ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በመጀመሪያ ሩብ ዓመት 377.4 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

0
1096

ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በ2015 የመጀመሪያው ሩብ የበጀት ዓመት ዘጠኝ የሎተሪ ዓይነቶችን ለገበያ በማቅረብና ከዕድል ጨዋታ ኮሚሽን 377.4 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቴዎድሮስ ንዋይ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በሦስት ወራት ውስጥ ዘጠኝ የሎተሪ ዓይነቶችን ለገበያ በማቅረብና ከዕድል ጨዋታ ኮሚሽን ለማግኘት ከታቀደው 91.6 በመቶውን ማሳካት ተችሏል። በዚህም አስተዳደሩ በአጠቃላይ የተጣራ 136.1 ሚሊዮን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን፣  በሩብ ዓመቱ የእቅዱን 148 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ቴዎድሮስ ገልጸዋል።

አስተዳደሩ በሦስት ወራት ውስጥ ያገኘው ትርፍ ከእቅድ በላይ የተሳካው፣ በሦስት ወራት ውስጥ መፈጸም የነበረበትን ግዥ ካለመፈጸምና በጀትን በቁጠባ ከመጠቀም አንጻር ትርፉ ከፍ ሊል እንደቻለ ገልጸዋል። አስተዳደሩ በተጠናቀቀው ሩብ በጀት ዓመት ያገኘው ገቢ በ2014 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር የ115 ሚሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ በዚህም የአስተዳደሩ ገቢ የ44 በመቶ እድገት አሳይቷል ተብሏል። በሩብ ዓመት የተገኘው ትርፍ ደግሞ ከ2014 ተመሳሳይ ወቅት ጋር የ65.1 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው ሲሆን፣ ይህም የአስተዳደሩ የትርፍ ምጣኔ በ91 በመቶ ከፍ እንዳለ ያሳያል።

ይህ የገቢና የትርፍ መጠን ብሔራዊ ሎተሪ በሩብ በጀት ዓመቱ ለሽያጭ ባቀረባቸው ዘጠኝ የሎተሪ አይነቶችና ከዕድል ጨዋታዎች ኮሚሽን በሚያገኘው ገቢ ሲሆን፣ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር አዲስ ያስጀመረውን አድማስ የአጭር መልዕክት የሞባይል ሎተሪ የተገኘውን ገቢ አያካትትም።

ከአድማስ ሎተሪ ከሚገኘው ገቢ 25 በመቶውን ኢትዮ ቴሌኮም 75 በመቶውን ደግሞ ብሔራዊ የሎተሪ አስተዳድር የሚወስድ ሲሆን፣ ከፋይናንስ ጋር ያሉ የሲስተም ሥራዎች ባለመጠናቀቃቸው በዚህ ሩብ የበጀት ዓመት ከአድማስ ሎተሪ የተገኘውን ገቢና ትርፍ ለመናገር እንደማይቻል ቴዎድሮስ ተናግረዋል።

አድማስ ዲጂታል ሎተሪ ሥራ ከጀመረ ሶስት ወራትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ የወረቀት ሎተሪዎች መድረስ የማይችሉበትን ቦታዎች ጭምር ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ በብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርና በኢትዮ ቴሌኮም ትብብር ለሞባይል ተጠቃሚዎች የቀረበ የሎተሪ አይነት ነው።

በቅርቡ በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የባንክ ሂሳባቸው ስለታገደው 13 የስፖርት አወራራጅ ድርጅቶች የተጠየቁት ቴዎድሮስ፣ ድርጅቶቹ አሁንም በሥራ ላይ እንዳሉ የገለጹ ሲሆን፣ የባንክ ሂሳባቸው እንጂ ከሥራ አልታገዱም ብለዋል። ሥራቸውንም ለአስተዳደሩ ሪፖርት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከ10 ሺሕ በላይ በሚሆኑ የሎተሪ አዟሪዎች ሎተሪዎችን ለደንበኞቹ የሚያደርስ ሲሆን፣ በተለያዩ አማራጮች ሎተሪዎችን ለደንበኞቹ ለማድረስ እየሰራ እንደሆነ ቴዎድሮስ ተናግረዋል። በዚህም አድማስ ዲጂታል ሎተሪ ተጠቃሹ ሲሆን፣ በርካታ የዝግጅት ሥራዎችን ይጠይቃል የተባለው የኦንላይን (ኢንተርኔት) ሎተሪ ግን በቅርቡ እንደማይጀመር ተነግሯል።<


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015/p>

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here