የኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም በሦስት ወራት ውስጥ የ9.8 በመቶ እድገት ማሳየቱን ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አጠቃቀም በ9.8 በመቶ ማሳደግ መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም፣ በ2015 የበጀት ዓመት የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም አጠቃቀም 65 በመቶ ለማድረስ እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የማምረት አቅም አጠቃቀም ኢንዱስትሪዎች እንዲያመርቱ ታስቦ ከተገነቡበት መጠን ምን ያህሉን በማምረት ላይ እንደሚገኙ የሚለካ ሲሆን፣ ለበርካታ ዓመታት የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም ከ50 በመቶ በታች እንደነበር ታረቀኝ ተናግረዋል። በ2014 የበጀት ዓመት መጨረሻም ይሄው የማምረት አቅም አጠቃቀም 42.7 በመቶ የነበረ ሲሆን፣ በ2015 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራትም ይህንን ምጣኔ ወደ 52.5 በመቶ ማድረስ እንደተቻለ ታረቀኝ ገልጸዋል።
ከአምራች ኢንዱስትሪዎች የጨርቃ ጨርቅ እንዲሁም የምግብና መጠጥ አምራች ዘርፎች ከ60 በመቶ በላይ አጠቃቀም በማሳየት የተሻለ አፈጻጸም ያላቸው ሲሆን፣ የብረታ ብረትና የቆዳ ዘርፎች ደግሞ ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዳሳዩ ታረቀኝ ተናግረዋል። የማምረት አቅም አጠቃቀም ዝቅተኛ እንዲሆን የዳረጉ በርካታ ምክንያቶች እንዳሉ የገለጹት ታረቀኝ፣ ከነዚህም መካከል የግብአት አቅርቦትና የኋልዮሽ ትስስር አለመስተካከል፣ የሥራ ማስኬጃ ካፒታል እጥረት፣ የገበያ ትስስር ችግሮች፣ ለኢንዱስትሪ የሚያስፈልግ በቂና በአግባቡ የተማረ የሰው ኃይል እጥረት እንዲሁም የመብራት መቆራረጥ ችግሮች ተጠቃሽ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም አጠቃቀማቸውን ለማሻሻል አቅደውና ክፍተቶቻቸውን ለይተው ለማስተካከል እንዲሠሩ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ የተናገሩት ታረቀኝ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ከኢንዱስትሪዎች ጋር በመተባበር የሰው ኃይልን ማብቃት ላይ በሰፊው እንዲሠሩ በማድረግ ላይም እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንዳለ ተናግረዋል።
“ኢትዮጵያ ታምርት” በሚለው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የ10 ዓመት ፕሮጀክትም፣ ከአምራች ኢንዱስትሪው ምርቶች ወደ ውጭ አገራት በመላክ በ10 ዓመታት ውስጥ 10 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት የታቀደ ሲሆን፣ በ2014 የበጀት ዓመት 500 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ የሚታወስ ነው። በ2015 የበጀት ዓመት ደግሞ 527 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዷል።
የዐስር ዓመቱ ፕሮጀክት እንዲሳካም ይህንን የማምረት አቅም አጠቃቀም ከፍ በማድረግ ኢንዱስትሪዎች አሁን ባላቸው መሠረተ ልማት እያመረቱ ያሉትን ምርት በእጥፍ ማሳደግ እንደሚቻልም ተነግሯል።
አሜሪካ ለአፍሪካ አገራት ከሰጠችው ከቀረጥ ነጻ የገበያ እድል (አገዋ) ኢትዮጵያን ከማስወጣቷ ጋር ተያይዞ የገበያ ትስስር ችግሮች እንዳሉ የተናገሩት ታረቀኝ፣ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔውን በድጋሚ ያጤነዋል የሚል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ይሁንና የአገዋ እድልን በድጋሚ ማግኘት ባይቻል እንኳን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው ሌሎች አማራጭ ገበያዎችን በማፈላለግ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከ30 የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ከ200 በላይ የጨርቃ ጨርቅ ዘርፍ አምራቾች የሚሳተፉበትና ከስድስት ሺሕ በላይ ጎብኚዎችና ገዢዎች እንደሚሳተፉበት የሚጠበቅ ‘የአፍሪካ ሶርሲንግና የፋሽን ሳምንት’ በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ጥቅምት 25 መካሄድ የጀመረ ሲሆን፣ እስከ ጥቅምት 28 ድረስ ቆይታ ይኖረዋል። በዚህ ዝግጅት ላይም 39 አገር በቀል የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት አምራቾች በመሳተፍ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ መሰል ዝግጅቶችም አማራጭ ገበያዎችን ለመፈለግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ታረቀኝ ተናግረዋል።
ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015


