ማክሰኞ ጥቅምት 22 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ የነበሩት ቤንጃሚን ወንዴ እሁድ ጥቅምት 20 ቀን ምሽት ባልታወቁ ግለሰቦች በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።
የቀብር ሥነ ስርዓታቸውም በትውልድ ሥፍራቸው ምዕራብ ጎጃም ዞን አዴት ወረዳ ኮቲ ቀበሌ ማህደሪቱ ማሪያም ቤተክርስቲያን ወዳጅ ዘመዶቻቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው በተገኙበት ትናንት ጥቅምት 21/2015 ከቀኑ 7:00 ላይ ተፈጽሟል።
የከተማ አስተዳደሩ በቤንጃሚን ወንዴ ድንገተኛ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን የገለጸ ሲሆን፤ የከንቲባ ጽ/ቤቱ ከፍተኛ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆነው ህይወታቸው እስካለፈበት ዕለት ድረስ በቅንነት፣ በታማኝነት ከምንጊዜውም በላይ ደግሞ ከሥራ ባልደረቦች ጋር በፍጹም ወንድማማችነት አብሮ የመሥራት ባህል እንደነበራቸውም ገልጿል።



