ማክሰኞ ጥቅምት 15 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ኢትዮጵያ ተላላፊ ባልሆኑ በሽታዎች አምራች ዜጎቿን እያጣችና የኢኮኖሚ እድገቷ እየተገታ ከመሆኑም በላይ ለነዚህ ህመሞችም በዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ታወጣለች፡፡
ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አንዱና ዋነኛ አጋላጭ ነው፡፡
ጤናማ ያልሆኑ ምግቦች የሚባሉት ስኳር፣ በመደበኛ የቤት ውስጥ ሙቀት የሚረጋ ዘይትና የአትክልት ቅቤ (transfat & Saturated Fat)፣ ጨው መጠናቸው የበዛባቸው ምግቦችና መጠጦች ሲሆኑ፤ እነዚህን የምግብ ዓይነቶች አብዝቶ መመገብ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎችና ለሌሎች የጤና እክሎች ያጋልጣሉ፡፡
ፈጣንና በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን አብዝቶ መጠቀም ዋና ዋና ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች፣ የልብና የደም ቧንቧ በሽታዎች (የልብ ድካምና ስትሮክ፣ ካንሰር፣ ሥር የሰደዱ የመተንፈሻ አካላት ህመሞች (ሥር የሰደደ የሳምባ ምችና አስም) እንዲሁም የስኳር በሽታ ያጋልጣል፡፡
በኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ብዙ ሰዎች በፋብሪካ የተቀነባበሩ ምግቦችን ገዝተው በመጠቀም ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የምግብ አይነቶች በፍጥነት ወደ ገበያ እየገቡ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2019 በአገሪቱ የተመዘገበው 39 ነጥብ 2 በመቶ አጠቃላይ ሞት ተላላፊ ባልሆኑ ህመሞች እንደ ልብ ድካም፣ ስትሮክ፣ የስኳር በሽታ እና ካንሰር ባሉ ሥር በሰደዱ በሽታዎች ምክንያት ነው፡፡
በ2017 ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጠቃላይ የመንግስት ወጪ 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በዚሁ ዓመት (ቀጥታ እና ቀጥተኛ ያልሆነ ወጪ) 31 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር የኢኮኖሚ ኪሳራ አጋጥሟል። ይህም ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP) 1 ነጥብ 84 በመቶ አካባቢ ይይዛል፡፡
አብዛኛዎቹ ተላላፊ ያልሆኑ ህመሞች ጤናማ ባልሆነ አመጋገብ ምክንያት የሚከሰቱ በመሆናቸው ጤናማ የአመጋገብ ልማድን በመከተል ራሳችንና ቤተሰባችንን ተላላፊ ካልሆኑ በሽታዎች እንከላከል ሲል ጤና ልማትና ፀረ ወባ ማህበር አሳስቧል።



