች ሲሆን፤ ኃላፊዋ ጉዳዩን ከሰሙ በኋላ ቆይታችሁ ደውሉ የሚል ምላሽ በመስጠታቸውና ከቆይታ በኋላ ሲደወል እንዲሁም መልዕክት ሲጻፍ ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸው ሐሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።

ለተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲው የበጀት እጥረት አለበት ብለዋል ያሏቸው የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጸሐፊ ሙሉ ዋቅጅራ ጉዳዩን ከሰሙ በኋላ ምላሽ ለመስጠት ፋቃደኛ አልሆኑም።

ቅሬታ አቅራቢ ተማሪዎቹ በይበልጥ ጉዳዩን ሲከታተሉላቸው የነበሩት ኢዶሳ ተርፌሳ (ዶ/ር) መሆናቸውን ገልጸው እርሳቸው እንዲጠየቁላቸው ጠቁመዋል።

ተማሪዎቹ ከትግራይ ክልል በተመለሱበት ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የመምህራንና ተማሪዎች አገልግሎት ዳይሬክትር ለነበሩት ኢዶሳ ተርፌሳ (ዶ/ር) አዲስ ማለዳ ከሦስት ጊዜ በላይ ጥያቄውን ያቀረበችላቸው ሲሆን፤ ምላሽ ለመስጠት አልችልም በማለት ፈቃደኛ አልሆኑም።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here