በዘመናዊ የእንሰት አዘገጃጀት ኢትዮጵያዊቷ ፕሮፌሰር ዓለም አቀፍ ሽልማት አሸነፉ

0
951

በጋዜጣው ሪፖርተር

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተዘጋጀና መደበኛ ምግብን በዘመናዊ መልክ ለማዘጋጀት በሚያስችል ውድድር ኢትዮጵያቷ ሄለን ወልደሚካኤል (ረ/ፕ) ከእንሰት ተክል የሚገኘውን የቆጮ ዘመናዊ አዘገጃጀትን ባቀረቡበት ሓሳቧባቸው አሸናፊ ሆነዋል።

በማደግ ላይ ያሉ አገራትን ትኩረት በማድረግ በዩኤስ ኤይድ ድጋፍ፣ ፊድ ዘ ፊውቸር በሚያሰናዳውና ፉድ ሴፍቲ በተሰኘው ውድድር ኢትዮጵያዊቷ ሄለን ወልደሚካኤል(ረ/ፕ) አንደኛ ሆነው ሽልማት እንደተበረከተላት ሌክስ ብሎግ የተሰኘው ድረገጽ ይፋ አድርጓል።

በወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት የውድሩ አሸናፊ፣ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን በመደበኛነት ለምግብነት የሚጠቀሙበትን እንሰትን የውድድራቸው ምርጫ ማድረጋቸው ታውቋል። ከእንሰት ተክል በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጀውን ቆጮ ዘመናዊ በሆነና ስራውን በሚያቀል መንገድ ማዘጋጀት የሚያስችል ሂደትን ይዘው መቅረባቸው ተሰምቷል።

በተለምዶ ኋላ ቀር ሊባሉ የሚችሉ መሳሪያዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያውያን እናቶች ከእንሰት ምግብን ለማዘጋጀት የሚፈጅባቸውን ረጅም ድካምና ልፋት የሚቀንስ የዝግጅት መንገድ መሆኑን የውድድሩ አዘጋጆች ተናግረዋል። የእንሰት ተጠቃሚዎች የሚያወጡትን ጉልበት መቀነስ ብቻ ሳይሆን፣ በአጭር ጊዜ እንዲዘጋጅ በማድረግም ከአላስፈላጊ ወጪ የሚጠብቃቸው መንገድም ነው ተብሏል።

ከአዘገጃጀቱ ባሻገር፣ ሄለን ያስተዋወቁት መንገድ ጤናማ የምግብ ዝግጅት መስፈርቶችን ያሟላና፣ የተመጋቢውን ጤንንት በመጠበቅ ከማናቸውም ስጋት የሚከላከል ዘመናዊና ውጤታማ መንገድ ነው ተብሎለታል። ከአቆራረጡ ጀምሮ ምን ያህል ጊዜ በምን ሁኔታ መቆየት አለበት የሚለውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማጥናት ግኝታቸውን ለውድድር አብቅተው አሸናፊ እንዳደረጋቸው ተነግሯል።

ቆጮ በባሕላዊ መንገድ ሲዘጋጅ የሚቆይበት ወቅትና ሁኔታ እንደየ አዘጋጃጀቱ ስለሚለያይ ፈርመንት እንዲያደርግ የሚቆይበትና የሚብላላበት ሁኔታ ወጥ ባለመሆኑም ለጣዕሙም ሆነ በጤናማነቱ ላይ ስጋት እንደሚያሳድር ተጠቁሟል።

ምን አይነት ሕዋሶች በትክክል ለማብላላት እንደሚረዱት፣ እንዲሁም የትኞቹ እንደሚያበላሹት በጥናት በመለየታቸውና አዘገጃጀቱን ሳይንሳዊ በማድረጋቸው ኢትዮጵያዊቷአሸናፊ የ10 ሺሕ ዶላር ሽልማት አግኝተዋል ተብሏል። እንደ አዲስ የተዋወቀው አዘገጃጀት ለወደፊት የእንሰት ምርትን ለማሳደግና በስፋት ለማምረት ጥቅም ላይ የሚውል ግብዓት ይሆናል ተብሏል።

ውድድሩ የተካሄደው፣ የምግብ ስጋት ተደቅኖባቸዋል ተብለው ከሕዝብ ብዛታቸው አንፃር ከተመረጡ የአፍረካ አገራት መካከል ከ750 የሚበልጡ ተወዳዳሪዎች ከወራት በፊት ጀምሮ ሐሳባቸውን ለምርመራ በማቅረባቸው ነው። ከኢትዮጵያና ናይጄሪያ የተመረጡ ሦሥት ሦሥት ተወዳዳሪዎች ሐሳባቸው ወደቴክኒካል ዩኒቨርስቲ ኦፍ ዴንማርክ ከተላከ በኋላ እርስ በርስ ተወዳድሮ ከአንድ እስከ ሦስት ያለው ደረጃ እንደተመረጠ ታውቋል።

የውድድሩ አሸናፊዋ ሄለን በአርሶ አደሩ ቤት አልፊ በሆነ መንገድ የሚዘጋጅን ቆጮ ቀለል ባለ መንገድ ፋብሪካ ውስጥ በብዛት በማዘጋጀት ለአገልግሎት እንዲቀርብ የሚያስችል ሐሳብ ያቀረቡት የእናቶችን ልፋት ለማስወገድ እንደሆነ ተናግረዋል።

እንሰት ከኢትዮጵያ ውጪ ባይታወቅም በገንፎና ቆጮ መልኩ ተሰርቶ ለምግብነት ይውላል። የእንሰት ተክል በተለይ በደቡብ ኢትዮጵያ በስፋት የሚገኝ ሲሆን፣ እንሰት ከደቡብ ደግሞ ከጉራጌ ማኅበረሰብ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለው ተክል ነው። አሁን አሁን መላ ኢትዮጵያን ለማካለል እየተገዳደረ መሆኑም ይታወቃል። የእንሰት ዓይነቶች ከ50 በላይ መሆናቸውን የሚነገር ሲሆን፣  እንሰት ከምግብነቱ በተጨማሪ እንደ እንሰቶቹ ዓይነት ለስብራት፣ ለሕመም መድኃኒትነት እንደሚያገለግል ይነገራል።

እንሰት ኢትዮጵያ ውስጥ 20 ሚሊዮን ለሚሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ዋነኛ ምግብ ቢሆንም፣ በሌሎች አገራት ግን ሲመረት አይታይም። ሳይንቲስቶች በኢትዮጵያ ከዋነኛ ተክሎች አንዱ የሆነው እንሰት፣ በአየር ንብረት ለውጥ በርካታ ቀውሶችን እያስተናገደች ላለችው ዓለም ነፍስ አድን ሊሆን ይችላል ሲሉ ነበር። በዘርፉ ላይ ጥናት ያደረጉ ምሑራን እንደሚሉት ተክሉ  ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን መመገብ የሚችል መሆኑን ይገልጻሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here