ሕይወት ጉዞ ናት እንደሚባለው ሁላችንም የተሳፈርንበት መጓጓዣ ይለያይ እንጂ ያሰብንበትም ሆነ ያላሰብነው ቦታ ስንደርስ መውረዳችን አይቀርም። እንደከተማ አገልግሎት ሰጪዎች የሰው ልጆች ጉዞም በዓላማና መዳረሻ የተለያየ ቢሆንም፣ መጨረሻውን አውቆ የሚሳፈር እንዳለ ሁሉ ሳያውቅና እየጠየቀ የሚጓዝም መኖሩን የዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ በኃይሉ አበበ ይናገራሉ። ሰው ከሚጓዝበት ተሸከርካሪ ወራጅ አለ ብሎ እንደሚወርደው ሁሉ ሳይወርድ መጨረሻ የሚደርስም ውረድ መባሉ አይቀሬ ነው። በሕይወትም ከነበሩበት ደረጃ ዝቅ በማለትም ወራጅ የሚባሉ እንዳሉ በንፅፅር ፀሐፊው እንዲህ ያሳያሉ።
ከተማ ውስጥ ነው የምትኖሩት? መልሳችሁ አዎ ከሆነ በየቀኑ ምናልባትም ሁል ግዜ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመንቀሳቀስ አውቶብስ፤ ታክሲ ወይም ባጃጅ ትጠቀማላቸሁ ማለት ነው።
ከተማ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ20 ሺሕ በላይ ሰዎች የሚኖሩበት አንድ ሥፍራ ማለት ነው። በዚህ መስፈርት መሠረት በኢትዮጵያ ወደ 1 ሺሕ 200 ያህል የከተማነት ሥም የተሰጣቸው አሉ ማለት ነው። እርሶም ከነሱ በአንዱ ይኖራሉ ብዬ ልገምት። ከተሜነት ደግሞ ከሚለይባቸው ባህርዮች ወይም ነገሮች አንዱ የመሠረተ ልማት መሟላት ማለትም መብራት፤ ውሃ፤ መንገድ፤ ትምህርትና የጤና ተቋማት በአማካይ የሚገኙበት ሲሆን፤ ሌላው የከተማ ሰው መለያ ደግሞ ሕይወት በአብዛኛው በእቅድና በእቅድ የበለጠ የምትመራ መሆኗ ነው። ስለዚህ በየቀኑ ለነገ እናቅዳለን፤ እንወጣለን፤ እንሰለፋለን፤ ወረፋ እንይዛለን፤ እንሳፈራለን የማናውቀውን እየተዋወቅን፤ ከምናውቀው ጋራ የባጥ የቆጡን እያነሳንና እየጣልን እንሄዳለን።
ወዴት ነው የምንሄደው? ወደ መሥሪያ ቤት ወይም ወደ ሥራ ገበታችን፤ ወደ ራሳችን የግል ሥራ ወይም ወደ ተቀጠርንበት የሥራ ቦታ። “… ኢትዮጵያ ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን ቢዝነስ የያዘው ኢንፎርማል ሴክተሩ ነው” ይላል አንድ ሪፖርት። በመሆኑም፣ ከተማ ውስጥ ብዙው ሰው የሚሠራው የግል ቢዝነስ ባለቤት በመሆን የራሱን በመመሥረት፤ የራሱን ቆሞ በመምራት ወይም በመሥራት አልያም ሌሎች ሠራተኞችን በመቅጠር ነው ማለት ነው። ይሄም የከተሜነት አንድ መስፈርት ነው። በአንጻሩ ከተሜ ያልሆኑ ቦታዎች ላይ ጥቂት የመንግሥት ሠራተኞች እንደ ብርቅ እንደሚታዩም የቅርብ ግዜ ትውስታችን ነው። እኔ እንኳ ዛሬ ላወጋችሁ የፈለኩት ስለ ከተሜነትና ተያያዥ ጉዳዮች አይደለም። ከተሜነት ካደመቁት ኮከቦች አንዱ ስለሆኑት ትራንስፖርቶቻቸው እንጂ።
ፈልገንም ሳንፈልግም፤ አቅደንም ሳናቅድም በሕይወት አጋጣሚ አብረን አንድ ታክሲ እንሳፈራለን። እንበልና አሁን አንድ ታክሲ አብረን ተሳፍረናል። ከዚህ በታች የማካፍልዎ የታክሲ ላይ እሳቤዎችና ዕይታዎቼን ነው። አብረን ከአንድ የታክሲ ተራም ይሁን ፌርማታ የተሳፈርን ብዙዎች አንድም ፌርማታ ኹለትም ፌርማታ … እያልን እንወርዳለን። የደረሰ እየወረደ፤ ያልደረሰ ለቀጠሮው እየጓጓ፤ በመሃል በወረዱት ተሳፋሪዎች ምትክ ሌሎች ተሳፋሪዎች እየተሳፈሩ እስከ መጨረሻው ፌርማታ እንሳፈራለን።
የመጨረሻዎቹ ወራጆች የመጨረሻው ፌርማታ ላይ እንወርዳለን። ከዚያም ወደ ጉዳያችን ወይም ሥራችን እናመራለን። ደራሲ አዳም ረታ ለጋሽ ስብሃት ገበረእግዚአብሔር እረፍት የጻፋትና በደራሲ አለማየሁ ገላጋይ አርታኢነት በቀረበው “ስብሃት ገበረ እግዚአብሔር ሕይወትና ክህሎት” የሚል መጽሐፍ ላይ ያቀረባት አንድ መጣጥፍ ርዕስ “ሕይወት ፌርማታ ናት ። ሁላችንም ደርሰን የምንወርድባት” /ቃል በቃል አይደለም/ ብሏል። ሁሉም ሰው አንድም ብዙም መውረጃ ቦታዎች አሉት። ለአንድም ለብዙም ጉዳይ ታክሲ የተሳፈርነውን ያህል በነዚያው ምክንያቶች እንወርዳለን።
የከተማን ሕዝብ በትከሻቸው የተሸከሙት የአውቶብስና የታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች ከጠዋት እስከ ማታ ሳይሰለቹ የሚሰሙት አንድ የጋራ ድምጽ ቢኖር፣ “ወራጅ አለ!” የሚለውን ቃል ነው ብዬ እገምታለሁ። እኛም ተሳፋሪዎች ለምዶብን ምናልባት በህልማችንም ጭምር ልንል የምንችለው አንድ ቃል ቢኖር “ወራጅ አለ!” ሳይሆን ይቀራል ብላችሁ ነው?
አንድ ነን ማለት ነው? ተሳፋሪዎቹ ብዙ ናቸው። ኹለት ጾታዎች፤ ለብዙ ጉዳዮች፤ አንዱ ለሕይወት አንዱ ለሕክምና ብዙ ዓይነት መልኮች፤ ብዙ ዓይነት ባህሪዎች፤ ብዙ ዓይነት የእድሜ እርከኖች፤ ብዙ ዓይነት ባህርይ ያላቸው ሰዎች፤ ቆንጆዎችና ቆንጆ ያልሆኑቱ፤ ብዙ ዓይነት የትምህርት ደረጃዎችና የኢኮኖሚ ሁኔታዎች፤ ብዙ ብዙ ሆነን…ግን በአንድ አውቶብስ፤ በአንድ ታክሲ …አንድ አገር… እያልን እንሄዳለን።
ተሳፍረናል። ታክሲ ከሆኑ እስቲ አሁን ከጎንዎ ማን አለ? እንደተሳፈርን አንቀርም አይደል? መድረሻችን ስንደርስ ወይም የምንፈልገው ቦታ ስንደርስ መውረድ አይቀርምና ከታክሲ እንወርዳለን። ብዙ ዓይነት ወራጆች አሉ መውረጃቸውን አውቀው ቀድመው ያቀዱና የተዘጋጁ፤ መውረጃቸውን ቀድመው ያወቁና ያቀዱ ግን ያልተዘጋጁ፤ መውረጃቸውን ያላወቁ ያቀዱና የተዘጋጁ፤ መውረጃቸውን ያላወቁና ያልተዘጋጁ ወዘተ። ቀድመው ያወቁ እያቀዱ እየወረዱ፤ ያላወቁም እያቀዱ እየጠየቁ እየወረዱ…. ይቀጥላል። እንዲህም ሊሆን ይችላል፦ ቀድመው መውረጃ ቦታቸውን ተናግረው የሚወርዱ ያሉትን ያህል በሐሳብም ጠፍተው ወይም በግዴለሽነት እዚያው መውረጃቸው ሲደርሱ “ወራጅ አለ!” ይላሉ።
አዲስ አበባ ውስጥ አሉ ከምንላቸው ኢትዮጵያዊ እሴቶች ውስጥ አንዱ አድራሻ የሚጠቁመን አለመጥፋቱ ሲሆን፣ ሰው ያለምንም ጥርጥርና ማንገራገር ሊተባበርዎ ከሚችላቸው ነገሮች ጥቂቱ እንደሆነ እንኳን እኔ ሚሊዮኖች ይመሰክራሉ። ጋስ ስብሃት “ሃበሻ አፍንጫው ወዳመለከተበት ይመራሃል” ቢልም፣ በሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ጋሽ ስብሃትንም እነ ስንዱና እንዳለጌታ ቤቱ ሲጠፋው እየተከተሉ ቤቱ ያስገቡት ነበር አሉ። ጨዋዎች አሉ፤ ባያውቁም ጠይቀው ከመውረጃ ቦታቸው ሲደርሱ ቀድመው ተናግረው የሚወርዱ። ይሄ በነገራችን ላይ ሥልጣኔም መሆኑን መዘንጋት የለብንም፤ “አላውቅም እርዳኝ!” ማለት።
ቀድሞ ያወቀ መውረጃውን ያሳወቀ እየወረደ፤ መውረጃውን የጠየቀም እየተመራ ይወርዳል። እዚህ ጋራ ጥቂቶቹን መዘንጋት የለብንም፤ ችግር ፈጣሪዎቹን። እንዲህ ይላሉ “እዚህ ጋር ያዝልኝ” የፖሊስ ትእዛዝ በመሰለ ድምጽና የቅርብ ባልመሰለ ሸካራ ድምጽ… እኔ ሲገባኝ መቼም መኪና እግር አይደል ባንዴ የሚቆመው። አንዳንዱ እዛው መውረጃ ቦታው ሲደርስ “ወራጅ አለ!” ይላል ደግሞ። ሾፌሩ እዚያው ፍሬን ይዞ እዚያው በደቂቃ ውስጥ ካላቆመለትና ካላስወረደውማ ሌላ ክርክርና ንትርክ እንዲሁም ብጥብጥ ይከተላል። መነጫነጭ የባህርዮ ከሆነ ወይ ቀድሞ ማሳወቅ አልያም መታከም ነው። ራስን መግራት ለጥቂት ደቂቃዎች ቢከተል እኔ የሰማዎት ራሱ እንዲህ አልልዎትምና።
ያልተገባ ንግግር የሚናገሩ፤ ስድብ የሚሳደቡም አይጥፉም። በነገራችን ላይ እንኳን መሳደብ ሰውን ለመናገር እኮ ራሱ ማስፈቀድ አለብን ይላል ሳይንሱ። የማኅበረሰባችንን ሃቅና እሴት እዚህ ጋራ ሳልዘነጋ ማለቴ ነው። አንዳንዱ የባሰበትማ የትጋ ታክሲ እንደሚቆምና እንደማይቆም እንደ ተሳፋሪም ብናስረዳው ራሱ ከሹፌሩ ገቢ ተካፋይ የሆንን ያህል እስኪሰማን ድረስ ሊነግረን ይዳዳዋል። ሳንከፍል የረዱን፤ በሐሳብ ጠፍተንና የምንሄድንበት ቦታ በሐሳብ ገዝቶን ሳንከፍል ስንረሳና ስንሄድ ያለፉንን በዚች ስህተት ያለሆነ ነገር መናገር ያስተዛዝባል። ከሾፌሮችም ከታች በጠቀስኩት ምክንያትና በሌሎችም ምክንያቶች ሊያስቀይሙን ቢችሉም።
እኔ እንኳ ብዙ አወራሁ አይደል!? አይገርምም ወደ ዋናው ነጥቤ አልገባሁምኮ። እኔ እንደዚህ አምናለሁ ስልህ! ከላይ እንዳልኩህ ነው። አንተም እንደዚህ ብታምን ሳይሻል አይቀርም። ….አዎ በሕይወት ውስጥ “ወራጅ አለ!”። በቃ ትወርዳለህ። እዚህ ጋራ በጋራ እንዲህ እናስብ። እዚያው ፍሬን ቢይዝ አንድም ከኋላ መኪና መጋጨት፤ ሁለትም ያልተፈቀደ ቦታ በማቆም ቅጣት፤ ሦስትም የፍሬን ሸራና ጎማ መጨርስ ነው አይደል? ይሄ ያንተም ሀብት አይደል እንዴ ታዲያ? እነሱ እንደሆነ እንዳንተ ዓይነት 100 ሺሕ፣ 200 ሺሕ ሰዎች አገልግለዋልና ሾፌሮቹ አይገርማቸው! ሌላ እንዳንተ ዓይነት ሰው ጭነው ይቀጥላሉ። መላ ይክፈል እንጂ ማንንም አያገሉም። ሁሉንም በአግባቡ እንደጸባዩ ያገለግላሉ። አድርሰው ይመልሳሉ መልሰው ያደርሳሉ።
የክፍለ አገር ልጅ ለዩኒቨርሲቲ በል ለትምህርት፤ ለሥራ በል ለሌላ ጉዳይ ለውጭ አገር ጉዞ በል ለሕይወት ጉዳይ….ቦታ የመሩህ የአዲሳባ ታክሲ ሾፌሮችና ረዳቶች አይደሉም ነው የምትለኝ። “ወራጅ አለ!” ከማለታችን በፊት በተከፈለ ልብ፤ ባለማወቅ ፍርሃት እንጀራችንን ለማብሰል ቦታ አልጠየቅናቸውም ካላችሁኝ ከማርስ ነው የመጣችሁ ብል ማጋነን አይሆንብኝም።
አሁንም ታክሲ ውስጥ ናችሁ አይደል? ተደላድላቹ ተቀምጣችኋል አይደል ሰዓት ረፍዷል አይደል፤ አምሳ ሜትር ቀድማችሁ “ወራጅ አለ!” አላላችሁም አይደል፤ ሽንኩርት ኪሎ 45 ብር ገብቷል አይደል፤ ትምህርት ቤት ክፍያና የመስከረም በአሎች ኪሳችንን አራቁተዋል አይደል፤ ልጅ አልመከር ብሏል አይደል፤ ሚስት ባህሪዋ ተቀይሯል አይደል፤ ፌስቡክ መልካም ዜና አንሶታል አይደል፤ ሌባ በከተማ በዝቷል አይደል፤ ጓደኛችን ፖለቲከኛ ሆኗል አይደል፤ ያለመተማመን ነግሷል አይደል፤ ምን ያልሆነ ነገር አለ ‘ሁሉም ያማል’ አይደል?!
…ይሄን ሁሉ የተሸከመ ምናልባትም አንድ ሰው ነን አይደል ታክሲ የተሳፈርነው። የታክሲ ሾፌሩም እንደዚያ! ምነው ወንድም ዓለም፤ ምነው እህት ዓለም እሱምኮ ያንተን/ያንቺን ያህል ይሄን ያህል ራስ ምታት እያለበት ነው ሰውን ከእንጀራውና ከጉዳዩ የሚያደርሰው። ራስን መግራት አይሻልም ብለህ ነው ወይ ታዲያ የማናውቀውን አንድ ሾፌርና ረዳት ምናልባትም በሕይወት ዘመናችን ላናገኝ የምንችላቸውን ሰዎችና ምናልባትም ከደቂቃዎችም በኋላ በሕይወት ዘመን ላናገኘው የምንችለውንና መውረዳችንም አይቀርምና ለሦስትና አምስት ደቂቃዎች ትዕግስት አጥተን መልካም ያልሆነ ነገር ክፉ የተናገርናቸው ሰዎች አያሳዝኗችሁም!
እሺ እኛስ ለምን ከአፋችን በወጣ ቃል ለምን እንመዘናለን? ከደቂቃዎች በኋላኮ ሌላ ቦታ ሌላ ጉዳይ ላይ ልንሆን እንችላለን፤ ምናልባትም አንዱ አገልግሎት ሰጪ አንዱ ተገልጋይ! እንደው በራሳችሁ መኪና በግልም ይሁን በመሥሪያ ቤት መኪና ያልተፈቀደ ቦታ እንደደረሰ ያዝልኝ ቢላችሁ ጠላቴ ነው እንዴ እስክትሉ ድረስ አትገረሙም? አንድ ወዳጄ እንዲያውም የአዲስ አበባን አውቶብስና የታክሲ ሾፌሮች “ያዲሳባ ትከሻዎች” ይላቸዋል። ለነገሩ ምን ያልተሸከሙት ነገር አለ። ሥራ ፈላጊና ኹለት ሥራ የሚሠራ ጨምሮ። አዲስ አበባን የማያውቃት ግን በውስጧ አዲስ አበባን አቋርጦ የሚያልፍ። ከአገር ውስጥም ከአገር ውጭም። ይሄ ከዚህ በላይ የምለው ግን ሥርዓት አልበኞቹንና ተሳፋሪ በሆነ ባልሆነው የሚያንጓጥጡትን አይጨምርም።
ለሁሉም ወደ ዋናው ጉዳዬ ልመለስ።
ከኒው ዮርክም፣ ከጄኔቫም፣ ከለንደንም፣ ከመቀሌም፣ ከወለጋም ተቀብለው አገር ያደርሳሉ፤ አገር ያላምዳሉ፤ ስለ ሃገሩም Update ያደርጋሉ፤ የአዲሳባ ታክሲዎች። እኔ የክፍለ አገሩ ልጅ አዲስ አበባ የምትናፍቀኝን ያህል እነሱ የለንደንና የዋሽንግተን ጉደኞቻቸው ይናፍቋቸዋል፤ እንደነገሩን። አንተም ካልተካካድን ይቺን እንደው አትክደኝም። …ያው አሰራሩ ነው የ<city citizen> ልበልህ!። ያው ከሰዉ ከአገሩ ይቀላቅሉሃል፤ ያላምዱሃል። ከጊዜ በኋላ አንተም አዲሳባ ባትወለድም ከሦሶቱ አንዱ ላይ የመሆን እድልህ 1 ሚሊዮን ከ100 ሚሊዮንኛ ነው። ወይ ሾፌርነቱን ትቀላቀላለህ ወይም ረዳት ሆነህ ሜክሲኮን መስኪኮ እያልክ ታድጋለህ አልያም ተሳፋሪ ትሆናለህ። አራተኛዎቹም ባለ መኪናዎቹም እክል ሲገጥማቸው ታክሲ ይቀናቸዋል አሉ።… ይሄን ነገር ከዚህም በላይ አስበው …በሰው ልክነት ምታው…በኔና ባንተ እንጀራ አስላው።
በአንጻሩ! ከዚህ በታች ደግሞ “ወራጅ አለ” ስል አንድ ሰው ከወጣበት አንድ ነገር ወይም ደረጃ ማለትም ከትምህርት ፤ ከሥልጣን፤ ከሀብት፤ ከእድሜ፤ ከኅብረተሰብ፤ ከመታመን፤ ከሥነምግባር ደረጃ ወደ ታች መውረድ ማለቴ ነው፤ ሞትንም ይጨምራል። የክብር ሞት እንዳለ አልረሳሁም፤ ግን ‘ወርዶ’ መሞትም እንዳለ እንዳንዘነጋ ብዬ ነው። የሞትም ውርደት አለው ለማለት ያህል ነው። “death has ritual” ያለውን ፈላስፋ አልዘነጋሁትም። መውረድ ሙሉ በሙሉም ቅጣት ነው አልልም። ከልክ መጉደል ግን መውረድ ነው። …ወደ ላይ እንደመሄድ ወደታቹን መጀመር ግን ያው መውረድ ነው ማለቴ ነው። የሰርክ የተፈጥሮ ሕግም ነውና መውረድ በሕይወት መልኮች ውስጥ ተጽፏልና አለ ይኖራል። ለምሳሌ ሰው በእርጅና ምክንያት የማድረግ አቅሙ ሊወርድ ይችላል፤ ይሄንንም ማለቴ አይደለም።
በተለያየ ምክንያት የሰው ልጅ ይወርዳል፤ ለምሳሌ በመልካም። ፍቅር “ወራጅ አለ” ብሎ ልብ ጥሎ ያፋቀራቸው እንዳሉ እናውቃለን፤ ትዕቢት “ወራጅ አለ” ብሎ ለትዕግስት ሲያንበረክካቸውም ታዝበናል፤ ጭብጨባም ጎርፍ ሆኖ ሊወስዳቸው ሲገማሸር “ወራጅ አለ” ብለው በጎን ያሳለፉና ትህትና በኃይል ግዳይ ሲጥላቸውም አይተናልም አንብበናልም። ክፉዎች ክፋታቸውን “ወራጅ አለ” ሲሉ ትተው ለበጎ ሲሰለፉም ሰምተናቸዋል። ከእቡይነት “ወራጅ አለ” ብለው የወረዱና ታዛዥ የሆኑ አሉ። እነሱ ለመልካም የወረዱ “ወራጅ አለ” ባዮች ናቸው። እንዲህ ብንወርድ አይሻልም ብላችሁ ነው?
በአንጻሩ መልካም ያልሆነ አወራረድ ወርደው የተጎዱ “ወራጆች” ይኖራሉ። በሕይወት ውስጥ ዛሬ የሚወለድ ዛሬ የሚቀናው ሥልጣንም ሀብትም እውቀትም የሚያገኝ ሰው የኖረውን ያህል፤ ዛሬም ከሕይወት ደረጃዎች ደርዝ ወደ ታች ባልተገባ መንገድ “ወራጆች አሉ!” ዛሬን ለፍተው ደክመው፤ ወጥተው ወርደው፤ ላባቸውን አንጠፍጥፈው አልመው አቅደው ያልተሳካላቸው “ወራጆች አሉ!” ይሄም የተፈጥሮ ሕግ ነው። ከክብር መውረድ ይኖራል፤ ከሥልጣን መውረድም አይቀርም፤ ጊዜም ጊዜ ከድቶት ምናልባት ከጊዜም ይወረዳልና። ሁሌ ትክክል አይኮንምና አንድም ቀን አንድም ሰዓት መውረድ በሕይወት ውስጥ አለ፣ በስሜት እንበለው በእውቀት። አትጠራጠሩ መቼ ነው የሚለውን ነው እንጂ የማናውቀው መውረድማ አይቀርም። ያስፈራል።
“ወራጅ አለ” የሕይወት መርሃችን ቢሆን ጥልና ክርክር እንዲሁም ጠላትነት ቦታቸው ይቀንሳል ብዬ አስባለሁ። እኛ እያለፍንም፣ ጊዜም እየሄደ፤ እኛም “ወራጅ አለ” እያልን በጎ ካልሆኑ ነገሮቻችን ላይ እንውረድና ቀጣዩን ለቀጣዩ ተሳፋሪ ቦታ እንልቀቅ። ከታክሲ ውስጥ በሕይወት፤ ከሕይወት ደግሞ በሞት “ወራጅ አለ” ባይነት መውረድ የሚቀረው የሰው ልጅ የቱ ነው? በሞት ወርደን ወይ ለገነት አልያም ለሲኦል በሞት “ወራጀ አለ” ባይነት አንድ ቀን የሰው ልጅ ከዚህ ዓለም በመሞት ‘መውረዱ’ አይቀርም። እኔ እንዲያውም ሞት “ወራጅ አለ!” እያለ ከጎናችን የሚያሽሟጥጥ ይመስለኛልና እባካቹ መልካም የሆነ አወራረድ እንውረድ። አልደረስንም? ደርሰናል? “እንደርሳለን!” ይላል ትራንስፖርት ሚኒስቴር ያውም በ30። እኔም ዕይታዬን ካካፈልኩበት ከዚህ ፁሑፍ ስለደረስኩ “ወራጅ አለ” ብያለሁ፤ “አትጨቃጨቁ፤ ተሸጋሸጉ በቃ ወራጅ አለ!”!
የዚህ ፅሑፍ አዘጋጅ በኃይሉ አበበን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ያገኙዋቸዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015



