86 የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ሠራተኞች ከሕግ አግባብ ውጪ ከሥራ ተባረናል አሉ

0
1476

86 የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ሠራተኞች ተቋሙ ከሕግ አግባብ ውጭ በሆነ አሠራር ከሥራ ቀንሶናል ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ተናገሩ።

ተቋሙ 86 ነባር ባለሙያዎችን ከሕግ አግባብ ውጭ በሆነ አሠራር ከሥራ አሰናብቶ፤ ‹ልምድ የሌላቸው ሠራተኞችን› ለመቅጠር ፈተና እየፈተነ ነው ሲሉም ሠራተኞች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ከሥራ የተባረሩት እስከ 10 ዓመት የሥራ ልምድ ያላቸው የተቋሙ ሠራተኞች ጭምር ናቸው።

ከዚህ በፊትም 100 አዳዲስ ሠራተኞች ተቀጥረዋል የተባለ ሲሆን፤ ሰሞኑን ደግሞ የሥራ ልምድ ያላቸው የተቋሙ ነባር ሠራተኞች ተባርረው፤ 30 የሚሆኑ አዳዲስ ሠራተኞች ተፈትነው አልፈዋል መባላቸውንና በመፈተን ላይ ያሉ መኖራቸው ተገልጿል።

አዲስ ማለዳ በተመለከተችው አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ያወጣው ማስታወቂያ 59 ጀማሪ ሪፖርተሮች መስከረም 3/2015 ለጽሑፍ ፈተና መጥራቱን ያሳያል።

ሠራተኞቹ ግን ተቋሙ የሕግ አግባብነት በሌለውና ብሔር ተኮር በሆነ አሠራር ተባረናል የሚል ቅሬታ አሰምተዋል። ከቅሬታ አቅራቢዎቹ መካከል አንድ የ10 ዓመት የሥራ ልምድ አለኝ ያሉ የተቋሙ ሠራተኛ፣ ድርጊቱ ከሕግ አግባብ ውጪ ስለሆነ የተባረሩት ሠራተኞች ተሰባስበው ወደ ፍርድ ቤት ለማቅናት እንዳቀዱም ጠቁመዋል።

ሠራተኛው አክለውም፣ ‹‹ድርጊቱ ምንም ዓይነት የሕግ መሠረት የለውም›› ነው ያሉት። የሥራ ልምድ ያላቸው ሠራተኞች ተባረው ምንም የሥራ ልምድ የሌላቸው ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዲገቡ ስለመደረጉም ተናግረዋል።

ተቋሙ ከነሐሴ 23/2014 ጀምሮ ሠራተኞችን ለመቅጠር በማስታወቂያ ሲገልጽ የቆየ ሲሆን፤ 86 እስከ 10 ዓመት ልምድ ያላቸው ሠራተኞች ግን ከሥራ ተባረው ጀማሪዎቹ ‹እየተቀጠሩ› መሆኑ ተገልጿል።

ተቋሙ ሠራተኞችን ለመቀነስ ያወጣው የምዘና ፈተና ለሁሉም ሠራተኛ እድል የሚሰጥና ክፍት እንዳልነበረም ተጠቁሟል። የውጤቱ ምዘና ሲደረግ እያንዳንዱ ሠራተኛ ተቆጥሮና ተመዝግቦ ውጤቱም በሰሌዳ መለጠፍ እንዳለበት መመሪያው ቢያዝም፤ አንዱ ተፈታኝ ሌላኛውን በምን ያክል ውጤት በልጦ እንደሚቀጠር የታወቀ የተገለጸ ነገር አለመኖሩም ተነስቷል።

ከሪፖርተርነት ተነስተው ዳይሬክተር፤ ከአርታኢነት ተነስተው ዋና አዘጋጅ እንዲሁም ከዜና ክፍል ዳይሬክተርነት ተነስተው ሪፖርተር የሆኑ ሠራተኞች ስለመኖራቸው አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

የተቋሙ ሠራተኞች ስለሚያውቁት ብቻ እንጂ ምንም የሥራ ልምድ የሌለው ሰው በተባረሩት ሠራተኞች የሥራ መደብ እንደተተካ ነው የተገለጸው።

ሠራተኞቹ ከሥራው ሲታገዱ የሚከበርላቸው መብት ስለመኖሩ ተቋሙን ሲጠይቁ ‹‹ወደ ሲቪል ሰርቪስ ተቋም እንልካችኋለን›› የሚል ምላሽ ተሰጥቶናል ይላሉ።

ይሁን እንጂ በአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ 20 ሺሕ ብር ሲከፈለው የነበረ የቤተሰብ አስተዳዳሪ ሠራተኛ በሲቪል ሰርቪስ ተቋም ተቀጥሮ ስምንት ሺሕ ብር ተከፍሎት ቤተሰቡን ሊበትን እንጂ ሊያስተዳድር አይቻለውም ባይ ናቸው ሠራተኞቹ።

አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በጡረታ ምክንያት 16፤ በሥራ አፈጻጸምም ሆነ በሌላ ምክንያት እንከን ያልታየባቸው 86 ባለሙያዎችን በአጠቃላይ ከ100 የሚልቁ ሠራተኞችን ከሥራ ማሰናበቱ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ተቋሙ ከዚህ በፊት 90 በመቶ የሚሆኑት ሠራተኞች አንድ ቋንቋ (አማርኛ) ተናጋሪ ናቸው ሲል እንደቆየና፤ ሠራተኞቹን ከሥራ ያባረረው ብሔርን መሠረት አድርጎ ሳይሆን እንዳልቀረም በቅሬታ አቅራቢዎቹ ተጠቅሷል።

አዲስ ማለዳ የተነሳውን ቅሬታ በማስመልከት ምን ምላሽ እንዳላቸው ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ሳሙኤል ከበደ ጥያቄ አቅርባለች። ምክትል ሥራ አስፈጻሚውም ስብሰባ ላይ ነኝ ቆይታችሁ ደውሉ ያሉ ሲሆን፤ በቀጠሮው መሠረት በተደጋጋሚ ሲደወል ግን ስልክ ባለማንሳታቸው ሐሳባቸውን ለማካተት ሳይቻል ቀርቷል።

ተቋሙ አሠራሩ ፍትሐዊ እንደሆነ በመጠቆም ቅሬታውን በመቀበል የሚያበረታታ አካልን በሕግ እንደሚጠይቅ ሲገልጽ የሰነበተ ሲሆን፤ ሠራተኞቹ ግን ገና ወደ ፍርድ ቤት እንዲሚያቀኑ ገልጸዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 206 ጥቅምት 5 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here