የመንግሥት ግዢን ወደ ኤሌክትሮኒክስ ግዢ ሥርዓት የማሸጋገር ሥራ ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ በሚቀጥለው ዓመት የመንግሥት ማንዋል ግዢ እንደሚቆም የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን አስታወቀ።
የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን የፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች የሚፈጽሙትን ግዢ በኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት እንዲፈጽሙ እያደረገ መሆኑን ተከትሎ፣ በወረቀት ላይ የተደገፈው የግዢ አገልግሎት ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ እንደሚቆም የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ኢብሳ ተናግረዋል። ዋና ዳይሬክተሩ ጥቅምት 14/2015 ስለ ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት ለንግዱ ማኅበረሰብ ስለሚሰጠው አጠቃላይ ጠቀሜታና ስለሚሠሩ ሥራዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጹት፣ ማንዋል የግዢ ሥርዓት መቆሙ እንደማይቀር ለንግዱ ማኅበረሰብ ወይም አቅራቢው ጠቁመዋል።
ማንዋል የመንግሥት ግዢ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚያቀርቧቸውን የግዢ ጨረታዎች፣ በወረቀት ሰነድ ለአቅራቢዎች የሚሸጡበትና አቅራቢዎች የጨረታ ሰነዳቸውን በወረቀት ሰነድ የሚያስገቡበት የወረቀት ሰነድ ግዢ ነው። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ተግባራዊ ያደረገው ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው የሆነው ኤሌክትሮኒክስ ግዢ ሥርዓት ይህንን የማንዋል ግዢ ከሥርዓት የሚያስወጣ ነው።
ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ የሚገኘው ኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት፣ የግዢ ዕቅድ ማቅረብ፣ ጨረታ ማውጣት፣ ለአቅራቢዎች ጨረታ መሸጥ፣ የጨረታ ሂደትን ማስተዳደር፣ አሸናፊዎችን መግለጽ፣ ውል መፈራረምና የውል አስተዳደር ሥራዎችን ማከናወን የሚያስችል በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሠራር ነው። ሥርዓቱ ከአቅራቢዎች እስከ ገዢዎች የጊዜና የገንዘብ አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት የሚችልና አካላዊ ግንኙነትን የሚያስቀር ሥርዓት ነው።
ማንዋል የመንግሥት ግዢን የተካው ኤሌክትሮኒክ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት በኢትዮጵያ ሙስና ከሚፈጸምባቸው ዘርፎች አንዱ የሆነውን የግዢ አሠራር እንደሚያስቀር ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ስትጠቀም የነበረው የግዢ ሥርዓት በቴክኖሎጂ ያልተደገፈና ከሰው ግንኙነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ በጨረታዎች ላይ ሙስና የመፈጸም እድሉ ሰፊ እንደነበር የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሃጂ ጠቁመዋል። በቀጥታ በሰዎች አማካይነት የሚሠራ የጨረታ ሥራ ለሙስና ተጋላጭ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው የሚሉት ሃጂ፣ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ያደረገችው የኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት ችግሩን ይቀርፈዋል ብለዋል።
ሥርዓቱ ከዓመታዊ በጀቷ እስከ 70 በመቶ የሚሆነውን ለግዢ የምታውለው ኢትዮጵያ፣ በግዢ ዘርፍ በየዓመቱ በሙስና የምታጣውን ገንዘብ ከማዳኑ ባሻገር፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን የበጀት አጠቃቀም በአግባቡ ማስተዳደር የሚያስችል ነው። በሚቀጥለው ዓመት ማንዋል ግዢን ሙሉ በሙሉ ይተካል ተብሎ የሚጠበቀው ኤሌክትሮኒክስ የመንግሥት ግዢ ሥርዓት የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ዓመታዊ እቅዳቸውን በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ በሥርዓቱ ላይ እንዲያሳውቁ የሚያስገድድ ሲሆን፣ በሥርዓቱ ያልተመዘገቡ አቅራቢዎች ደግሞ በቀረቡ ጨረታዎች ላይ መሳተፍ እንዳይችሉ ይገድባል።
እስካሁን ድረስ 73 የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ወደ ሥርዓቱ እንዲገቡ የተደረገ ሲሆን፣ ሁሉንም የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ወደ ሥርዓቱ ለማስገባት ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በአንክሮ እየሠራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሥርዓቱ ተጠቃሚ ለሆኑ መሥሪያ ቤቶችና አቅራቢዎች ስለ ሥርዓቱ ጥቅምና አጠቃቀም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየሠራ ነውም ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015




በጣም ደስ ይላል በዚህ ቀጥሉበት።