1 ሺሕ 43 ቶን ያልተወገደ ኬሚካል አለ
ከኹለት ዓመት በፊት የተጀመረው ጊዜያቸው ያለፈባቸው የዲዲቲ፣ ኦርጋኖ ፎስፌት እና ኦርጋኖ ክሎሪን የሚባሉ ኬሚካሎችን የማስወገድ ሥራ በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን እንዳልተጠናቀቀ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የአካባቢ ሕግ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ጀነራል ግርማ ገመቹ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በሦስት ዙር በተከፋፈለው ኬሚካሎችን የማስወገድ ሂደት እስካሁን ድረስ በመጀመሪያው ዙር አዳሚ ቱሉ በሚገኘው ማእከላዊ የኬሚካሎች ማከማቻ መጋዘን ከሚገኘው 460 ቶን ኬሚካል ውስጥ 240 ቶኑን ብቻ ከአገር ማስወጣት እንደተቻለ ገልጸዋል።
ቀሪውን 220 ቶን የማሸግ ሥራ ደግሞ 97.5 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ አዳማ ከሚገኘው ማእከላዊ የኬሚካሎች ማከማቻ መጋዘን በኹለተኛው ዙር ለማስወገድ የታቀደውን 310 ቶን ኬሚካል የማሸግ ሥራ ደግሞ በዚህ ሳምንት እንደተጀመረ ገልጸዋል።
ኬሚካሎቹን የማስወገድ ሥራ እስካሁን ድረስ መጠናቀቅ እንደነበረበት የገለጹት ግርማ፣ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በመቋረጡ ኬሚካሉን ለማስወገድ የሚያስፈልጉ የወረቀት ሥራዎች እንዲሁም ኬሚካልን ለማስወገድ የሚያስፈልገው ዓለም ዐቀፍ የማጓጓዝ ሂደት ላይ ያጋጠሙ መጓተቶች የማስወገድ ሥራው እንዲጓተት እንዳደረጉት ግርማ ተናግረዋል። የሩሲያና ዩክሬን ጦርነትም በተለይ በባሕር ላይ ለሚደረገው የማጓጓዝ ሂደት አለመካሄድ አንዱ ምክንያት እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ለመጨረሻ ጊዜም በግንቦት ወር 2014 ሰባት ኮንቴይነር ኬሚካል ከአገር እንደወጣ የተናገሩት ግርማ፣ መዘግየቶች የተፈጠሩት ከኢትዮጵያ መንግሥት ቁጥጥር ውጭ በሆኑ ምክንያቶች እንደሆነ ገልጸዋል።
ኬሚካሎችን ለማስወገድ በዓለም ዐቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም (Global environmental facility) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ መርሀ ግብር በኩል በተመደበ 4.5 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እየተሠራ ይገኛል። የማስወገድ ውል ያልተገባለትና በሦስተኛው ዙር የማስወገድ ሥራ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ተሰባስቦ የሚወገደው 513 ቶን ኬሚካልን ለማስወገድም የኹለቱን ዙር ኬሚካሎች የማስወገድ ሥራ እየሠራ ከሚገኘው ቪዮሊያ ኢንቫይሮመንታል ሰርቪስ ጋር ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ መርሀ ግብር ጋር ስምምነት እንደሚደረግ ታውቋል።
ቪዮሊያ ኢንቫይሮመንታል ሰርቪስ በዘርፉ ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ ያለው ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከ16 ዓመታት በፊት የነበራትን ተመሳሳይ ኬሚካሎች ክምችት ስታስወግድም ከፍተኛ ድርሻን የተወጣ ድርጅት ነው።
ይህ ኬሚካሎችን የማስወገድ ሥራ ከመጀመሩ በፊት 1 ሺሕ 283 ቶን ዲዲቲ፣ ኦርጋኖ ፎስፌት እና ኦርጋኖ ክሎሪን ክምችት የነበረ ሲሆን፣ ከዚህም መካከል 1 ሺሕ 43 ቶን ኬሚካል እስካሁን ድረስ ያልተወገደ ነው።
በአጠቃላይ ይህንን ኬሚካል የማስወገድ ሥራ ቴክኒካል አፍሪካን ኢንስቲትዩት የተባለ እና መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገ ድርጅት የሚያስተባብረው ሲሆን፣ የጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ደግሞ ቴክኒካል ክፍሉን ይመራሉ።
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የኬሚካሎቹ አስመጪ እንደመሆኑ መጠን ኬሚካሎቹን የማስወገድ ኃላፊነትም የእሱ የነበረ ቢሆንም፣ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋነኛው ኃላፊነቱ ኬሚካሎቹ በሰውና በአካባቢ ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ማድረግ ከመሆኑ አንጻር ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየሠሩ እንደሚገኙ ግርማ ተናግረዋል።
ኬሚካሎችን ማስወገድ በአገር ውስጥ መከወን የማይችል በመሆኑ ምክንያት የኢትዮጵያ የኬሚካል ክምችት በከፍተኛ የማስወገጃ ወጪ በርካታ ኪሎሜትሮችን በማቆራረጥ በስፔን አገር እንደሚወገድ ለማወቅ ተችሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015



