የኩባንያው ጠቅላላ ሀብት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል
ኅብረት ኢንሹራንስ በፈረንጆች 2021/22 በጀት ዓመት ከግብር በፊት ከ206 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱን ገለጸ።
ይህም ከባለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ21 ነጥብ 5 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ እና የኩባንያው የበጀት ዓመቱ የተጣራ ትርፍም ከ181 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑ ነው የተመላከተው።
ኩባንያው 28ኛ የባለአክሲዮኖች መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ባደረገበት ወቅት እንደገለጸው፣ ከቀጥታ የመድን ዘርፍ ያገኘው ትርፍ ከ247 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ሲሆን፣ ይህም ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ17 በመቶ ብልጫ አለው ብሏል።
እንዲሁም ሕይወት ነክ ካልሆነው የመድን ዘርፍ ኩባንያው ከ860 ሚሊዮን ብር በላይ የአረቦን ገቢ መሰብሰብ መቻሉ ተጠቁሟል።
ከኹሉም የመድን ዘርፎች በተለይ በአቪዬሽን ኢንሹራንስ ዘርፍ ከፍተኛ እድገት የተመዘገበ ሲሆን፣ ይህም ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ሬድ ስታር አቪዬሽን ለተባለ ድርጅት አውሮፕላኖች የመድን ሽፋን በመሸጡ ምክንያት መሆኑ ነው የተገለጸው።
በበጀት ዓመቱ ከፍተኛ የአረቦን ገቢ የተሰበሰበው ከሞተር ኢንሹራንስ ዘርፍ መሆኑን በመጥቀስም፣ ሕይወት ነክ ከሆነው የመድን ዘርፍ ከ93 ሚሊዮን ብር በላይ የአረቦን ገቢ መገኘቱን ኩባንያው አመላክቷል።
ስለሆነም ከኹለቱም ዐቢይ የመድን ዘርፎች የተሰበሰበው አጠቃላይ የአረቦን ገቢ፣ ከባለፈው በጀት ዓመት የ30 በመቶ እድገት በማሳየት ከ953 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑ ተጠቅሷል።
በበጀት ዓመቱ ኩባንያው ሕይወት ነክ ባልሆነው የመድን ዘርፍ አጠቃላይ የከፈለው የካሳ ክፍያ ምጣኔ ከባለፈው ዓመት ከነበረው ጋር ተቀራራቢ መሆኑም ነው የተገለጸው። በጠቅላላ እና በሕይወት ነክ የመድን ዘርፎች ለካሳ ክፍያ የወጣው ወጪ፣ ከባለፈው በጀት ዓመት በ21 በመቶ በማደግ ከ349 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
ይህም በዋናነት የኩባንያው የአረቦን ገቢ ማደግ፣ ከተሽከርካሪ አደጋ መብዛት እና የመለዋወጫ ዕቃዎች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ጋር የተያያዘ መሆኑ ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል ኅብረት ኢንሹራንስ የተከፈለ ካፒታል 500 ሚሊዮን ብር በመያዝ፣ ጠቅላላ ሀብቱ ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ተመላክቷል። ኩባንያው ጠቅላላ የባለአክሲዮኖችን ቁጥር ወደ 519 ማሳደጉም የተገለጸ ሲሆን፣ በሪል እስቴት ኢንቨስትመንት ዘርፍ በመሰማራት ተጨማሪ ገቢ የሚያገኝ መሆኑም ነው የተጠቀሰው።
እንዲሁም ኩባንያው ሰኔ 30/2022 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በኅብረት ባንክ እና በኢትዮጵያ የጠለፋ ዋስትና ኩባንያ ካሉት ኢንቨስትመንቶች ጨምሮ ከተሰማራባቸው የተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ከ173 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ያገኘ ቢሆንም፣ ከሀበሻ ሲሚንቶ አክሲዮን ማኅበር ካሉት አክሲዮኖች ያገኘው የትርፍ ድርሻ አለመኖሩን ጠቁሟል።
ከ460 በላይ ሠራተኞች እንዳሉት የጠቀሰው ኩባንያው፣ ለሠራተኞች የተለያዩ የሙያ እና የአመራር ሥልጠናዎችን ለመስጠትም ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ነው የገለጸው።
ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015



