ከዚህ ቀደም 102 ሺሕ ዜጎችን ለማስመለስ ዕቅድ ተይዞ በ198 በረራዎች 71 ሺሕ 697 ሰዎች መመለሳቸው ተገልጿል
ረቡዕ ጥቅምት 30 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) ተቋርጦ የነበረው እና በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ኹኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ዳግም የማስመለስ ሥራ ህዳር 12 ቀን 2015 እንደሚጀመር ብሄራዊ ኮሚቴው ገልጿል።
ከ16 ሴክተር መስርያ ቤቶች የተውጣጣው ብሄራዊ ኮሚቴው ዜጎችን ለማስመለስ የተሰሩ አጠቃላይ ዝግጅቶችን በትናንትናው ዕለት የገመገመ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም የነበረውን የሥራ አፈፃፀምም ገምግሟል።
የብሄራዊ ኮሚቴው ሰብሳቢና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ መንግስት ዜጎችን ለማስመለስ ያለውን የፀና አቋም የገለፁ ሲሆን ከመጡ በሗላ የሚያርፉበት ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ዝግጁ መሆኑን አሳውቀዋል፡፡
አምባሳደር ብርቱካን የተያዘውን ብሄራዊ እቅድ ከግብ ለማድረስ የሚመለከታቸው የፌዴራል እና የክልል ተቋማቶች በቅንጅት መሰራት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህ ቀደም ዜጎችን በማስመለስ ሂደት ያጋጠሙ ችግሮች እንደነበሩ ኮሚቴው ያነሳ ሲሆን፤ በዚህም የአሸባሪ ቡድን ተላላኪዎች እና የሌላ አገር ዜጎች ከተመላሾቹ ጋር በተጭበረበረ ሰነድ ለመግባት መኩረው አስቀድሞ በተደረገ የማጣራት ስራ ሊያዩ መቻላሉን በውይይቱ ተጠቅሷል።
ከዚህ ቀደም ከሳዑዲ አረቢያ 102 ሺሕ ዜጎችን ለማስመለስ ዕቅድ ተይዞ በ198 በረራዎች 71 ሺሕ 697 ሰዎች በማስመለስ የታቸለ ሲሆን የብሄራዊ ኮሚቴ አባላትም በዕቅድ ተይዞ፤ ሳይመለስ የቀሩትን 30 ሺሕ 303 ዜጎችን ከህዳር 12 ቀን 2015 ጀምሮ ለማስመለስ 16ቱም የኮሚቴው አባል ተቋማት የበኩላቸውን ዝግጅት ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።



