የሲሚንቶ ምርት በበቂ ሁኔታ እየደረሳቸው አለመሆኑን የሲሚንቶ አከፋፋዮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በአዲሱ የግብይት መመሪያ መሰረት ሲሚንቶ ለተጠቃሚዎች እንዲያከፋፉሉ ከተመረጡ ወኪሎች ብዙዎች ከአንድ ዙር በላይ ማግኘት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል በወረዳ ደረጃ የሲሚንቶ አከፋፋይ የሆኑ ነጋዴ እንደገለጹት፣ በርካታ ነዋሪዎች ባሉበት የወረዳው ከተማ ከተመረጡ ኹለት አከፋፋዮች አንዱ እርሳቸው መሆናቸውን በመግለጽ፣ የመንግሥት መመሪያ ከወጣ በኋላ አንድ ጊዜ 250 ኩንታል ሲሚንቶ ያከፋፈሉ ሲሆን፣ ከዚያ ቀጥሎ ግን ሲሚንቶ ማግኘት አልቻሉም።
ሲሚንቶውን የማገኘው የወረዳው ንግድ ጽህፈት ቤት ለዞኑ ንግድ መምሪያ ካመለከተ በኋላ ፈቃድ ሲያገኝ ከዞን አከፋፋዮች ነው ያሉት ነጋዴው እየተነገረኝ ያለው ዞን ላይ ሲሚንቶ እንደሌለ ነው ብለዋል።
ነገር ግን፣ ዞኑ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ግለሰቦች መኖራቸውን በመጥቀስ፣ ለአብነተም የነዳጅ ማደያ በማሰራት ላይ ለሚገኝ ግለሰብ 100 ኩንታል ተፈቅዶለት ሄዶ አምጥቷል ነው ያሉት።
ሌላኛው አከፋፋይም፣ እርሳቸውን ጨምሮ የበርካታ ወረዳዎች ወኪል አከፋፋይ የሆኑ አካላት አንድ ዙር ብቻ እንደወሰዱና ለቀጣዩ ዙር እየተጠባበቁ መሆኑን በመግለጽ፣ የሲሚንቶ እጥረቱ በጣም የጎላ ነው ብለዋል።
እንደከዚህ ቀደሙ ሲሚንቶ ማግኘት ባለመቻሉም ህብረተሰቡ ቀላል የቤት እድሳት እንኳን ማድረግ እንዳልቻለ አንስተዋል። ሲሚንቶ ሲመጣም የማዘጋጃ ቤትና የንግድ ጽህፈት ቤት በጋራ ካልፈቀዱ ተጠቃሚዎች ከአከፋፋዮች ሲሚንቶ ማግኘት እንደማይችሉና ይህም ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ይገኛል ሲሉ አመላክተዋል።
እንደገለጹት ሲሚንቶ ላይ ያለው የግብይት ስርዓት ከወራት በፊት በወጣው መመሪያ መሰረት ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ይካሄዳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፣ በገበያው ሁኔታ ቀጥሎ ምን እንደሚፈጠር ለማወቅ አስቸጋሪ ነው ብለዋል።
የመጀመሪያውን ዙር ሲሚንቶ ስንወስድ በቅርቡ ኹለተኛውን ዙር እንደምንጭን ነበር የተነገረን፣ ነገር ግን ለማስጫን ሂደት ስንጀምር አልቋል ጠብቁ ተባልን በማለት አክለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ሲሚንቶ ሲያከፋፍሉ የነበሩ አካላት በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት ከገበያ ውጭ መሆናቸውን እና በዚህም ኢኮኖሚያዊ ጫና እየፈጠረባቸው እንደሚገኝም ተናግረዋል።
አዲሱ የሲሚንቶ ግብይት መመሪያ በአገር አቀፍ ደረጃ አከፋፋዮች እንዲወጡ እንደሚደግፍ አምናለሁ ያሉ እና መቀመጫቸውን አዲስ አበባ በማድረግ ከዚህ በፊት በመላ አገሪቱ ሲሚንቶ ሲያከፋፍሉ እንደነበር የገለጹት ሴት ነጋዴ፣ ክልሎች የየራሳቸውን አከፋፋይ መርጠው እያሰሩ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ግን ከክልሎች ጋር ተመሳሳይ የሆነ አሰራር አለመኖሩን በማንሳት፣ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ከሥራ ውጭ ሆነዋል ነው ያሉት። በዚህም ቸርቻሪዎች ሱቃቸውን እየዘጉ መሆኑን ጠቅሰው መንግሥት ዜጎችን ሥራ እንዲሰሩ ማድረግ ነው እንጂ የሚገባው ከሥራ ውጭ ማድረግ የለበትም ብለዋል።
የሲሚንቶን ዋጋ ያስወደደው አከፋፋይ ነው ከማለት ይልቅ፣ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም፣ የተጠቃሚውን የፍላጎት መጠንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮቸን በጥልቀት ማጥናትና መፍትሄ መስጠት ይገባል ባይ ናቸው።
በመመሪያው መሰረት ሲሚንቶ ማከፋፈል ካቆምን አራት ወራት ሆኖናል ያሉት ሌላኛው ነጋዴ ደግሞ፣ በአዲስ አበባ ሲሚንቶ እየተከፋፈለ ያለው በተመረጡ ወኪሎች ሳይሆን በመንግሥት በኩል ነው ብለዋል። በዚህም ሲሚንቶ የሚያስፈልገው ማንኛውም አካል እያገኘ እንዳልሆነ እመለከታለሁ ነው ያሉት።
አዲስ ማለዳ ከንግድ ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ምላሽ ለማግኘት ለተቋሙ የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መስከረም ባህሩ ደጋግማ ብትደውልም ስልክ ባለማንሳታቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015



