ጌዴኦ ከማይዋሰናቸው ዞኖችና ወረዳዎች ጋር ለሕዝበ ውሳኔ መቅረቡ ጥያቄ አስነሳ

1
1813

ምርጫ ቦርድ ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ እንደሚገባ ጠቁሟል

በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኙ ስድስት ዞኖችና አምስት ልዩ ወረዳዎችን የያዘ አዲስ ክልል ለመመሥረት መታቀዱን ተከትሎ፣ ከሌሎቹ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር የማይዋሰነው የጌዴኦ ዞን ጉዳይ ጥያቄ አስነስቷል።

በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ 12ኛውን ክልል ለመመሥረት ለሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ምክክር፣ በሕዝበ ውሳኔው ላይ በርካታ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን፣ የጌዴኦ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት የምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ አፈጻጸም ሕግን የተከተለ መሆን ይገባዋል ሲል አሳስቧል።

‹‹የጌዴኦ ዞን በምን ሕገ መንግሥታዊ ስሌት ነው ከሌሎች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር አንድ ክልል ለመሆን፣ ለሕዝበ ውሳኔ የቀረበው›› ሲሉ የፓርቲው አመራር እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አለሳ መንገሻ ጠይቀዋል።

አለሳ አክለውም፣ መንግሥት ስድስቱ ዞኖችና አምስቱ ልዩ ወረዳዎች በኩታ-ገጠም (ክላስተሪንግ) አንድ ክልል እንዲሆኑ አቅጣጫ ካስቀመጠ፣ ከአንዳቸውም ጋር ኩታ-ገጠም ያልሆነው ጌዴኦ ዞን እንዴት የአዲሱ ክልል አካል ሊሆን ይችላል ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል።

የጌዴኦ ዞን በሲዳማ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል የሚዋሰን ሲሆን፣ በክልልነት አብረዉት ከሚደራጁ ዞኖችና ወረዳዎች ጋር የወሰን ግንኙነት የለውም። በዞኑ ላይ ጥያቄ የተነሳው ዞኑ አብረዉት ከሚደራጁ ዞኖችና ወረዳዎች ጋር ኩታ-ገጠም ባለመሆኑ ነው።

ውሳኔው ጌዴኦ ዞንን የአማራ ክልል ወይም የአፋር ክልል አካል ማድረግ እንደማለት ነው ያሉት የፓርቲው አመራር፣ ሕገመንግሥቱም ኩታ-ገጠም ያልሆኑ ዞኖች አንድ ክልል ሆነው መዋቀር ይችላሉ የሚል አሠራር የሌለው መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ፣ ጥያቄው ከቦርዱ ኃላፊነት ያለፈ ሊሆን እንደሚችል አንስተው፣ ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረብ እንደሚቻል ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 46 ስለ ክልል አደረጃጀት ያስቀመጠው ድንጋጌ ‹ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው› ይላል።

የአዲሱ ክልል አወቃቀር ሕዝብ ከሚፈልገው ይልቅ መንግሥት በሚመቸው ሁኔታ እንዲፈጸም መወሰኑን ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቁመዋል። ይህም የሕዝቡን ጥያቄ የማይፈታ ነው ሲሉ በውይይቱ የተሳተፉ የተለያዩ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተናግረዋል።

የወላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ፓርቲ፣ የወላይታ ሕዝብ ‹ክልል መሆን አልያም ሞት› እያለ ባለበት ሁኔታ፣ የመንግሥትን ኢ-ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ምርጫ ቦርድ ለማስፈጸም በማቀዱ ‹‹ስብራት ተሰምቶኛል›› ብሏል።

ሕዝቡ በአፈና ሥርዓት ውስጥ ባለበት ሁኔታ የአፈና ሥርዓቱን ይበልጥ ለማስቀጠል አንተባበርም ያለው ፓርቲው፣ የሲዳማ ሕዝብ መብት ተሰጥቶት የወላይታ ሕዝብ የሚነፈግበት ሁኔታ የለም ነው ያለው።

‹ያለሕዝብ ፍላጎት ሕዝበ ውሳኔ መደረጉ ምን ፋይዳ ያመጣል? ሊሳካስ ይችላል ወይ የሚሉ እና አሁን ያለው የደቡብ ክልል መቀጠል እንደማይችል እየታወቀ ‹በክላስተሪንግ ወይስ በነበረው ትቀጥላለህ› ብሎ ምርጫ ማቅረብ አግባብ ነው ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችም ቀርበዋል።

በቀረቡለት በርካታ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ የሰጠው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በአዋጅ ተሰፍሮ የተሰጠውን ሥልጣን ብቻ እንደሚወጣና አስፈጻሚ አካል መሆኑን በመግለጽ፣ በሌሎች ተቋማት ኃላፊነት ላይ ጣልቃ አይገባም ነው ያለው።

‹‹አህያውን ፈርቶ ዳውላውን›› እንዳይሆንም የሚመለከተውን ጥያቄ ለሚመለከተው ብታቀርቡ ይሻላል ‹‹የቄሳርን ለቄሳር›› ካለ በኋላ፣ ቦርዱ የሕዝብን ውሳኔ ያስከብራል ሲል አብራርቷል።

ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ እና ጌዴኦ ዞኖች እንዲሁም አማሮ፣ አሌ፣ ባስኬቶ፣ ቡርጂ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎችን የያዘ አዲስ ክልል ለማዋቀር ጥር 29/2015 ሕዝበ ውሳኔ ለማካሄድ እቅድ ተይዟል።

ለዚህም ከ541 ሚሊዮን ብር በላይ ከመንግሥት በጀት መጠየቁን የገለጸው ምርጫ ቦርድ፣ ከሦስት ሺሕ በሚልቁ ምርጫ ጣቢያዎች ከ3 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ መራጮች ሊሳተፉ ይችላሉ ነው ያለው።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

 

አስተያየት

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here