የኢትዮጵያዊያን ስደተኞች አስከሬን እንደሆነ የተገመተ የ25 ሰዎች አስከሬን ሚዚምባ በሚባለው የማላዊ ሰሜናዊ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ጥብቅ ደን ውስጥ መገኘቱን የማላዊ ፖሊስ አስታወቀ።
ከማላዊ ዋና ከተማ ኢሎንግዌ 250 ኪሎሜትር ርቃ በምትገኝ ሚዚንባ በተሰኘች ግዛት በጅምላ የተቀበሩ የ25 ኢትዮጵያዊያን ሳይሆኑ እንደማይቀሩ የተገመቱ አስከሬን ማግኘቱን ፖሊስ አሳውቋል።
የጅምላ መቃብሩ የተገኘው የአካባቢው ነዋሪዎች የዱር ማር ለመቁረጥ ጫካ ውስጥ በሚዘዋወሩበት ወቅት እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፤ ወዲያውም ለፖሊስ አሳውቀዋል ተብሏል።
ባለፈው ማክሰኞ የተገኘው የስደተኞቹ አስከሬን የተቀበረው ከወር በፊት እንደሆነ የተናገረው የአገሬው ፖሊስ፣ ኹሉም ወደ ደቡብ አፍሪካ ለማምራት ሲጓዙ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ገልጿል።
እድሜያቸው ከ25 እስከ 40 ይሆናቸዋል የተባሉት በጅምላ የተቀበሩት ኢትዮጵያዊያን፣ በምን ምክንያት እንደተገደሉና በጅምላ እንደተቀበሩ ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል።
አገሪቱ በተለምዶ ከምሥራቅ አፍሪካ የሚነሱ ስደተኞች እንደሚተላለፉባት የተጠቀሰ ሲሆን፣ በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት በሕገወጥ መንገድ ገቡ ተብለው ከተያዙት 221 ስደተኞች ውስጥ 186ቱ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ከዚህ ቀደምም 22ቱ ወደኢትዮጵያ እንዲመለሱ መደረጉ ይታወሳል።
ባሳለፍነው ሰኔ ወር የመንግሥታቱ ድርጅት ባወጣው መግለጫ በማላዊ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በርካታ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን እንደሚገኙና ብዝበዛ እንደሚደርስባቸውም ማስታወቁ አይዘነጋም።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015


