የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ምቹ አለመሆን በፍርድ ቤቶች ሥራዎች ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የፌዴራል ፍርድ ቤቶች የ2015 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸማቸውን ጥቅምት 23/2015 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርበው ወይይት በተደረገበት መድረክ ላይ የምቹ ሁኔታዎች አለመኖር ለሥራቸው እንቅፋት መሆኑን አስረድተዋል።
በወይይት መድረኩ እንደ ተግዳሮት ከተነሱት ችግሮች መካከል የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በፍርድ ቤት ከፍተኛ ጫና መፍጠሩ፣ የፍትሕ አካላትና የፍርድ ቤቶች በጋራ አጀንዳ ላይ የሚጠበቀውን ያህል አለመሥራታቸውን በቀዳሚነት ተነስተዋል። የፍርድ ቤቶችን ተግዳሮት ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝደንት ሰለሞን አረዳ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ መንግሥት የፍርድ ቤቶችን ተልዕኮ አለመገንዘቡ አሁንም የፍርድ ቤቶች ተግዳሮት ሆኖ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በመንግሥት በኩል የሚታየው የፍርድ ቤቶችን ተልዕኮ አለመገንዘብ በማኅበረሰቡ ዘንድም እንደሚታይ ምክትል ፕሬዝደንቱ ለቋሚ ኮሚቴው የገለጹ ሲሆን፣ የፍርድ ቤቶችን ተልዕኮ ካለመገንዘብ የሚመነጩ ችግሮች በፍርድ ሥርዓቱ ላይ ተጽእኖ መፍጠራቸውን ጠቁመዋል። እንዲሁም በፍርድ ቤቶች ሥራዎች ላይ የጠበቆች ሚና አናሳ መሆን እንደ ተግዳሮት ተነስቷል።
በውይይት መድረኩ ላይ ከቋሚ ኮሚቴ፣ ከፌዴራል ፍርድ ቤቶችና በውይይቱ ላይ ከታደሙ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ከተለያዩ አካላት በፍርድ ቤት ተልዕኮዎችና ሥራ ላይ የተዛቡ አመለካከቶች እንደሚነጸባረቁ አንስተዋል። በተለያዩ አካላት የሚንጸባረቁ የተዛቡ አመለካከቶች በፍርድ ቤቶች ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድሩም ተመላክቷል።
በፍርድ ቤቶች ላይ ከተለያዩ አካላት ከግንዛቤ እጥረት የሚንጸባረቁ አሉታዊ ግንዛቤዎችን ለማስቀረት ፍርድ ቤቶች ከማኅበረሰብ እስከ ባለድርሻ አካላት የግንዛቤ መስጫ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚገባቸው ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል። በውይይት መድረኩ ላይ የሩብ ዓመት ሪፖርታቸውን ያቀረቡ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች፣ ስለ ፍርድ ቤት የሚንጸበረቁ የተዛቡ አመለካከቶች መስተካከል እንዳለባቸው አንስተዋል።
ፍርድ ቤቶች የበጀት ዓመቱን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሪፖርት ባቀረቡበት መድረክ፣ የውይይት መድረኩ ታዳሚ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች አለመፈጸም በፍርድ ሥርዓቱ ላይ እየፈጠረ ስላለው ችግር ጠንካራ ጥያቄዎችንና አስተያየቶችን ለፍርድ ቤቶች አመራሮች ሰንዝረዋል።
የውይይቱ ተጋባዥ የሆነው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት ዳይሬክተር መስዑድ ገበየሁ፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዞች አለመክበር፣ የመገናኛ ብዙኀን ባለሙያዎች፣ የሰብዓዊ መብት ታጋዮችና የተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ያለ ፍርድ ለረዥም ጊዜ መታሰራቸው ማኅበረሰቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን እምነት የሚሸረሽርና ስለ ፍርድ ቤት የሚኖረውን ግንዛቤ የሚያዛባ መሆኑን አንስተዋል።
የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ፕሮግራም ዳይሬክተር አጥናፉ ብርሃኔ በውይይት መድረኩ፣ ፖሊስ የፍርድ ቤት ትዕዛዞችን አለማክበሩን እንደ አንድ ችግር አንስተዋል። አጥናፉ ለፍርድ ቤት አመራሮች ባቀረቡት ጥያቄም፣ ፍርድ ቤቶች የውሳኔዎቻቸውን አለመከበር እንዴት እንደሚየዩት እና ውሳኔውን ለማስፈጸም ምን ያክል እንደሚከታተሉ ጠይቀዋል።
የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበርን የተመለከቱ ጥያቄዎች በውይይቱ ጎልተው የታዩ ጥያቄዎች ሲሆኑ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት መዓዛ አሸናፊን ጨምሮ የፍርድ ቤት አመራሮች ፍርድ ቤቶች ውሳኔያዎቻቸውን ተከታትለው እንደሚስፈጽሙ እና በተወሰነ ሁኔታ ችግሩ እንደሚታይ አንስተዋል። መዓዛ ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ የፍርድ ቤት ውሳኔን የማስፈጸም የዳኞች ኃላፊነት ነው ያሉ ሲሆን፣ ዳኞች ውሳኔዎቻቸውን እንደሚያስፈጽሙም ጠቁመዋል።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ብርሃነመስቀል ዋጋሪ በበኩላቸው በሰጡት ምላሽ፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ መከበር እንዳለበት አሳስበዋል። በመሆኑም፣ ፍርድ ቤቶች ትዕዛዞቻቸውን የማስፈጸም ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ ጠቁመዋል። የፍርድ ቤት ትዕዛዞች አለመከበር አሁንም የቀጠለ ችግር መሆኑ እንደ ተግዳሮት ተነስቷል።
ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015


